ከበርካታ ዓመታት በኃላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ባለፈው ዓመት በመቐለ 70 እንደርታ እና ስሑል ሽረ ቆይታ ያደረገው አርዓዶም ገብረህይወት ከእግር ኳስ ራሱን ማግለሉን አስታውቋል።
በ2003 ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ያነሳው አጥቂው በወጣትነት ዕድሜው ብዙ ተስፋ ተጥሎበት በእግር ኳስ ህይወቱ መጀመርያ የብዙዎች ትኩረት ቢስብም በጉዳት ምክንያት እንደተጠበቀው መድመቅ አልቻለም።
ለትራንስ ኢትዮጵያ፣ ንግድ ባንክ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ አየር ኃይል፣ መቐለ 70 እንደርታ፣ ስሑል ሽረና የኢትዮጵያ ወጣት ብሄራዊ ቡድን መጫወት የቻለው አጥቂው ባለፉት ዓመታት በእንግሊዝ ከእግር ኳስ በተያያዘ የስፖርት ሳይንስ ትምህርት ማጥናቱ ሲታወስ ትምህርቱን ዳር ለማድረስ ነው ተመልሶ ወደ እንግሊዝ የሚያመራው።
ከወራት በፊት ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ የነበረው አጥቂው በተማረበት ሙያ የሃገሩን እግር ኳስ ለመቀየር እንደሚሰራ መግለፁ ሲታወስ በአንድ ዓመት የኢትዮጵያ ቆይታው ባለው የእግር ኳስ አጠቃላይ አሰራር ደስተኛ አለመሆኑን ገልጿል።
ተጫዋቹ ከኢትዮጵያ ውጭ በእንግሊዙ ሰሜን ሊግ የመጀመርያ ዲቪዝዮን ለሚጫወተው ፋየር ዩናይትድ መጫወቱ ይታወሳል።
© ሶከር ኢትዮጵያ