የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተወሰኑ ለውጦች አድርጎ ወደ ዝግጅት ይገባል

የሃገር ውስጥ ተጫዋቾች ብቻ ለሚሳተፉበት ቻን ውድድር ማጣርያ ከዛሬ ጀምሮ ወደ መቐለ በማቅናት ዝግጅት የሚጀምሩት ዋልያዎቹ ባለፈው ሳምንት ሌሶቶን ባሸነፈው ስብስብ ውስጥ በነበሩት በውጪ ሊግ የሚጫወቱት ተጫዋቾች ምትክ ጥቂት ተጫዋቾች ወደ ስብስባቸው ሊቀላቅሉ እንደሚችሉ ታውቋል።

በቅድምያ ወደ ስብስቡ ይቀላቀላል የተባለው በቅርቡ ለሰበታ ከተማ ከተማ ፊርማውን ያኖረው አስቻለው ግርማ ሲሆን ተከላካይ ክፍል ለማጠናከር ጥሪ ይደርሳቸዋል የተባሉት የኢትዮጵያ ቡናው ፈቱዲን ጀማል ወይም የሃዋሳ ከተማው ወጣት ተከላካይ መሳይ ጳውሎስ ናቸው። አሰልጣኙም ከሁለቱም ተከላካዮች አንዳቸውን ወደ ስብስቡ ይቀላቅላሉ ተብሏል።

ከዚህ በተጨማሪም በጋብቻ ምክንያት ከዓለም ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታው ውጭ የነበረው ሱራፌል ዳኛቸው እንዲሁም በጉዳት ምክንያት በሌሶቶ የደርሶ መልስ ጨዋታ ያልተካተቱት ግብጠባቂው ምንተስኖት አሎ እና አማኑኤል ዮሐንስ ፣ ዘግይቶ ቡድኑን ቢቀላቀልም ወደ ሌሶቶ ያላቀናው ጌቱ ኃ/ማርያም ከቡድኑ ጋር ወደ መቐለ የሚያቀኑ ሲሆን አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ እንደየአስፈላጊነቱ ተጨማሪ ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ ሊያካትቱ እንደሚችሉ ሰምተናል።

ለጨዋታው ቅድመ ዝግጅት ዛሬ ወደ መቐለ በማቅናት ዝግጅት ይጀምራሉ የተባሉት ዋልያዎቹ ለመስከረም 12 ወሳኝ ጨዋታ ወደ ከተማው በገቡበት ቀን ጠንካራ ልምምዳቸው ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ