ኢትዮጵያ ቡና ዛሬ ከሰዓት በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ከአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ጋር በይፋ የቅጥር ስምምነት ተፈራርሟል።
ለሁለት ሰዓታት በቆየው ጋዜጣዊ መግለጫ የክለቡ ፕሬዝዳንት መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ፣ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ስንታየሁ በቀለ ፣ የክለቡ ደጋፊዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ ክፍሌ አማረ እና አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ተገኝተው ማብራሪያ ሰጥተዋል። በቦታው በዋናነት ክለቡ ከአሰልጣኙ ጋር ይፋዊ ስምምነት የተፈፀመ ሲሆን ስለ አሰልጣኙ እና ከክለቡ ጋር የተያያዙ ወቅታዊ ጉዳዩች ገለፃ ተደርጎባቸዋል።
መርሐ ግብሩን በይፋ የጀመሩት የክለቡ የቦርድ ፕሬዝዳንት መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ሲሆኑ በንግግራቸው አሰልጣኙ እንዴት ወደ ክለቡ ሊመለስ እንደቻለ ማብራሪያ ሰጥተዋል። “ኢትዮጵያ ቡና ካፈራቸው ምርጥ ተጨዋቾች መካከል ካሳዬ አንዱ ነው። የእግር ኳስ ህይወቱንም ከጨረሰ በኋላ በአሰልጣኝነት ከክለባችን ጋር ቆይታ አድርጎ ወደ ውጪ ሃገር ሄዷል። ክለባችን ደግሞ ላለፉት ዓመታት የውጪ አሰልጣኝ አምጥቶ ሲሰራ ቆይቷል። ነገር ግን ያመጣናቸው አንዳንድ አሰልጣኞች ጥሩ ባለመሆናቸው ወደ ሃገር ውስጥ ለመመለስ ተገደናል። ወደ ሃገራችን ስንመለስ ደግሞ ማን ያሰልጥነን ብለን ብዙ አስበናል። በመጀመሪያ ያደረግነው ነገር የቴክኒክ ኮሚቴ አቋቁመን ኮሚቴው በራሱ መስፈርት አውጥቶ አሰልጣኝ እንዲመርጥ ነው። በዚህም የተቋቋመው የቴክኒክ ኮሚቴ ከአንድም ሁለት ጊዜ ስብሰባ አድርጎ ካሳዬን በአንደኝነት መርጦ ለቦርዱ አሳውቋል። ቦርዱም የኮሚቴውን ውሳኔ አፅድቆ ድርድሮችን ስናደርግ ቆይተናል።” ብለዋል። መቶ አለቃ ጨምረውም መደበኛ ባለሆነ መልኩ ክለቡ ከአሰልጣኙ ጋር ለሁለት ዓመት ድርድር ሲያደርግ እንደቆየ እና ቀደም ብሎ ስምምነት ላይ እንደተደረሰ አስረድተዋል።
ከመቶ አለቃ በመቀጠል የክለቡ የደጋፊዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ ክፍሌ አማረ ደጋፊዎችን በመወከል ለአሰልጣኙ የእንኳን ደህና መጣህ ንግግር አድርጓል። “ካሳዬ በኢትዮጵያ ቡና የ40 ዓመታት ታሪክ ውስጥ ጥሩ ስም አለው። ክለቡን ለአጭር ጊዜ ባሰለጠነበት ወቅትም ደጋፊዎችን ወደ ስታዲየም የሳበ አጨዋወት ተከትሏል። በቅርብ ጊዜያት ግን ደጋፊዎቻችን ‘ቡናን መልሱልን’ የሚል ድምፅ በማሰማት እሱ እንዲመጣ ጥያቄ አቅርቧል። ይህንን ጥያቄያችንን ደግሞ ክለባችን ሰምቶ ደጋፊዎች የሚፈልጉት አሰልጣኝ ወደ ክለባችን እንዲመጣ በመደረጉ እናመሰግናለን። ካሳዬም ከምትኖርበት ሃገር እንኳን ደህና መጣህ።” በማለት አጠር ያለ ንግግሩን ካሰማ በኋላ ደጋፊዎች አሰልጣኙ ክለቡን እስኪገነባ በትህግስት እንዲጠብቁ አሳስቧል።
በቀጣይ የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ስንታየሁ በቀለ እና አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ውል ተፈራርመዋል። ከፊርማ ስነ-ስርዓቱ በመቀጠል የክለቡ ፕሬዝዳንት መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ኢትዮጵያ ቡና በ1970ዎቹ መጨረሻ እና በ1980ዎቹ ሲጠቀምበት የነበረውን መለያ (የአሰልጣኙ ስም የታተመበት) ለካሳዬ በስጦታነት አበርክተዋል።
አሰልጣኝ ካሳዬም ይፋዊ ፊርማውን ካኖረ እና ስጦታውን ከመቶ አለቃ ከተቀበለ በኋላ የተሰማውን ስሜት አጠር አድርጎ በቦታው ለታደሙ የሚዲያ አካላት እና ደጋፊዎች አጋርቷል።”በቅድሚያ በጣም አመሰግናለሁ። ረጅም ጊዜ የተጫወትኩበት እና ለአንድ ዓመት ያሰለጠንኩበት ክለብን በድጋሚ እንዳገለግል ዕድሉ ስለተሰጠኝ አመሰግናለሁ።” በማለት በአጭሩ ሃሳቡን ቋጭቷል።
ረዘም ያለ ደቂቃ የፈጀው ጋዜጣዊ መግለጫው ቀጥሎ ጥያቄዎች ከብዙሃን መገናኛ እንዲሰነዘር እድል አመቻችቷል። ለተሰጡ ጥያቄዎችም የሚመለከታቸው ምላሻቸውን ሰጥተዋል።
መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ
ስለ ስምምነቱ ዝርዝር ይዘት
” ካሳዬን ያስፈረምነው ለአራት ዓመታት ነው። በዚህ አራት ዓመታት ግን ሊፈጠሩ የሚችሉ ጉዳዮችን በስምምነታችን አካተናል። ከዚህ ቀደም አሰልጣኝ ስንቀጥር በስምምነታችን ቡድኑ አራት ተከታታይ ጨዋታ ከተሸነፈ ኮንትራት እናቋርጣለን። ይህ ጉዳይ ግን በመጀመሪያው ዓመት ካሳዬ ላይ እንደዚህ አይነት ገደብ አላደረግንም። ከሁለተኛ ዓመት ጀምሮ ግን ቡድኑ ግዴታ ከ1-3ኛ መውጣት አለበት። ይህ ካልሆነ ግን ኮንትራት ለማቋረጥ እንገደዳለን። ከዚህ በተጨማሪ በስምምነታችን መሰረት አሰልጣኙ የታዳጊ ቡድኖቻችንን እየተከታተለ የስልጠና ፕሮግራም እንዲያወጣ ተነጋግረናል። ይህ ብቻ ሳይሆን ክለባችን ከአዲስ አበባ ውጪ የጀመራቸውን ፕሮጀክቶች (የአስኮ እና ሃዋሳ) እንዲከታተል ነግረነዋል።
“የደሞዝ ጉዳይ በተመለከተ መጠኑን ባንናገርም ያለውን ማስረዳት እንችላለን። የአሰልጣኙ ቤተሰቦች ውጪ ሃገር ስለሚኖሩ የሚያገኘውን ደሞዝ ወደ ውጪ መላክ አለበት። ነገር ግን የዶላር ዋጋ ሊጨምር ወይ ሊቀንስ ስለሚችል ከነሃሴ 1 ጀምሮ ያለውን የዶላር ምንዛሬ ታሳቢ ያደረገ አከፋፈል እንደምንፈፅም ከስምምነት ላይ ደርሰናል። ከዚህ በተጨማሪ ከአሁን ጀምሮ የውጪ ተጨዋች ቡድናችን እንደማያስፈርም እና አሰልጣኙ ከወጣት ቡድኖቻችን ብሎም ከከፍተኛ ሊግ እና ብሄራዊ ሊግ ተጨዋቾችን እንዲመለምል ተነጋግረናል። ስለዚህ ከአሁን ጀምሮ ያለ ውጪ ተጨዋች ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ ደግሞ ስም በሌላቸው እና ተስጥኦ ባላቸው ተጨዋቾች ቡድኑ እንዲገነባ ተነጋግረን ተማምነናል።”
ክለቡ ስለሚወዳደርበት ሊግ…
” ከአዲስ አበባ ክለቦች ጋር ያደረግነውን ስምምነት በተመለከተ ምንም ይፋ ያደረግነው ነገር የለም። ወደዚህ ውሳኔ የመጣነው በተለያዩ ችግሮች ነው፤ በተለይ በፀጥታ ችግር። በደጋፊዎቻችን ላይ ብቻ ሳይሆን በቡድናችን ተጨዋቾች ላይም ይህ ነገር ተፅዕኖ እያደረገ ነው። በተለይ በክልሎች ላይ የሚደረገው ጨዋታ ወደ ጎጥነት ተቀይሯል። ይህ ደግሞ አገደኛ ነው። ከዚህ በተጨማሪ የደላላ ጉዳይ ነው እያሳሰበን የመጣው። ዳኞችን የሚያዙ ጉልበተኛ ደላሎች በእግር ኳሳችን እየተፈጠሩ ነው። በንፁህ መልኩ ነው ወይ እየተወዳደርን ያለነው ብለን ብንጠይቅ መልሱ አደለም ነው። ስለዚህ ይህንን ውሳኔ መወሰን ነበረብን። ከምንም በላይ ደግሞ መታሰብ ያለበት የ2012 የሃገሪቱ ሁኔታ ነው። እንደሚታወቀው በቀጣይ ዓመት ሃገሪቱ ምርጫ ታከናውናለች። ስለዚህ ማንም የምርጫ ተወዳዳሪ ዘሎ ወደ እኛ እንዲገባ አንፈልግም። ለዚህ ነው ይህንን ውሳኔ የወሰነው። በአሁኑ ሰዓት ደግሞ ለመንግስት ጥያቄ አቅርበን ምላሽ እየጠበቅን ነው። መንግስት ችግር የለም እኔ ዋስትና እሰጣችኋለው ካለን ወደ ቀደመው እንገባለን። ነገር ግን ተዟዙሮ መጫወት አለ ቢባል እንደ ከዚህ ቀደሙ በየጫካው እየዞርን አንጫወትም። ለፊፋ አሳውቀን ሜዳው ለጨዋታ አመቺ ነው ስንባል ብቻ ነው ሄደን የምንጫወተው። ”
ስለ ተጨዋቾች የ50 ሺ ብር ጣርያ ጉዳይ
” ይህ ጉዳይ በጣም አደገኛ ነው። በጉዳዩ ስብሰባ ሲጠራ እኛ አልሄድንም። መኼድ ከነበረበት መንገድ በተቃራኒ ነው የተኬደው። በእኛ እምነት ውሳኔው (የተጨዋቾች የደሞዝ ጉዳይ) መወሰን የነበረበት በክለቦቹ በራሳቸው ነው። ይህ ማለት ክለቦቹ የራሳቸውን ተጨዋች ጠርተው ማነጋገር እና ያለውን ነገር ማስረዳት ነበረባቸው። ነገር ግን ይህ ሳይሆን በአቋራጭ ተኪዷል። እኛ አሁን በፌደሬሽኑ ስር ስላለን በደንቡ መሰረት እያስፈረምን ነው። በጊዜያዊነት ቢሆንም ወደ ፊት ግን ጉዳዩን የማንስማማበት በመሆኑ አሰራራችንን እንቀይራለን።”
አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ
የሚፈልጋቸውን ተጨዋቾችን ስለማግኘቱ እና ውል ስላላቸው ተጫዋቾች ጉዳይ
“እኔ ሊጉ ከተጠናቀቀ በኋላ ስለምመጣ መመረጥ የነበረባቸው ተጨዋቾች መመረጥ ነበረባቸው። እዛ ሆኜ በጠቆምኳቸው ሰዎች አማካኝነት ምርጫ ተደርጓል። ስለዚህ የተመለመሉት እና የፈረሙት ተጨዋቾች በእኔ ይሁኝታ በተሰጣቸው ግለሰቦች አማካኝነት ስለሆነ ሃላፊነቱን እኔ እወስዳለሁ። ውል ያላቸውን ተጨዋቾች በተመለከተ በቶሎ ውሳኔዎች እንዲወሰኑ እንጥራለን። ተጨዋቾቹ እኛ ካልፈለግናቸው ወደ ሌላ ክለብ መሄድ ስላለባቸው በቶሎ የዝግጅት ጊዜ ላይ ተመልክተናቸው ውሳኔ እንወስናለን። ነገር ግን ተጨዋቾቹ በማይጎዱበት መልኩ ለመጓዝ እንሞክራለን።”
ስለ አሰልጣኝ ቡድን አባላት
“የኔን ሃሳብ የሚደግፉ አሰልጣኞች እንዲቀጥሉ እፈልጋለሁ። በወጣቶች ቡድን ላይ የሚሰሩ አሰልጣኞችን ደግሞ ገና አግኝቼ ማውራት አለብኝ። ከአሰልጣኞቹ ጋር መነጋገር ያሉብን ነገሮች ስላሉ ከተነጋገርን በኋላ ውሳኔ እንወስናለን።”
ስለ ጨዋታ አስተሳሰብ ለውጥ
“ብዙ ለውጥ የለም። እግር ኳስ የሚያድግ ነገር ስለሆነ ያደጉ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ዋናው ነገር ግን በፊትም አሁንም ያሉ ተጨዋቾች ተመሳሳይ ስለሆኑ መሰረታዊ ለውጥ አይኖርም። ምናልባት ግን የተጫዋቾች አቅምን አስተውለን አማራጮችን ልንመለከት እንችላለን። ይህ የሚሆነው ግን የተጨዋቾቻችንን አቅም አይተን ነው።”
በስተመጨረሻም አሰልጣኙ ከአንድ የክለቡ አንጋፋ ደጋፊ ‘ውጤት አመጣለሁ ብለህ ቃል ግባልን’ ተብሎ ለተነሳ ጥያቄ አጭር ምላሽ ሰቷል።” መጫወት አለብን ባልነው ነገር ውስጥ ውጤት ይመጣል።”
*በመርሃ-ግብሩ መሐል ክለቡ በ1970ዎቹ እና 1980ዎቹ ሲጠቀምበት የነበረውን መለያ ለደጋፊዎች በሽያጭ መልክ ማቅረቡ ተገልጿል።
© ሶከር ኢትዮጵያ