ኢትዮ ፕሪምየር ሊግ አክስዮን ማኅበር ምስረታን አስመልክቶ መግለጫ ተሰጠ (ዝርዝር ዘገባ)

ዛሬ ከሰዓት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በገዛው አዲስ ህንፃ ላይ ኢትዮ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ምስረታን አስመልክቶ መግለጫ ተሰጥቷል።

ጋዜጣዊ መግለጫውን ለመስጠት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት እና የሊግ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አወል አብዱራሂም (ኮሎኔል)፣ የውድድር እና ስነ-ስርዓት ኮሚቱ ሰብሳቢው አቶ ጌታቸው የማነብርሃን (ኢንስፔክተር)፣ የሕግ ባለሙያ አቶ ኃይሉ ሞላ እና አቶ ቴድሮስ ተገኝተዋል።

ዘለግ ያለ ጊዜን በወሰደው ይህ ጋዜጣዊ መግለጫ የተለያዩ ጉዳዮች የተነሱበት ሲሆን በተለይ ሊቋቋም ስለታሰበው የ”ኢትዮ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር” ገለፃ ተደርጓል።

በቅድሚያ ሃሳብ የሰጡት አቶ አወል አብዱረሂም (ኮሎኔል) ሊመሰረት ስለታሰበው የሊግ አክሲዮን ማኅበር ማብራሪያ ሰጥተዋል። “ከ1990 ጀምሮ ሲከናወን የነበረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተለያዩ ጥያቄዎችን ሲያስተናግድ ቆይቷል። በዋናነት ደግም የሚነሳው ጥያቄ ‘ሊጉ ለምን በራሱ አይመራም?’ የሚል ነው። ይህ ጥያቄ ደግሞ የፌደሬሽኑም ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አዲሱ አመራር ወደ ኃላፊነት ከመጣ ማግስት ጀምሮ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ቁልፍ ችግሮች ካላቸው እና የሪፎርም ጥናቱን ሳይጠብቅ ወደ ስራ ከገባባቸው ጉዳዮች ይህ አንደኛው እና ዋነኛው ነው። የስራ አስፈፃሚው ገና እንደተገናኘ ባደረገው ስብሰባም ይህ ጉዳይ ተነስቶ ሰፊ ውይይት ተደርጓል። በስብሰባውም የተለያዩ ሃሳቦች ተነስተው ነበረ። ነገር ግን በአጠቃላይ ድምፅ የወሰነው 2011 የመዘጋጃ ጊዜ እንዲሆን እና 2012 ፕሪምየር ሊጉ በራሱ እንዲመራ ማድረግን ነው። በዚህም ውሳኔ መሰረት ክለቦችን መስከረም ወር ላይ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ጠርተን አነጋግረን ውሳኔውን አስረድተናል። ስለዚህ በውሳኔው መሰረት 2011 የዝግጅት ጊዜ በመሆኑ ክለቦችን ሁለት ጊዜ በየካቲት እና ሚያዚያ ወር ጠርተን የአደራጅ ኮሚቴ አቋቁመናል። ኮሚቴውም ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ የተለያዩ ስራዎችን አከናውኗል። በነበረው ጊዜም የበርካታ ሃገራት ተሞክሮ ለማየት ተሞክሯል። ከውጪ ሃገራት ተሞክሮ በተጨማሪ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ያስጠናው የሪፎርም ጥናትም ለማየት ተሞክሯል። ነገር ግን ከሪፎርም ዶክመንቱ ውስጥ የተወሰደው ጥቂት ነገር ነው። በአጠቃላይ ግን የወሰድናቸውን ተሞክንም በቀጥታ አላመጣንም፣ በሃገራችን ነባራዊ እና የህግ ሁኔታ መሰረት ነው ይህንን ያመጣነው።

“ሌላው የተመለከትነው ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ይቋቋም ወይስ አክሲዮን ማኅበር ይመስረት የሚለውን ነው። ይህንንም ለመወሰን የሃገራችንን ክለቦች ባለቤት እና ተያያዥ ጉዳዮች ተመልክተናል። ይህ ማለት ብዙዎቹ የሃገራችን ክለቦች በመንግስት እጅ ስር ስላሉ አደረጃጀቱ ምን ይምሰል በማለት ነው የተወያየነው። በዚህም በሃገራችን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ለማቋቋም ግዴታ ክለቦቹ የግል መሆን ስላለባቸው ይህንን አልመረጥንም። የአክሲዮን ማኅበር ግን ለህዝባዊም ሆነ ለመንግስት ክለቦች አመቺ አሰራር ስለሚቀበል ይህንን መርጠናል።” ብለዋል። ኮሎኔሉ ቀጥለውም አክሲዮን ማኅበሩ 24 ተሳታፊ ክለቦችን እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽንን የያዘ እንደሆነ (በአጠቃላይ 25 አባላት ያሉት) ገልፀው እያንዳንዱ አባል ድርሻ ገዝቶ ወደ አክሲዮኑ እንደሚገባ አስረድተዋል።

በቀጣይ ኮሎኔል ዐወል ስለ ሊጉ አክሲዮን ማኅበር አደረጃጀት ማብራሪያ ሰጥተዋል። “አደረጃጀቱን በተመለከተ ያስቀመጥናቸው ነገሮች አሉ። ከላይ ሰባት አባላት የሚመሩት የዳሬክቶሬት ቦርድ አለ። ከዛ ዋና ዳይሬክተር ወይም ዋና ስራ አስኪያጅ አለ። ከዋና ስራ አስኪያጁ ስር የፅህፈት ቤት፣ የውስጥ ኦዲተር እና የህግ አማካሪ የሚባሉ አካላት አሉ። ከዚህ በመቀጠል የውድድር ዳይሬክቶሬት፣ የማርኬቲንግና ኮምኒኬሽን ዳይሮክቶሬት፣ የንግድ እና ኢንቨስመንት ዳይሬክቶሬት እና የፋይናንስ ዳይሬክቶሬት የሚባሉ አራት አካላት አሉ።” በማለት አደረጃጀቱን በዝርዝር አስረድተዋል። ማብራሪያ መስጠታቸውን የቀጠሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ካምፓኒው ሲቋቋም ስምንት አላማዎች አሉት በማለት አላማዎቹን ተናግረዋል።

ረዘም ያለ ማብራሪያቸውን ያላገባደዱት ኮሎኔል ዐወል 24 ክለቦች ለማወዳደር ስላሰቡበት መንገድ እና ስለ ቀጣይ እርምጃ ሃሳብ ሰጥተዋል። “በመጀመሪያ የመግባቢያ ሰነድ ነው የምንፈራረመው። በአቶ ቴዎድሮስ ፍራንኮ የተዘጋጀ የመግባቢያ ሰነድ አለ እሱን እኛ እና ክለቦች እንፈራረማለን። መስከረም 13 ከክለቦች ጋር ስንገናኝ የመግባቢያ ሰነዱ፣ የማስረጃ ፅሁፉ እና የመተዳደሪያ ደንብ ይቀርባል። ከዚህ በተጨማሪ የአመራር ቦርድ አባላት እንዲመረጡ እናደርጋለን። ከዛ በኋላ የአመራር ቦርዱ እና እኛ የሽግግር ስራዎችን ሰርተን እንወጣለን። 24 ክለቦችን የምናዋቅርበት መንገድን በተመለከተ ደግሞ እኛ የተመለከትነው እግር ኳሱ ሰላም እንዲሆን የሚያስችሉ እድሎችን ነው። በ2011 የተለያዩ ስራዎች ቢሰሩም አስገዳጅ ችግሮች አጋጥመውናል። እኛ ግን የተለያዩ ችግሮች ቢያጋጥሙንም ውድድሩ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ አድርገናል። አሁን ግን እግር ኳሱ በተለያዩ መንገዶች ለሚመጡ ችግሮች ማባባሻ መሆን የለበትም ብለን ጊዜያዊ መፍትሔ አስቀምጠናል። ወደፊት ግን ችግሮች በሚፈቱ ሰዓት አሁን የተቀመጠው መንገድ በማኅበሩ አማካኝነት ሊቀየር ይችላል። እኛ ያስቀመጥነው ጊዜያዊ መፍትሔን ነው እንጂ ቋሚ አደለም።”

ምክትል ፕሬዝዳንቱ አክለውም የሊጉ አሸናፊ የሚሆነው ክለብ (ከየምድቡ አንደኛ የሚሆኑት ክለቦች በደርሶ መልስ በገለልተኛ ሜዳ ከተጫወቱ በኋላ የሚያሸንፈው) በቀጥታ ወደ ቻምፒዮንስ ሊግ፤ ሁለተኛ የሚወጣው ደግሞ (በደርሶ መልሱ የተረታው) ወደ ኮንፌደሬሽን ዋንጫ እንደሚጓዝ፤ የጥሎ ማለፉን የሚያሸንፈው ክለብ በሴካፋ ዋንጫ እንደሚሳተፍ አስረድተዋል። በንግግራቸው መጨረሻም መስከረም 13 የምስረታ ጉባኤው እንደሚከናወን ጠቁመው ጉዳዩ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪካዊ እርምጃ ነው ብለዋል።

47 ደቂቃ ከፈጀው የፌደሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት ገለፃ በኋላ በቦታው የተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት ጥያቄዎች ሰንዝረዋል። በተለያዩ ጋዜጠኞች የተነሱ ጥያቄዎችንም መግለጫውን ለመስጠት በመድረኩ የተገኙት ኮሎኔል ዐወል፣ አቶ ሃይሉ፣ አቶ ቴዎድሮስ እና ኢ/ር ጌታቸው በየተራ ምላሽ ሰተዋል።

አቶ ኃይሉ

ስለ አክሲዮን ማኅበሩ አባላት እና ስለ 7ቱ የቦርድ አባላት?

“በመጀመሪያ አክሲዮን ማኀበሩ የሚፀድቀው በጠቅላላ ጉባዔው ነው። ከላይ እንደተገለፀው የጠቅላላ ጉባዔው አባላት ስለተለዩ መስከረም 13 ተሰብስበው አክሲዮን ማኅበሩን ያፀድቃሉ። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ደግሞ የአክሲዮን ማኅበሩ አባል የሆነው በህግ መሰረት ነው። ፌደሬሽኑ እዚህ አክሲዮን ማኅበር ውስጥ አንድ ድምፅ ነው ያለው። ስለዚህ ችግር የለውም። ደግሞም አባላቱ ፌደሬሽኑን አንፈልግም ካሉ ሊወጣ ይችላል በጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ መሰረት። ስለ 7ቱ የቦርድ አባላት ደግሞ ያለው ነገር ግልፅ ነው። በኢትዮጵያ የንግድ ህግ መሰረት አንድ ኩባንያ የሚመሰረተው ፍላጎት ባላቸው አባላት ነው። እነዚህ ፍላጎት ያላቸው አካላት ደግሞ ባለ አክሲዮን ይባላሉ። ስለዚህ እነዚህ ባለ አክሲዮኖች ናቸው የቦርድ አባል የሚመርጡት። በአጠቃላይ ከ25ቱ ባለ አክሲዮኖች ነው 7ቱ የቦርድ አባል የሚመረጠው። ቁጥሩን ደግሞ የወሰንነው በሃገራችን ህግ መሰረት ነው። በሃገራችን ህግ መሰረት አንድ አክሲዮን ማኅበር ሲመሰረት የቦርድ አባላቱ ከሶስት እንዳያንሱ ከአስራ ሁለት ደግሞ እንዳይበልጡ ያስገድዳል። ይህንን ተከትለን ነው የቦርድ አባላትን ቁጥር የወሰነው።”

ኮሎኔል ዐወል

ስለ አክሲዮን ማኅበሩ ድርሻ (ሼር) ጉዳይ….

“አንድ አክሲዮን አንድ ሺ ብር ነው የሚሸጠው። አንድ ክለብ ደግሞ ወደ ማኅበሩ ለመግባት አምስት ሺ አክሲዮኖች መግዛት አለበት። ይህ ማለት ደግሞ አምስት ሚሊዮን ብር ማለት ነው። አከፋፈሉን በተመለከተ ያስቀመጥናቸው ነገሮች አሉ። በአክሲዮን ማኅበር ምስረታው ወቅት አንድ አባል አንድ ሚሊዮን ሁለት መቶ ሃምሳ ሺ ብር ይከፍላል። ቀሪው ሶስት ሚሊዮን ሰባት መቶ ሃምሳ ሺ በቀጣይ አራት ዓመታት የሚከፈል ነው። ስለዚህ በአራት ዓመት ውስጥ ነው ተከፍሎ የሚጠናቀቀው። ገንዘቡም ደግሞ ብዙ አይደለም። ስንደምረው መቶ ሃያ አምስት ሚሊዮን ነው የሚመጣው። ስለዚህ መጠኑን ያስቀመጥነው ትርጉም ወዳለው ስራ ለመግባት ነው።”

ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጉዳይ…

“የወልዋሎ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ሊካሄድ አይችልም። ምክንያቱም ክለቡ (ቅዱስ ጊዮርጊስ) ሁለት ፎርፌ ስለሰጠ እና በህጉ መሰረት ሁለት ፎርፌ የሰጠ ጨዋታ ማድረግ ስለሌለበት ወልዋሎዎችን ጨዋታው እንደማይደረግ ገልፀን ሸኝተናል። አሁን ቅዱስ ጊዮርጊስን 24ቱ ውስጥ ያካተትንበት መንገድን ለመግለፅ ሞክረናል። እኛ እያልን ያለነው ወደ ታች የወረዱ ክለቦች እያመጣናቸው ስለሆነ ቅዱስ ጊዮርጊስም ይካተት ነው። ምክንያቱን ከ16 ወደ 24 ክለቦችን ከፍ ስላደረግን። ነገር ግን እኛ ህጉን ለመተርጎም እየሰራን በነበረበት ሰዓት ነው ይህ ነገር የመጣው።”

24ቱ ክለቦች ስለተለዩበት መንገድ…

“ክለቦቹ የተለዩበት መንገድ ግልፅ ነው። 16 የፕሪምየር ሊግ ክለቦች አሉ፣ 3 የወረዱ ክለቦች አሉ (መከላከያ ደቡብ ፖሊስ እና ደደቢት)፣ 3 ከከፍተኛ ሊግ ሁለተኛ ሁለተኛ የወጡ እንዲሁም 24 እንዲሞላ ከየምድቡ የተሻለ ነጥብ ያላቸው ሁለት ክለቦችን ወስደናል። ዋናው የወሰድነው መመዘኛ ነጥብ ነው። ሌላ መመዘኛ አልወሰድንም። ለምሳሌ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጥያቄ ጠይቆን ነበር። ነገር ግን ክለቡ ባለበት ምድብ ለገጣፎ 42 ነጥብ ሲኖረው ኢትዮ ኤሌክትሪክ 32 ነው ይዞ ያጠናቀቀው። ስለዚህ ይህንን ክለብ በየትኛውም መመዘኛ አናስገባውም። ያለን መመዘኛ ነጥብ ስለሆነ። ከዚህ በተጨማሪ እኛ ጋር በሁለቱም ምድብ አስር አስር ክለቦችን እናድርግ የሚል ነገር ተነስቶ ነበር። ነገር ግን እንደዚህ ከሆነ የጨዋታ ቁጥር ስለሚያንስ ይህንን አልወሰድንም። በአጠቃላይ ግን ፌደሬሽናችን ግዴታ 24 ክለቦች ይወዳደሩ ብሎ አያስገድድም። ከክለቦች ጋር ስንወያይ ክለቦች የተሻለ ነገር ካመጡ በዛ እንጓዛለን። ነገር ግን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ሳይዘነጋ።”

ክለቦቹ ስለሚደለደሉበት መንገድ….

“ድልድሉን የሊግ ኮሚቴው ቁጭ ብሎ ነው እየሰራበት ያለው። ድልድሉ ደግሞ ታሳቢ የሚያደርጋቸው ነገሮች አሉ። የመጀመሪያው እና ዋነኛው ለፎርማቱ መለወጥ ምክንያት የሆነው በክለቦች መካከል የተፈጠረው ነገር ነው። ይህ ማለት ለጊዜው መገናኘት የሌለባቸውን ክለቦች በተቻለ መጠን አለመገናኘት ነው። ሁለተኛው ክለቦቹ የሚሸፍኑት ርቀት ነው። ይህ ማለት ክለቦቹ ከሚያወጡት ወጪ አንፃር ማለት ነው። ሶስተኛው ደግሞ ተደራሽነትን ነው።”

በመጨረሻም የክለቦችን እግርኳሳዊ ያልሆነ ስያሜ ለማስቀየር ስራዎች መሰራታቸው የተገለፁት ምክትል ፕሬዝዳንቱ በሊጉ የሚወዳደሩ ክለቦች ከፖለቲካ፣ ዘር እና ማንነት ጋር የተያያዘ ስያሜያቸውን እንዲቀይሩ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ