ኢትዮጵያ ቡና ከወራት በፊት ቡድኑን በአሰልጣኝነት እንዲረከብ ከስምምነት ከደረሰው ካሳዬ አራጌ ጋር ዛሬ በተዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋዊ የፊርማ ሥነ -ስርዓት አከናውኗል።
በኢንተር ኮንቲኔንታል እየተካሄደ በሚገኘው በዚህ የፊርማ ሥነ-ስርዓት ካሳዬ አራጌ፣ የክለቡ ፕሬዝዳነት መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ፣ የደጋፊ ማኅበሩ ፕሬዝዳንት ክፍሌ አማረ እና ሥራ-አስኪያጁ ስንታየሁ በቀለ የተገኙ ሲሆን ለአራት ዓመታት የሚዘልቅ ኮንትራት ተፈራርመዋል። የመጀመርያው ዓመት ያለ ቅድመ ሁኔታ እንደሚሰራ በኮንትራቱ ላይ የተገለፀ ሲሆን በቀጣዮቹ ዓመታት ደግሞ ቡድኑ እስከ 1- 3ኛ ደረጃ የመጨረስ ቅድመ ሁኔታ ተቀምጧል።
የፊርማ ሥነ-ስርዓቱ ከተካሄደ በኋላም ካሳዬ አራጌ በኢትዮጵያ ቡና በተጫዋችነት ይለብሰው የነበረው 15 ቁጥር በዘመኑ በነበረው የማልያ ገፅታ ተሰርቶ ተበርክቶለታል።
ከ1979 እስከ 1994 ድረስ በኢትዮጵያ ቡና የተጫወተውና ለአንድ ዓመት ከግማሽ ክለቡን ያሰለጠነው ካሳዬ የወቅቱ አነጋጋሪ ቡድንን በመስራት የጥሎ ማለፍ ድል ማሳካቱ ይታወሳል። ከኢትዮጵያ ቡና ከለቀቀ በኋላም ተስፋ ለኢትዮጵያ በሚል በተቋቋመ ቡድን ውስጥ ሲሰራ ቆይቶ ብዙም ሳይቆይ ወደ አሜሪካ ከተጓዘ ከረጅም ዓመታት በኋላ ወደ ክለብ ኢትዮጵያ ቡናን በ4 ዓመታት ውል በመረከብ ወደ አሰልጣኝነት ሥራ ተመልሷል።
– ዝርዝሩን ከቆይታ በኋላ ይዘን እንመለሳለን።
© ሶከር ኢትዮጵያ