ቅዱስ ጊዮርጊስ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች አስፈረመ

ፈረሰኞቹ አይቮሪኮስታዊው ዛቦ ቴጉይ ዳኒን ለአንድ ዓመት ወደ ቡድናቸው መቀላቀል ችለዋል፡፡

አይቮሪኮስታዊው የ27 ዓመት አጥቂ ከወራት በፊት ማንዚኒ የተሰኘው የኢስዋቲኒውን ክለብ ለቆ የጋናው አሳንቲ ኮቶኮን በሶሦት ዓመት ውል መቀላቀል ቢችልም ለጊዜው ባልታወቀ ምክንያት ከክለቡ ጋር ተለያይቶ ወደ ኢትዮጵያ ማምራት ችሏል፡፡

ተጫዋቹ በጋናው አሻንቴ ኮቶኮ በነበረው የወራት ቆይታም የጋናውን የኤምቲኤን ኤፍኤ ካፕን ማንሳት ሲችል በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የምድብ ጨዋታዎች ላይ መጫወት ችሏል።

ተጫዋቹ በተጨማሪም በቻይናው ውሀን ዛልና በኳታሩ አልሜሳሚር ስለመጫወቱ የክለቡ ይፋዊ የፌስቡክ ገፅ ላይ ተገልጿል፡፡

ምንም እንኳን ላለፉት ዓመታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከውጪ የሚያስመጣቸው አጥቂዎች ስኬታማ መሆን ሲቸገሩ ቢስተዋልም በርከት ያሉ ጥራት ያላቸው የሀገር ውስጥ የአጥቂ መስመር ተሰላፊ ተጫዋቾችን ለያዘው የቅዱስ ጊዮርጊስ አስፈሪ የፊት መስመር የዛቦ ዝውውር ተጨማሪ አማራጭ ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል። ፡፡

በሰርቢያዊው አሰልጣኝ ሰርጂዬ እየተመሩ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን እያደረጉ የሚገኙት ፈረሰኞቹ ዛቦ የመጀመሪያ የውጭ ዜጋ ፈራሚያቸው ሆኗል። በአሁኑ ወቅት በክለቡ ከሚገኙት ግብጠባቂው ፓትሪክ ማታሲና ተከላካዩ ኤድዊን ፍሪምፖንግ በመቀጠልም የክለቡ ሦስተኛ የውጭ ዜጋ ተጫዋቾች ይሆናል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ