ቻን 2016፡ ቱኒዚያ ምድብ ሶስትን በበላይነት ጨርሳለች

በሩዋንዳ አዘጋጅነት እየተካሄ ያለው 4ኛው የአፍሪካ ሃገራት ዋንጫ (ቻን) የምድብ ሶስት ጨዋታዎች ዛሬ በስታደ ኡሙጋንዳ እና በስታደ ናያሚራምቦ ተደርጋዋል፡፡ 

አላፊ ሃገራት እስከ የምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ ድረስ አለመታወቃቸው ሁሉንም ሃገራት ሩብ ፍፃሜውን የመቀላቀል ዕድል አስፍቶ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ቱኒዚያ የምድቡ መሪ ሆና ስታጠናቅቅ ጊኒ ባስገራሚ መልኩ ናይጄሪያን ጥላ ሩብ ፍፃሜውን ተቀላቅላለች፡፡

በስታደ ናያሚራምቦ ኒጀርን የገጠመችው የቻን 2011 አሸናፊዋ ቱኒዚያ 5-0 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፋለች፡፡ የካርቴጅ ንስሮቹ ሙሉ የጨዋታ ብልጫ የነበራቸው ሲሆን የሳአድ ቡጉኢር ሁለት ግቦች (በ5ኛው እና 39ኛው ደቂቃ) በመጀመሪያው ግማሽ የተቋጠሩ ነበሩ፡፡ ከዕረፍት መልስ በ74ኛወ ደቂቃ የኒጀሩ የሱፍ ኦማሩ አሊዮ በሁለት ቢጫ ከሜዳ ተወግዷል፡፡ ከአራት ደቂቃዎች በኃላ የኤትዋል ደ ሳህል ተጫዋች የሆነው አህመድ አኪያቺ በ78ኛው ደቂቃ ሶስተኛውን ግብ አስቆጥሮ የኒጀርን የማለፍ ተስፋ አጨልሟል፡፡ ለኤትዋል ደ ሳህል የኮንፌድሬሽን ዋንጫ አሸናፊ መሆን እንዲሁም ለቱኒዚያ በ2015 የአፍሪካ ዋንጫ ሩብ ፍፃሜ መድረስ ቁልፍ ሚና የነበረው አኪያቺ በውድድሩ ያስቆጠራቸውን የግብ መጠን ወደ 4 አሳድጎ ከናይጄሪያው ቺሶማ ቺካታራ ጋር በጣምራ የቻን2016 ኮከብ ግብ አግቢነትን መምራት ጀምሯል፡፡ መሃመድ አሚን ቤን አሞር እና ሃኪም ኢሲፊ ቀሪዎቹን ግቦች አክለው ጨዋታው 5-0 ተጠናቅቋል፡፡ የቱኒዚያ እና የሲኤስ ሴፋክሲያን አምበል የሆነው የግራ ተመላላሹ አሊ ማሎል ሶስት ግብ የሆኑ ኳሶችን በማቀበል ለቱኒዚያ ድል ቁልፈ ፍሚና ተጫውቷል፡፡

በስታደ ኡሙጋንዳ ሰፊ የማለፍ ተስፋን ይዛ ጊኒን የገጠመችው ናይጄሪያ ከምድቧ መውደቅ ብዙዎችን አስገርሟል፡፡ ጊኒ 1-0 በሆነ ውጤት ናይጄሪያን አሸንፋ ከቻን ውድድር ውጪ አድርጋለች፡፡ በፈረንዳዊው ሊዊስ ፈርናንዴዝ ለሚሰለጥነው የጊኒ ብሄራዊ ብድን የማሸነፊያ ግብ ኢብራሂማ ሶሪ ሳንኮሆን የመጀመሪያው ግማሽ መጠናቀቂያ ላይ አስቆጥሯል፡፡ የናይጄሪያ አሰልጣኝ ሰንደይ ኦሊሴ የቻን 2016ን በኮከብ አግቢነትን በመምራት ላይ የሚገኘውን ቺሶማ ቺካታራን ቀይረው ቢያስገቡም ናይጄሪያን ከመውደቅ ሊታደጉ አልቻሉም፡፡ የጊኒው ግብ ጠባቂ አብዱልአዚዝ ኬታ ኮከብ ሆኖ አምሽቷል፡፡ ምድብ ሶስትን ቱኒዚያ በአንደኛነት ስታጠናቅቅ ጊኒ ሁለተኛ ሆናለች፡፡

12583848_766293826835121_1767959053_n

ያጋሩ