በ2022 የዓለም ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ ላይ ተሳታፊ የሆነችው ኢትዮጵያ ከቀናት በፊት በባህር ዳር ሌሶቶን አስተናግዳ 0-0 በሆነ ውጤት መፈፀሟ የሚታወስ ሲሆን ዛሬ ደግሞ ማሴሮ ላይ በመልሱ ጨዋታ 1-1 በሆነ ውጤት በመለያየቷ ከሜዳ ውጪ ጎል ህግ መሠረት ወደ ምድብ ማጣርያው መግባቷን አረጋግጣለች፡፡
ከባህርዳሩ ጨዋታ የሦስት ተጫዋቾችን ቅያሪ በማድረግ ወደ ሜዳ የገቡት አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ረመዳን ናስር፣ መጂብ ቃሲም እና ዑመድ ኡኩሪን ወደ ተጠባባቂ በማውረድ ደስታ ደሙ፣ ሀይደር ሸረፋ እና መስፍን ታፈሰን ወደ መጀመርያ አሰላለፍ አካተዋል። ደስታ በቀኝ በኩል በመሰለፉም አህመድ ረሺድ ወደ ግራ መስመር ተከላካይነት ሲሸጋሸግ፤ አማካዩ ቢኒያም በላይ ደግሞ በመስመር አጥቂነት ጨዋታውን ጀምሯል። በታቦ ሴኖንግ የሚመሩት ሌሶቶዎች በአንፃሩ የሁለት ተጫዋች ለውጥን በማድረግ ሴህሎሆኖሎ እና ሶአሬሎ አርፈው ምትሎሜሎ ሞኳንዚ እና ንካይ ሌሮቶሊ ወደ አሰላለፉ ተካተዋል።
ቅብብል ላይ ካተኮረ እንቅስቃሴ በቀር ተጠቃሽ የግብ አጋጣሚን መመልከት ባልቻልንበት የመጀመሪያው አጋማሽ ሌሶቶዎች ረጃጅም ኳስ ላይ ትኩረት ቢያደርጉም ለኢትዮጵያ የተከላካይ ክፍል ግን እምብዛም ከባዶች አልነበሩም፡፡ ኳስ መስርቶ ከመጫወት ጀምሮ በአንፃራዊነት ጥሩ የነበሩት ዋሊያዎቹ ደግሞ ወደ ማጥቃት ወረዳ ሲደርሱ በቀላሉ ወደ ጎል እድልነት መቀየር ሳይችሉ መቅረታቸው በዚህኛው አጋማሽ ጎልተው ሊታዩ ችለዋል፡፡
አማኑኤል እና ቢኒያም በፈጠሩት አጋጣሚ የሌሶቶን የተከላካይ ክፍል ለማስከፈት ከጅማሮው ጥረት ያደረጉት ዋልያዎቹ የነበሩ ሲሆኑ 25ኛው ደቂቃ ላይ በቅብብል ስህተት እና አስቻለው ታመነ በሰራው ጥፋት ኸሎምፎ ካላኬ ያደረገው ኢላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ሌሶቶዎችን በሙከራ ቀዳሚ አድርጓቸዋል፡፡ 28ኛው ደቂቃ ላይ በተደጋጋሚ በቀኝ በኩል አስከፍቶ ለመግባት የግል ጥረትን ሲያደርግ የነበረው ቢኒያም በላይ በዚሁ ሂደት ያመጣትን ኳስ ለመስፍን ታፈሰ ሰጥቶት ለጥቂት በሌሶቶ ተከላካይ ተነጥቋል። አማኑኤል ገ/ሚካኤል ወደ ሳጥን እየገፋ ገብቶ የመታው እና ኢላማዋን ሳትጠብቅ የወጣችሁ በኢትዮጵያ በኩል፤ 43ኛው ደቂቃ በግራ መስመር ከጋቶች ፓኖም እግር ስር ኳስን የነጠቀው ሴፖ ሴቱሩማንግ ወደ ጎል መትቶ ያሬድ ባዬ እንደምንም ያወጣበት ደግሞ በሌሶቶ በኩል ሌሎች የሚጠቀሱ ሙከራዎች ናቸው፡፡
የተሻለ የጎል ሙከራ በታየበት እና ጎሎችም በተቆጠሩበት ሁለተኛው አጋማሽ ኢትዮጵያ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት ሳትቸገር የተመለከትናት ሲሆን ሌሶቶዎች ደግሞ ከቆሙ ኳሶች አስጨናቂ ሙከራዎችን አድርገዋል። ሀይደር ሸረፋ ባደረጋት መልካም አጋጣሚ የሁለተኛ አጋማሽ ቀዳሚ ሙከራን ማድረግ የቻሉት ዋልያዎቹ ብዙም ሳይቆዩ ጎል አስቆጥረዋል። 50ኛው ደቂቃ ላይ ቢንያም በላይ ቀኝ መስመር በኩል ወደ ሳጥን ገብቶ ያሻገረውን ኳስ ንካይ ኔትሮሊ ለማውጣት ሲል በራሱ ላይ አስቆጥሮ ኢትዮጵያን ቀዳሚ አድርጓል፡፡
ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በተደጋጋሚ ወደ ኢትዮጵያ የግብ ክልል የደረሱት ሌሶቶቸች አቻ ለመሆን ብዙም ደቂቃ አልፈጀባቸውም። ከማዕዘን ምት በተሻገረ አጋጣሚ ጃንግ ታባንትሶ በግንባር ገጭቶ ለጥቂት በተከላካዮች ተንክታ ከወጣች ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ 55ኛው ደቂቃ ላይ የተገኘችውን የቅጣት ምት ሴፖ ሴትሩማንግ በቀጥታ መትቶ መስፍን ታፈሰን ጨርፋ ከመረብ አርፋ 1-1 መሆን ችለዋል፡፡ ግቧ በመስፍን ትጨረፍ እንጂ በሴፖ ስም ተመዝግባለች፡፡
አቻ መሆናቸውን የመተለከቱት አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ በመከላከሉ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ያደረጉ ሲሆን አማካዩ ሽመልስ በቀለን አስወጥተው ተከላካዩ አንተነህ ተስፋዬን በማስገባቶ የኋላ ክፍላቸውን ለማጠናከር ጥረት አድርገዋል። ከጎሉ በኋላ ትጋታቸውን የጨመሩት ሌሶቶዎች በሶአሬሎ የርቀት ሙከራ እና በሁለት የቆሙ ኳሶች ግብ ሊያስቆጥሩ ተቃርበው ነበር። ተቀይሮ የገባው ንኮቶ ማባሲ በ74ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን በግንባር ገጭቶ ጀማል ጣሰው እንደምንም ያወጣው እና ከአንድ ደቂቃ በኋላ በተመሳሳይ ከማዕዘን የተሻማውን በድጋሚ በግምባሩ ገጭቶ የጎሉ አግዳሚ የመለሰው እንዲሁም ጨዋታው ሊጠናቀቅ 5 ደቂቃዎች እየቀሩት ከሜዳው አጋማሽ በስተቀኝ የተገኘውን የቅጣት ምት ሳኔሎ በረጅሙ ወደ ግብ ክልል ልኮ ንኮቶ ማባሲ በግንባር ገጭቶ በድጋሚ የጎሉ ብረት የመለሰበት ሌሶቶዎች የማሸነፍያ ግባቸውን ለማስቆጠር በእጅጉ የቀረቡባቸው ነበሩ።
በመጨረሻ ደቂቃዎች ሌሶቶዎች ብልጫን ያሳዩ ቢሆንም አፈግፍገው በመጫወት ውጤቱን ለማስጠበቅ የጣሩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ተሳክቶላቸው ጨዋታው 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። ይህን ተከትሎም ከሜዳ ውጪ ጎል ህግ መሠረት ኢትዮጵያ ወደ ምድብ ማጣርያው ዙር ገብታለች፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ