የኢትዮጵያ ቡና አራት ተጫዋቾች በክለቡ ላይ ቅሬታቸውን አሰሙ

አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌን ዋና አሰልጣኝ አድርገው የሾሙት ኢትዮጵያ ቡናዎች ለነባር (ውል ላላቸው) ተጫዋቾቹ የሙከራ ጊዜ እንዲያደርጉ መጠየቁ ቅሬታን አስነስቷል።

ኢትዮጵያ ቡናን ከተረከቡበት ጊዜ አንስቶ ለቀጣይ ውድድር ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ የሚገኙት አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ የተወሰኑ ተጫዋቾች በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ስላልተመለከቷቸው በቀጥታ በክለቡ ለማቆየት እንደሚቸገሩ እና የሙከራ ዕድል እንዳመቻቹላቸው በመግለፅ ዛሬ ለዘጠኝ ውል ላላቸው ተጫዋቾች ጥሪ ያቀረቡ ቢሆንም ጥሪ ከተደረገላቸው ተጫዋቾች መካከል ሄኖክ ካሳሁን፣ ተካልኝ ደጀኔ፣ የኃላሸት ፍቃዱ እና ቃልኪዳን ገዛኸኝ በውሳኔው የተሰማቸውን ቅሬታ ገልፀዋል።

ተጫዋቾቹ “የሚኖረን የሙከራ ጊዜ የለም። ውል ያለን እና ከዚህ ቀደምም በትላልቅ ቡድኖች በመጫወት ያገለገልን በመሆኑ ክለቡ ኮንትራታችንን አክብሮ የሚያስቀጥለን ከሆነ ለመጫወት ዝግጁ ነን። ይህ የማይሆን ከሆነ ከክለቡ ጋር በስምምነት እንለያይ።” በማለት ለአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ቅሬታቸው ያሰሙ ሲሆን አሰልጣኙም በምላሻቸው ጉዳዩን አጢነው በቀጣይ እንደሚያሳውቋቸው በመግለፅ ሙከራውን ሳያደርጉ ቀርተዋል።

ከዘጠኙ ተጫዋቾች መካከል ኃይሌ ለሙከራ ቢጠራም በኃላ ላይ ከዋናው ቡድን ጋር ዝግጅት እንደሚገባ ሲገለፅለት የተቀሩት ከተስፋ ቡድን ወደ ዋናው ቡድን ያደጉ አራት ተጫዋቾች በቀጣይ የሙከራ እድል እንደሚያገኙ ሰምተናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ