የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ፕሪሚየር ሊግ በዚህ ሳምንት

 

የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ፕሪሚየር ሊግ የመካከለኛ ዞን 3ኛ ሳምንት ጨዋታ አርብ ፣ ትላንት እና ዛሬ ተደርገዋል፡፡ ደደቢት ፣ ሀረር ሲቲ ፣ ባንክ ፣ መከላከያ እና የኢትዮጵያ ወጣቶች አካዳሚ ድል ቀንቷቸዋል፡፡

አርብ በተደረገው ብቸኛ ጨዋታ ደደቢት ኤሌክትሪክን 1-0 ሲረታ ብሩክ ብርሃኑ ብቸኛውን የድል ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ድሉን ተከትሎ ደደቢት የሊጉን መሪነት በ7 ነጥብ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ተረክቧል፡፡

ትላንት በ9፡00 የተገናኙት ኢትዮጵያ ወጣቶች አካዳሚ እና የአፍሮ ፅዮን ጨዋታ በአካዳሚ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ የአካዳሚን የድል ግቦች ሬድዋን ሰኢድ እና እሸቱ ጌታሁን (2) ከመረብ ሲያሳርፉ አብርሃም ደጉአለም የአፍሮ ጽዮንን ብቸኛ ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ በእለቱ 2 ግብ ከመረብ ያሳረፈው እሸቱ ጌታሁን ባሳየው ብቃት በስታድየም የተገኘውን ተመልካች አድናቆት አግኝቷል፡፡  (ከላይ በምስሉ የሚታየው) እሸቱ በ3 ጨዋታ 4 ግቦች በማስቆጠር የሊጉን ከፍተኛ ግብ አግቢነት እየመራ ይገኛል፡፡

በ11፡00 ሀሀር ሲቲ ኢትዮጵያ ቡናን 2-1 በማሸነፍ ደረጃውን አሻሽሏል፡፡ ከፍተኛ ውጥረት በነበረበት ጨዋታ አማኑኤል ተስፋዬ እና ታዲዮስ አዱኛ በቀድሞው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች እስማኤል አቡበከር ለሚሰለጥነው ሀረር ሲቲ ግቦቹን አስቆጥረዋል፡፡ የቡናን ብቸኛ ግብ ከመረብ ያሳረፈው ናትናኤል አሸናፊ ቡና ያስቆጠራቸውን ሁሉንም ግቦች (3 ግብ) ከመረብ ማሳረፍ ችሏል፡፡ በጨዋታው የሀረር ሲቲው የመስመር አማካይ ሚኪያስ መኮንን ተጫዋቾችን አታሎ የማለፍ ችሎታ በርካቶችን አስደምሟል፡፡

ዛሬ በ9፡00 መከላከያ አዲስ አበባ ከተማን 3-1 አሸንፏል፡፡ የመከላከያን የድል ግቦች ዮሃንስ ደረጄ (2) እና አስማማው ፈረደ ሲያስቆጥሩ ብሩክ ሙሉጌታ የአአ ከተማን ብቸኛ ግብ አስቆጥሯል፡፡ ዮሃንስ ደረጄ የመከላከያን 2ኛ ግብ ካስቆጠረ በኋላ ረዳት ዳኛው ከጨዋታ ውጪ ነው በሚል ባንዲራቸውን አንስተዋል በሚል የአአ ከተማ ክለብ ክስ አስመዝግቧል፡፡

በ3ኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ 11፡00 ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅዱስ ጊዮርጊስን 1-0 ሲያሸንፍ ተመስገን ዘውዱ የሃምራዊ ለባሾችን ብቸኛ ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡

የማእከላዊ ዞን የደረጃ ሰንጠረዥ ይህንን ይመስላል፡-

week 4 u17 standing

በአርባምንጭ ከተማ ከውድድሩ መውጣት ምክንያት የውድድር ፕሮግራሙ ላይ ዝብርቅርቅ የተፈጠረበት የደቡብ ዞን 4ኛ ሳምንት ላይ ደርሷል፡፡ 4 ክለቦች እየተሳተፉበት በሚገኘው የደቡብ ዞን በ4ኛው ሳምንት በተደረገ ብቸኛ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ ወላይታ ድቻን 4-0 በማሸነፍ 100% የማሸነፍ ሪኮርዱን አስጠብቋል፡፡

የደቡብ ዞን የደረጃ ሰንጠረዥ ይህንን ይመስላል፡-

south week 4 standing

———

ውድድሩ የወደፊቱ ኮከቦች እና የብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች የሚፈልቁበት እንደመሆኑ በውድድሩ ላይ የተመለከትናቸው ተስፋ የሚጣልባቸው ተጫዋቾችን በተለያየ ጊዜ እናቀርባለን፡፡

ያጋሩ