ለረጅም ዓመታት ወጣቶች ላይ በመስራት የሚታወቀው ተመስገን ዳና አዲሱ የደቡብ ፖሊስ አሰልጣኝ ለመሆን ከስምምነት መድረሱ ሲታወቅ በዚህ ሳምንት በሚሰጥ ጋዜጣዊ መግለጫ በይፋ እንደሚፈራረም ክለቡ ገልጿል።
የከፍተኛ ሊግ ቻምፒዮን በመሆን በአሰልጣኝ ግርማ ታደሰ እየተመራ ወደ 2011 ፕሪምየር ሊግ አድጎ የነበረው ደቡብ ፖሊስ ዓመቱን በዘላለም ሽፈራው ጀምሮ በገብረክርስቶስ ቢራራ መጨረሱ የሚታወስ ነው። ከፕሪምየር ሊጉ የወረደበት መንገድ አግባብ እንዳልሆነ በመግለፅ ራሱን ከፌዴሬሽኑ ውድድር ለማግለል ማሰቡን ገልጾ የነበረው ክለቡ በቅርቡ የአሰልጣኝ ቅጥር ከፈፀመ በኃላ ተጫዋቾችን ወደ ማስፈረሙ እንደሚገባ ለሶከር ኢትዮጵያ እንዳስታወቀ የሚታወስ ሲሆን የወልቂጤ ከተማ ረዳት አሰልጣኝ ለመሆን ቅድመ ስምምነት ፈፅሞ የነበረውን ተመስገን ዳናን ምርጫው አድርጓል። በዚህ ሳምንት በሚሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫም የአሰልጣኙን ቅጥር ይፋ ያደርጋልም ተብሏል፡፡
በሀዋሳ ከተማ ከ17 እና 20 ዓመት በታች ቡድኖች ስኬታማ ጊዜያት ያሳለፈው ተመስገን ዳና የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች አሰልጣኝ ሆኖም መስራት ችሏል። አሰልጣኙ በተለይ ታንዛኒያ ላይ በተካሄደው የሴካፋ ውድድር ኢትዮጵያን እስከ ፍፃሜው በማድረስ ከብዙዎች አድናቆት ተችሮትም ነበር፡፡ በዘንድሮው የውድድር ዓመት የአሰልጣኝ አዲሴ ካሳ ረዳት በመሆን በሀዋሳ ከተማ የሰራው አሰልጣኝ ተመስገን በዓመቱ አጋማሽ ከክለቡ ጋር ከተለያየ በኋላ በወልቂጤ ከተማ የአሰልጣኝ ደግአረግ ረዳት አሰልጣኝ ለመሆን ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም የቢጫ ለባሾቹ አዲሱ አሰልጣኝ ለመሆን ከስምምነት ደርሷል።
የክለቡ ፕሬዝዳንት የነበሩት ኮማንደር ዳንኤል ገዛኸኝን ተክተው ወደ ፕሬዝዳንትነት የመጡት የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ ክለብ ፕሬዝዳንት አቶ ታሪኩ ኡጋሞ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ከሆነ አሰልጣኙ ረዳቶቻቸውን የመሾም ነፃነት የተሰጣቸው ሲሆን በጋዜጣዊ መግለጫውም የክለቡ እቅድ እና ስለ አዲሱ አሰልጣኝ አመራረጥም ገለፃ ይደረጋል ብለዋል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ