በከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ የሚወዳደረው ሀላባ ከተማ አዳዲስ ተጫዋቾች ወደ ቡድኑ መቀላቀል በመጀመር ሦስት ተጫዋቾች አስፈርሟል።
ከደቡብ ፖሊስ የፊት መስመር ተጫዋቹ በኃይሉ ወገኔ ቡድኑን የተቀላቀለ ቀዳሚው ተጫዋች ነው። ከዚህ ቀደም ነገሌ ቦረና አጥቂ የነበረው በኃይሉ ከደቡብ ፖሊስ ጋር ወደ ፕሪምየር ሊግ አድጎ የደድድር ዓመቱን በዛው ሲጫወት ቆይቷል።
በክሪ መሐመድ ሌላው ወደ በርበሬዎቹ ያመራ ተጫዋች ነው። የግራ መስመር ተጫዋቹ በክሪ ከዚህ ቀደም በስሑል ሽረ በመቀጠልም በኢኮስኮ የተጫወተ ሲሆን በ2011 በኢትዮጵያ መድን መጫወት ችሏል።
ሌላው የሀላባ አዲስ ፈራሚ ሐብታሙ ጥላሁን ነው። የአማካይ ስፍራ ተጫዋች የሆነው ሐብታሙ ከዚህ ቀደም በቡና እና ደቡብ ፖሊስ የተጫወተ ሲሆን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ካደገው ሰበታ ከተማ ነው ወደ ሀላባ ያመራው።
በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ ለበርካታ ጊዜ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ ጫፍ ደርሶ እየተመለሰ የሚገኘው ሀላባ ከተማ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ብቅ ለማለት የሚስችለውን አቅም ለመገንባት ጠንክረው እየሰራ እንደሚገኝ የክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ አኖር ሲጌርሳ ለሶከር ኢትዮጵያ የተናገሩ ሲሆን በ2011 ከግማሽ ዓመት የቀጠሩት አሰልጣኝ ካሊድ መሐመድም ወደ ሊጉ የመግባት እቅዳቸውን እንደሚያሳኩላቸው እንደሚተማመኑ ገልፀዋል። ፌዴሬሽኑ ባዘዘው መሰረት የመጫወቻ ሜዳውን ብቁ የማድረግ ስራ እንደተሰራም ጨምረው ተናግረዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ