“የአጨራረስ ችግር ታይቶብናል” አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ

ሌሶቶን ያስተናገደችው ኢትዮጵያ ያለምንም ግብ ከተለያየችበት ጨዋታ በኋላ የዋሊያዎቹ አስልጣኝ አብርሀም መብራቱ የሰጡትን አስተያየት እንደሚከተለው ሰጥተዋል።

ስለ ጨዋታው

በዛሬው ጨዋታ ቡድናችን ከሌላው ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ጥሩ ተንቀሳቅሷል። በርካታ የሚባሉ የግብ እድሎችንም ፈጥሯል። ነገር ግን ከጊዜ ወደጊዜ እየጎላ የመጣው የአጨራረስ ችግር ታይቷል። የተጫዋቾቻችን ለጎል መጓጓት ያገኘናቸውን አጋጣሚዎችን እንዳንጠቀም አድርጎናል። ቢሆንም ግን በተጫዋቾች የ90 ደቂቃ እንቅስቃሴ ደስተኛ ነኝ። ከዚህ በተረፈ ተጋጣሚያችን ምን እንደሚመስል አይተንበታል። በመልሱ ጨዋታ በተለይ በአጨራረስ ላይ ያሉብንን ክፍተቶች አርመን ውጤቱን ቀልብሰን ለመምጣት እንሞክራለን።

ስለ መልሱ ጨዋታ

ያው ቡድኑን አይተነዋል። እዚህም ቢሆን ብልጫ አልተወሰደብንም፤ ብልጫ ወስደናል። ብልጫውን ወደ ውጤት መቀየር ላይ እንሰራለን። እድሉ የሁለታችን ቢሆንም ቡድኑን እዚህ ማየታችን ጥቅሙ ለኛ ነው።

ስለ ደጋፊዎች

ሁሌም የምናገረው ነገር ነው፤ የባህር ዳር እና አካባቢው ህዝብ 90 ደቂቃ ነው ያላሰለሰ ድጋፍ የሰጠን። ለዚህ ደግሞ በተጫዋቾቼ ስም አመሰግናለሁ ።


© ሶከር ኢትዮጵያ