ኢትዮጵያን ፕሮፌሽናል ፉትቦለርስ አሶሴሽን ዛሬ አመሻሽ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ባከናወነው ስብሰባ በተጨዋቾች ደሞዝ ገደብ ላይ ስለተላለፈው ውሳኔ ተቃውሞውን ገልፆ የራሱን ውሳኔ አስተላልፏል።
ይጀመርበታል ተብሎ ከተነገረው አንድ ሰዓት ዘግይቶ የተጀመረው ስብሰባ ጥቂት ተጨዋቾች(10) የተገኙበት ነበረ። በቦታው ስብሰባውን በመምራት የማኀበሩ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ግርማ፣ የማኀበሩ ፀሃፊ አቶ ሳምሶንን ጨምሮ ሶስት የስራ አስፈፃሚ አባላት ተገኝተዋል።
በመጀመሪያ ሃሳባቸውን በመግለፅ ስብሰባውን የጀመሩት አቶ ግርማ በተደጋጋሚ ደብዳቤዎችን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ልከው ምላሽ እንዳልተሰጣቸው እና ስብሰባውን የጠሩበትን ምክንያት አስረድተዋል። “ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ተገናኝተን ስብሰባዎችን አድርገን መግለጫዎችን አውጥተን ነበር። ነገር ግን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ምንም መልስ አልሰጠንም። ስለዚህ በቀጣይ ስለምንወስነው ውሳኔ ለመወያየት ይህንን ስብሰባ ልንጠራ ተገደናል። እኛ እንደ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የራሱን መታዳደሪያ ደንብ፣ የፊፋን መተዳደሪያ ደንብ እና የኢትዮጵያን የፍትሃቤር ህግን የጣሰ ድርጊት አድርጓል ብለን እናምናለን።” በማለት በነሱ በኩል ፌደሬሽኑ ጥሷቸዋል ያሏዋቸውን ነጥቦች መዘርዘር ቀጥለዋል።
አቶ ግርማ በገለፃቸው ከፌደሬሽኑ ጋር ውሳኔው እንዲወሰን ያደረገው አካል (የስፖርት ኮሚሽን) በፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደምብ መሰረት የፌደሬሽኑ አባል አለመሆኑ፣ በፌደሬሽኑ ደምቡ ላይ የተገለፀው የአባላት (ተጨዋቾች) መብት አለመጠበቁ ፣ አንቀፅ 47 ላይ የተደነገገው የስፖርት ግልግል ጉባኤ አለመተግበሩ ጉዳዩን ህጋዊ እንደማያደርጉት አስረድተዋል። አቶ ግርማ በንግግራቸው ማብቂያም እስከ ሐሙስ (መስከረም 01) ድረስ ፌደሬሽኑ መልስ ካልተሰጣቸው ጉዳዩን ወደ ህግ ቦታ (ፍርድ ቤት) እንደሚወስዱት ጠቁመዋል።
በመቀጠል የአሶሴሽኑ ፀሃፊ አቶ ሳምሶን ተጨማሪ ሃሳብ ሰተዋል። “ምክትል ፕሬዝዳንታችን እንደገለፀው ለፌደሬሽኑ ጥያቄያችንን አስገብተን መልስ እየጠበቅን ነው። እኛ አሁንም ከፌደሬሽኑ ጋር ለመስራት ፍቃደኞች ነን። ግን በዚህ ዓይነት መልኩ አይደለም። የፌደሬሽኑ ዋናው ክፍሎች ተጨዋቾች ናቸው። ፌደሬሽኑም የተጨዋቾችን መብት ማስጠበቅ አለበት። ይህንን ሳያደርግ፣ ተጨዋቾች ሳያማክር እና መግለጫ ሳይሰጥ ውሳኔ ማሳለፍ ትክክል አይደለም።” በማለት ሀሳባቸውን ከገለፁ በኋላ በአምስቱ ቀናት (እስከ ሐሙስ) ፌደሬሽኑ እነሱን ለማነጋገር ከፈለግ በራቸው ክፍት እንደሆነ አስረድተዋል።
መድረኩን ሲመሩ ከነበሩት ስራ አስፈፃሚዎች ኤፍሬም ወንድወሰን በመጨረሻ ተጨማሪ ሃሳብ ሰንዝሯል። “ይሄ ማህበር ከተመሰረተ ጀምሮ አላማውን ለማሳካት እኛ የምንችለውን እያደረግን ነው። በዋናነት አላማችን የተጨዋቾችን መብት ማስከበር ነው። ከዚህ ቀደም ተጨዋቾች ላይ ሲደርሱ የነበሩ የተለያዩ የመብት ጥሰቶች ነበሩ። አሁን ግን ከመንግስት የተሰጠን ፍቃድ በመጠቀም የመብት ጥሰቶችን ለመከላከል እንሰራለን። እኛ ፍቃድ ካገኘን በኋላ ግን እኛን ያላማከለ ውሳኔ ተወስኖ የሞራል ጉዳት ደርሶብናል። እንደተባለው በተደጋጋሚ ለፌደሬሽኑ ጥያቄዎችን ብናስገባም ዝም ስለተባልን ካሉን የህግ ሰዎች ጋር ተመካክረን ቀጣይ መንገዳችንን ወስነናል። በዚህም ሁላችንም ወደምንዳኝበት ፍርድቤት ጉዳዩን ይዘን እንሄዳለን።” ብሏል። ኤፍሬም ጨምሮም ተጨዋቾች እና ክለቦች በጉዳዩ ግራ እየተጋቡ መሆኑን አስረድቷል።
ከሶስቱ የአሶስሽኑ ስራ አስፈፃሚዎች ገለፃ በኋላ በቦታው ለተገኙ ጥቂት(10) ተጨዋቾች ሃሳብ እንዲሰጡ ዕድል ተመቻችቶ ነበረ። ነገር ግን በቦታው የተገኙ ተጨዋቾች ሃሳብ ሳይሰጡ በቀጥታ ከብዙሃን መገናኛዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ መሰጠት ተጀምሯል።
አቶ ግርማ
ብዙ አባላት በቦታው ስላልተገኙበት ምክንያት
“ልክ ነው ብዙ አባላቶቻችን አልተገኙም። ያልተገኙበት ምክንያት ደግሞ ብዙ ሊሆን ይችላል። የእኛም ድክመት ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ዛሬ የቡድን አምበሎችን ብቻ ነው የጠራነው። እንደሚታወቀው ደግሞ በሀገራችን ብዙ የክልል ክለቦች አሉ። ስለዚህ እነሱ ካሉበት ቦታ ለመምጣት አልቻሉ ይሆናል። ከምንም በላይ ግን እኛ ገና ጀማሪዎች ስለሆንን እና ተጨዋቾች ስብሰባ ላይ የመገኘት ብዙም ልምዱ ስለሌላቸው ይሆናል ዛሬ ያልተገኙት።”
ስለሚከሱት አካል
“እኛ የምንከሰው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽንን ነው። ከክለቦች ጋር ምንም ችግር የለብንም። ክለቦቻችን ምንም አድርገውናል ብለን አናምንም። ከዚህም ቀደም የተጣላንበም ሆነ ወደ ህግ ቦታ የተዳረስንበት ነገር የለም። እርግጥ እስከ አራት ወር ደሞዝ ያልተከፈላቸው ተጨዋቾች ቢኖሩም ክለቦችን በትዕግስት እየጠበቁ ነው። ስለዚህ እኛ የምንከሰው ኋላ ቀር አሰራር የሚከተለውን እና የራሱን መተዳደሪያ ደምብ አገላብጦ ያላነበበውን ፌደሬሽናችንን ነው።”
ከደሞዝ ገደቡ ጉዳይ በዘለለ አሶሴሽኑ ሊሰራ ስላሰባቸው ስራዎች
“ማኅበራችን ድሮ ነበረ መቋቋም የነበረበት። በዋናነት አላማችን ኢትዮጵያ ውስጥ ፕሮፌሽናሊዝምን ማምጣት ነው። ምክንያቱም በአማተር ሰዎች ነው እግር ኳሳችን እየተመራ ያለው ይህንን ደግሞ መቀየር አለብን። ስለዚህ ዋና አላማችን ይህ ነው። ከዚህ በተጨማሪ የሃገራችንን እግር ኳስ ለማሳደግ የሚጠቅሙ ዓላማዎችን ይዘን ነው የተቋቋምነው።”
ኤፍሬም ዘካሪያስ
ስለ ማኅበሩ አመሰራረት እና በውስጡ ስላሉት የስራ አስፈፃሚ አባላት ህጋዊነት
“ማህበሩን ለመመስረት ረጅም ጊዜ ወስዷል። ከሦስት ዓመት በፊት የተጨዋቾችን ማህበር ለማቋቋም ፈልገው ፍቃድ ለመውሰድ የተንቀሳቀሱ ሰዎች ተከልክለው ነበረ። በዛን ሰዓት እየተጫወቱ ስላልሆነ። አሁን ግን ህጉ እንደ አዲስ ከተከለሰ በኋላ እኛ ሄደን ማህበሩን ተባብረን በህጋዊነት አቋቁመናል። እኛ ማህበራት እና በጎ አድራጎት ኤጀንሲ ሄደን ያለውን መመዘኛ አሟልተን ነው የተቋቋምነው ፤ ስለዚህ ህጋዊ ነን። በፕሬዝዳንትነት እና ምክትል ፕሬዝዳንትነት የተመረጡትም ሰዎች በጠቅላላ ጉባኤው አማካኝነት የተመረጡ ናቸው። ሁሉም ነገር በህጋዊ መንገድ የተደረገ ስለሆነ ምንም ጥያቄ የሚያስነሳ አይሆንም። እኛም እዚህ ቦታ የመጣነው ለሳንቲም ብለን አይደለም። ሙያውን ለማስከበር እንጂ። ስለዚህ ዋናው ነገር የሙያው ክብር ነው።”
© ሶከር ኢትዮጵያ