የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ኘሪምየር ሊጉ በአዲስ መልክ መካሄድ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ሲጠቀምበት የነበረውን አካሄድ በመቀየር እና የተሳታፊዎች ቁጥር በማብዛት በ2012 የውድድር ዘመን በሁለት ምድቦች 24 ክለቦች እንደሚሳተፉ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።
በፌዴሬሽኑ እንደምክንያትነት የቀረበው በየአካባቢው የሚንፀባረቁ የፖለቲካ አጀንዳዎች ወደ ውድድር ሜዳ በመምጣታቸው እና ይህንን ችግር “ለመቀነስ” ሲሆን ይህ ውሳኔ ባሳለፍነው ሐሙስ በፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈፃሚ አባላት ሲወሰን የነበሩትን ሁኔታዎች እናስቃኛችሁ።
* በፕሪምየር ሊጉ አሉ የተባሉ ችግሮችን ለመፍታት አማራጭ (የሊግ አደረጃጀት) ሀሳብ አልቀረበም። በቀጥታ 24 ይሁን የሚል መነሻ ሀሳብ ነው የቀረበው።
* ይህን የእግርኳሱ ትልቅ ውሳኔ ለመወሰን ሲታሰብ ምንም አይነት ጥናት አልቀረበም።
* የሊግ ኮሚቴ በዚህ ሂደት ላይ ምንም አይነት ተሳትፎ አላደረጉም።
* ከጉዳዩ ባለቤቶች ክለቦች ጋር የጋራ የምክክር መድረክ አልተዘጋጀም።
* የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን በጉዳዩ ላይ መነሻ ሀሳብ እንደሰጠ ተሰምቷል።
የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው እነዚህ ከላይ የቀረቡ ጉዳዮችን ሳያከናውን በቀጥታ የ2012 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በ24 ቡድኖች መካከል ይካሄዳል የሚል የውሳኔ ሀሳቡ ለስብሰባው ቀርቧል። አንድ የሥራ አስፈፃሚ አባል ይህ ሀሳብ ተቀባይነት የሌለው እና ለጠቅላላ ጉባዔ መቅረብ ያለበት እንደሆነ በመግለፅ “እንወስን ቢባል እንኳ በቀድሞ ፎርማት የሁሉም ክልል የውስጥ ውድድሩን ያወናውን (የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ይሁን)” የሚል ሀሳብ አቅርበዋል።
በዚህ ላይ ሰፊ ውይይት እና ክርክር ተደርጎ በቀደመው ፎርማት (የኢትዮጵያ ሻምፒዮና) ይካሄድ የሚል ሀሳብ ያቀረቡት የሥራ አስፈፃሚ አባላት ስብሰባውን አቋርጠው ሲወጡ በቀሩት አባላት ድምፅ ተሰጥቶ በአብላጫ ድምፅ ከ2012 ጀምሮ የኢትዮጵያ የኘሪምየር ሊግ በ24 ቡድኖች በሁለት በተከፈለ ምድብ እንዲካሄድ ተወስኗል። ከየምድቡ ከአንድ እስከ አራት የሚወጡ ስምንት ቡድኖችም በተመረጠ ቦታ የጥሎ ማለፍ ማጠቃለያ ጨዋታ በማድረግ የሊጉ አሸናፊ የሆነው ቡድን የሚለይበት አዲስ የውድድር አደረጃጀት ወስነው ሊወጡ ችለዋል።
አሁን እያወዛገበ ያለውና በቀጣይ የሚጠበቀው “የምድብ አደላደሉ በሊግ ኮሚቴ አማካኝነት ለክለቦቹ የሚቀርብ ይሆናል።” የሚለው ጉዳይ ነው። እንደተገኘው መረጃ ከሆነም የሊግ ኮሚቴው እስካሁን ምንም አይነት የምድብ ድልድል እንዳላደረገ እና ጉዳዩን በቀጣዮቹ ቀናት እንደሚመለከተው ለማወቅ ተችሏል።
ምንም አይነት ጥናት እና ቅድመ ዝግጅት ሳይደረግበት እንዲሁም የክለቦች ፍቃደኝነት ሳይታይ 24 ቡድኖች የሚሳተፉበት የፕሪምየር ሊግ ውድድር እንዲደረግ ፌዴሬሽኑ የወሰነው ውሳኔ ለእግርኳሱ ምን ይዞ ይመጣል የሚለው አጓጊ ሆኗል።
© ሶከር ኢትዮጵያ