የኢትዮጵያ ከ13 ዓመት በታች ቡድን እጣ ፈንታ… 

በቅርቡ ወደ ቻይና በማምራት ጨዋታዎች አድርጎ የተመለሰው የኢትዮጵያ ከ13 ዓመት በታች ቡድን ሳይበተን እንዲቀጥል በአንድ ግለሰብ አማካኝነት ድጋፍ እየተደረገለት ሲሆን ፌዴሬሽኑ ቡድኑ እንደማይበተን ቃል ቢገባም ቃሉን እስካሁን መፈፀም አልቻለም የሚል ቅሬታ ቀርቦበታል። ፌዴሬሽኑ በአንፃሩ በጉዳዩ ዙርያ የገባው ቃል እንደሌለ ገልጿል።

ከወር በፊት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የኢትዮጵያ ከ13 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በማቋቋም ለቻይና-አፍሪካ ወዳጅነት ውድድር ወደ ቻይና መላኩ ይታወሳል። 22 ተጫዋቾችን እና የፌዴሬሽኑ ተወካይ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻውን ጨምሮ 28 ጠቅላላ የልዑክ አባላትን በመያዝ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ናይጄርያ፣ ታንዛንያ እና ኬንያ ጋር በቻይና ሉዲ ከተማ ተገኝተው ጨዋታዎችን ማድረግ ችለው ነበር፡፡

ቡድኑ ወደ ሀገር ከመመለሱ በፊት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ በስፍራው ተገኝተው ቡድኑ እንደማይፈርስ ገልፀው የእያንዳንዱን ተጫዋች ስም ዝርዝር እና አጠቃላይ መረጃ በመውሰድ ወደ ኢትዮጵያ ቢመጡም በቃላቸው ሊገኙ እንዳልቻሉ ቡድኑን ወደ ቻይና ይዘው የተጓዙት አሰልጣኝ ኤርሚያስ ዱባለ ቅሬታቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ እንደ አሰልጣኙ ገለፃ ለሀገሪቱ የእግር ኳስ እድገት መሠረት የሆኑት እኚህ ታዳጊዎች ቃል የተገባላቸው በርካታ ነገሮች ቢኖርም ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ግን የተመለከታቸው አካል እንደሌለ ተናግረዋል። በቡድኑ ውስጥ ያሉ ታዳጊ ተጫዋቾች ወላጆች በበኩላቸው ፌዴሬሽኑ የገባላቸውን ቃል ተፈፃሚ እንዲያደርግ በቃል እና በፅሁፍ በተደጋጋሚ ቢሮ ድረስ ተጉዘው እንደጠየቁና ምላሽ ሊሰጣቸው እንዳልቻለ በመግለፅ ሁኔታው ታዳጊዎቹ የተነሳሽነት መንፈስን እንዲያጡ ማድረጉን ነግረውናል፡፡

አቶ ኢሳይያስ ጂራ በጉዳዩ ዙርያ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ቡድኑን ይዞ ለመቀጠል ቃል እንዳልገቡ ገልፀው የፌዴሬሽኑ እቅድም ይህ እንዳልሆነ ተናግረዋል። ” እኔ ቃል አልገባሁም፤ ፌዴሬሽኑም እንዲህ ዓይነት ፕሮግራም የለውም። እኔ ያልኩት ምንድነው የምትፈልጉት ብዬ ስጠይቃቸው እነሱ ደግሞ አንድ ላይ ተይዘው በዛ መልክ ይቀጥሉ አሉ። እኔ ደግሞ ድጋፍን ከፈለጉ ብቻ ለመርዳት ዝግጁ እንደሆንኩ ነግሬያቸዋለሁ። የሚገርመው በ75 ዓመት የፌዴሬሽኑ ታሪክ እንዲህ ዓይነት የታዳጊ ቡድን ተገንብቶ አያውቅም፡፡ ያ ጥሩ ሆኖ ሳለ ዓለም ያሉ ፌዴሬሽኖች የወጣቶች ልማት ላይ እንዲህ አይደለም የሚሰሩት። ሀያ አምስት ልጅ በአስራ ሦስት ዓመት ዕድሜ ከያዝክ በሁሉም የዕድሜ ገደብም የግድ መያዝ አለብህ። ስለዚህ እኔ ያልኩት ይህ ስለሚከብድ እናንተ መያዝ ከቻላችሁ ያዙ፤ ከዛ በኋላ እኛ ቁሳቁሶችን እንረዳለን፤ ማድረግ የምንችለው ይሄ ነው ብያለሁ፡፡ በሌሎች ዓለማት በወጣቶች ልማት ላይ ሲሰራ በየደረጃው ክለቦች በላይሰንሲንግ ሲስተም ራሳቸውን አደራጅተው የሚሰሩት ተግባር ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ለክለቦች አስገዳጅ ህግን በማውጣት እዚህ የዕድሜ ቦታ ላይ እንዲሰሩ በማድረግ እና እኛ ደግሞ እንደ ብሔራዊ ፌዴሬሽን በቁሳቁስ በመደገፍ ከጎን እንቆማለን። ከዚህ በፊትም ወጣቶች ላይ ለሚሰሩት ድጋፍን አድርገናል። በዚህ መንገድ ብቻ ወደፊትም እንቀጥላለን። ክለቦች ግን በዚህ ላይ ትኩረት የማድረጉ ተግባር የነሱ ነው፡፡” ብለዋል።

አሰልጣኝ ኤርሚያስም እንደ አቶ ኢሳይያስ ጂራ ሁሉ ክለቦች ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልፀው አሁን ባለው ሁኔታ ግን መስራት እእደሚገባ ይናገራሉ። ” እኛ ፍላጎታችን ክለቦች ከ13 ዓመት በታች እንዲያቋቁሙ ነው። አንደኛ ለሀገርም ይጠቅማል፤ ሲቀጥል ለክለቦቹም ብዙ ጥቅሞች አሏቸው። ይህ አንንዲደረግ ማድረግ የፌዴሬሽኑ ተግባር ሆኖ ሳለ ክለቦች ግን የበለጠ የመስራት ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ፌድሬሽኑን ስንጠይቃቸው ምንም የሰጡን ምላሽ የለም። ባለን ነገር ላይ በመስራት ጥሩ ልጆችን ማውጣት አለብን። ”

በዚህ ሁኔታ ላይ ቡድኑን ከመበተን ይልቅ በጋራ ልምምድ እየሰሩ እና ጨዋታዎች እያከናወኑ እንዲቆዩ በማሰብ አቶ ሁሴን አህመድ የተባሉ ግለሰብ ቡድኑን በመረከብ እያንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ በቡድኑ በአጥቂ ስፍራ የሚጫወተው ረመዳን ሁሴን አባት የሆኑት አቶ ሁሴን የልጃቸውን ተስፋ በመመልከት እና ወደ ቻይና የተጓዘውን የቡድኑን ጠቅላላ አባላት እንዳይበተኑ በማሰብ በራሱ አሰልጣኝ ኤርሚያስ መሪነት በጃንሜዳ በሳምንት ሁለት ጊዜ ልምምድ እየሰራ እንዲቀጥል ሁኔታዎችን ያመቻቹ ሲሆን ይህ ቡድን እንዳይፈርስ እና ታዳጊዎቹ ሳይበተኑ በጥሩ አቋም እንዲዘልቁ ባላቸው ፍላጎት ምክንያት ይህን እንዳደረጉ ገልፀዋል።

እንደ ትራንስፖርት ቁሳቁስ እና ምግቦችን ከግለሰቡ እያገኘ የሚገኘው ይህ ቡድን ከሌሎች በኢትዮጵያ ካሉ ታዳጊ የማሰልጠኛ ተቋማት ጋር የወዳጅነት ጨዋታ በማከናወን ላይ የሚገኝ ሲሆን በተጠናከረ መልኩ ቡድኑን ለማስቀጠል ሁሉም ከነኚህ ተስፈኞች ጎን እንዲቆም የቡድኑ አሰልጣኝ ጥሪን አስተላልፈዋል፡፡

አሰልጣኝ ኤርሚያስ ቡድኑን እየደገፉ የሚገኙት አቶ ሁሴን የሚረከብ አካል እስኪመጣ ድጋፍ እያደረጉ እንደሚቆዩ ገልጿል። ” አቶ ሁሴን በየቦታው በራሱ ወጪ እየወሰደ የወዳጅነት ጨዋታን በማመቻቸት የምግብ፣ የመታጠብያ፣ የመኝታ አገልግሎት እንድናገኝ ያደርግልናል። አዲስ አበባ ስንሆን ደግሞ በሜዳ ላይ እየመጣ ያበረታታናል። ምንም የተለየ ቃል የገባልን ነገር የለም፤ ግን ከጎናችን ሆኖ ድጋፍ እስከሚችለው እንደሚያደርግ ነግሮናል፡፡ የሱ አላማ አንድ ላይ አቆይቶ የተሻለ ፍላጎት ላለው አካል ማስተላለፍ ነው፡፡ ”


© ሶከር ኢትዮጵያ