የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ የሚደረግበት ጊዜ ታውቋል

የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ፌደሬሽን በየዓመቱ የሚያዘጋጀው የሲቲ ካፕ ውድድር ዘንድሮ ለ14ኛ ጊዜ እንደሚከናወን ይጠበቃል። ፌደሬሽኑ ውድድሩን ለማከናወን ያሰበበት ጊዜም ታውቋል።

በየዓመቱ የሚከናወነው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ (ሲቲ ካፕ) ውድድር ዘንድሮ ከመስከረም 23 – ጥቅምት 9 እንደሚደረግ የፌደሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ ዮናስ ሃጎስ (ጋዜጠኛ) ለሶከር ኢትዮጵያ አስታውቀዋል። ከቀደሙት ዓመታት በተለየ ውድድሩን ለማድመቅ ፌዴሬሽኑ እንዳሰበ የገለፁት አቶ ዮናስ በውድድሩ የሚሳተፉ ስምንቱ ክለቦች ሙሉ ለሙሉ ተለይተው እንዳልታወቁ ገልፀዋል።

ምንም እንኳን ሁሉም ተሳታፊ ክለቦች ባይታወቁም ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ኢትዮጵያ መድን እና መከላከያ በውድድሩ እንደሚሳተፉ መታወቁ ተገልጿል። ከአምስቱ የከተማዋ ክለቦች በተጨማሪም በዚህ ዓመት ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ያደጉት ወልቂጤ ከተማ እና ሰበታ ከተማ በውድድሩ ለመሳተፍ ፍላጎት ማሳየታቸውን አቶ ዮናስ ተናግረዋል።

በመጨረሻም ፌደሬሽኑ ከማልታው ቢርኪርካራ ክለብ ጋር ንግግር ላይ መሆኑ የተናገሩት አቶ ዮናስ ምናልባት ድርድሮች በጥሩ መልኩ ከተጠናቀቁ ክለቡ በተጋባዥነት በውድድሩ ላይ ሊሳተፍ እንደሚችል ገልፀዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ