አዲስ አዳጊዎቹ ወልቂጤ ከተማዎች በሲንጋፖር መቀመጫውን ካደረገው ዓለማቀፉ የትጥቅ አቅራቢ ኩባንያ ከሆነው ማፍሮ ስፓርት ጋር በይፋ የትጥቅ አቅራቢነት ውል መፈራረማቸው ይታወቃል። ይህን ተከትሎም የክለቡ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አበባው ሰለሞን ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ስለ ስምምነቱ እና ተያያዥ ጉዳዮች በሚከተለው መልኩ ሀሳባተውን ሰጥተዋል።
” ወልቂጤ ከተማ ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ ሲያድግ በአዲስ መልክ ለመቅረብ ብዙ ጥረት እያደረገ ነው። አሁን ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ ለውጥ መፍጠር የምንችለው እኛ ክለቦች ወደ ዓለም አቀፍ አሠራር እና ቅርፅ ወዳለው የስራ ሂደት ስንገባ ነው። ከዛ ውስጥ አንደኛው ደረጃቸውን የጠበቁ የስፖርት ቁሳቁሶች ማቅረብ ስንችል ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ ወደ ዓለምአቀፍ ገበያ ብቅ ማለት ያስፈልጋል። እግርኳሳችንን ወደ ኢኮኖሚ ምንጭነት ለማሳደግ ከእንዲህ ዓይነት ደረጃቸውን የጠበቁ ትጥቅ አቅራቢዎች ጋር መስራት አለብን።
“ወልቂጤ ከተማ ዓለምአቀፍ ትጥቅ አቅራቢዎችን አወዳድሮ ነው ማፍሮ ስፖርትን የመረጠው። ይህን ስናደርግ አቅማችንን ፈትሸናል። ከዛም በተጨማሪ ትጥቅ አቅራቢው ከዚህ ቀደም ከማን ጋር ሰራ የሚለውን አይተናል። በአፍሪካ ገበያ ውስጥ ልምድ ያለው ሲሆን ከክለብ አንስቶ እስከ ብሔራዊ ቡድን ድረስ ማቅረብ የቻለ ትልቅ ኩባንያ ነው። ጋና ውስጥ ትላልቆቹ አሳንቴ ኮቶኮ እና ኸርትስ ኦፍ ኦክ፤ ዩጋንዳ ላይ ከብሔራዊ ቡድኑ እና ኪሲሲኤ ጋር እንዲሁም ከኬንያ ብሔራዊ ቡድን ጋር መስራት ችሏል።
” ኩባንያው ለሁለት ዓመታት ከቡድናችን ጋር የሚሰራ ሲሆን በአንድ ዓመት ውስጥ ዋናው ቡድን በሜዳው እና ከሜዳው ውጭ የሚለብሰውን ከ300 በላይ ትጥቅ በነፃ ያቀርባል። ይህን ለማድረግ ማሟላት ያለብንን ረዘም ላለ ጊዜ ተደራድረናል። ዛሬ ላይ ዋናው እና ከሜዳ ውጭ የምንለብሰውን መለያም አሳውቀናል።
” ክለባችን ከዚህ በተጨማሪ የአካዳሚ ግንባታውን አጠናቆ ለማስመረቅ ጥቃቅን ነገር ነው የቀረው። ይህ ለኢትዮጽያ ሆነ ለአከባቢው ህብረተሰብ ትልቅ እገዛ ያደርጋል። ቡድኑ በቀጣይ የሜዳው ግንባታ ላይ የሚያተኩር ሲሆን ይህን ማሟላት ስንችል በትክክለኛ መንገድ ላይ ጉዟችንን እናደርጋለን። ወልቂጤ ከተማ በቀጣይም አዲስ ነገር ይዞ ብቅ ይላል። እግር ኳሳችንን ወደ ተሻለ እርምጃ ለማራመድ እጅጉን ጠንክረን እየሰራን ነው። ”
© ሶከር ኢትዮጵያ