የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ውሳኔ በቅዱስ ጊዮርጊስ ይግባኝ ዙርያ…

(መረጃው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ነው)

የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ከ28ኛ፣ 29ኛ እና 30ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ኘሪሚየር ሊግ ውድድር መርሐ ግብር ጋር በተያያዘ በፌዴሬሽኑ ከህግ ውጪ ተወስኖብኛል ስላላቸው ቅጣቶች ልዩ ልዩ ሰነዶችን በአባሪነት በማያያዝ የይግባኝ አቤቱታ በይግባኝ ማቅረቢያ ጊዜ ውስጥ አስፈላጊው ክፍያ ከተፈጸመበት ደረሰኝ ጋር አቅርቧል። የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴውም የቀረበለትን ጥያቄ በዝርዝር ተመልክቷል፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ፣ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተወሰነብኝ በማለት በአስረጂነት ካቀረባቸው ሰነዶች ለመመልከት እንደተቻለው ክለቡ በጨዋታ ላይ ባለመገኘቱ የተወሰነበት የፎርፌ ውጤት ቅጣት ፣ የገንዘብ ቅጣት እና የቡድን መሪው ላይ የተወሰነበት የዕገዳ ቅጣት መሆኑ ተገልጻል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ይኸ ቅጣት ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲስኘሊን መመሪያ አንጻር በአግባቡ ታይቶ የተወሰነበት ውሳኔ እንዳልሆነ ያስረዱልኛል ያላቸውን ማስረጃዎች በማያያዝ አቤቱታውን አቅርቧል፡፡

በ2011 ዓ.ም ጥቅምት ወር ተሻሻሎ በወጣው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲስኘሊን መመሪያ፡ ክፍል ሁለት ፣ ምዕራፍ አራት ፣ ከአንቀጽ 27-29፡ በተፈጥሮ እና በህግ ሰው በሆኑ አካላት ላይ የሚጣሉ የዲስኘሊን እርምጃዎችና ቅጣቶች ምን ምን እንደሆኑ በዝርዝር ተቀምጠዋል፡፡ በቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ በኩል ተወስነውብኛል ተብለው የተዘረዘሩት የፎርፌ ውጤት የገንዘብ እና በቡድን መሪው የዕገዳ ቅጣቶችም ከላይ በተጠቀሰው የዲስኘሊን መመሪያ ክፍል ውስጥ ከተዘረዘሩት የዲስኘሊን እርምጃዎችና ቅጣቶች መካከል ይገኙበታል፡፡

የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው በቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ በቀረቡት ሰነዶች ላይ ብቻ በመመርኮዝ የጉዳዩን አቅጣጫ ከመመርመር ይልቅ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽ/ቤት በኩል የዲስኘሊን ኮሚቴውን ውሳኔ ዝርዝር ሁኔታ የሚያሳዩ ቃለጉባኤዎች ፣ ይኸንን ጉዳይ የሚመለከቱ ማናቸውም ከቅዱስ ጊየርጊስ ስፖርት ክለብ ጋር የተደረጉ የደብዳቤ ልውውጦች እንዲሁም የጨዋታዎቹ የዳኞችና የኮሚሽነሮች ሪፖርቶች፣ እንዳቀርቡለት በደብዳቤ ጠይቆ በቃልም በተደጋጋሚ ቢያሳስብም ምላሽ ሳይሰጥ ቆይቶ ከረዥም ሳምንታት በኋላ የተወሰኑ ሰነዶት ከዲስኘሊን ኮሚቴ የጽሁፍ ምላሽ ጋር ቀርበዋል፡፡ የቀረቡት ሰነዶች ከመመልከቱ በፊት ይግባግ ሰሚ ኮሚቴው በዋናነት የመረመረው የዲስኘሊን ኮሚቴ በጽሁፍ የተሰጠውን የደብዳቤ ምላስ ነበር፡፡

የዲኘሊን ኮሚቴው ምላሽ ዋና ሐሳብ በአጭሩ ሲገለፅ፣ ይኸንን ጉዳይ ለማለት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ጋር በተያያዘ በተጠቀሱት ከ28-30ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ኘሪሚየር ሊግ ውድድሮችን በሚመለከት የቀረበለትም ሆነ ውሳኔ የሰጠበት ምንም ዓይነት ጉዳይ እንደሌለ ያሳወቀበት ምላሽ ነበር ፡፡

ከላይ በተጠቀሰው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲስኘሊን መመሪያ ፣ በክፍል ሁለት ምዕራፍ አንድ፣ አንቀጽ 11፣ ተ.ቁ 2፣ በግልጽ በተደነገገው መሰረት “በእግር ኳስ ዳኛው ከሚፈጽመው የቅጣት ውሳኔ ውጭ አንድ ድርጊት ማስቀጣት የሚችለው የፍትህ አካሉ ህገወጥ ድርጊት መፈጸሙን ከሚመለከታቸው አካላት ሪፖርት ቀርቦለት ሲያረጋግጥና ቅጣት የሚጣልበት ሆና ሲያገኘው ሲሆን በመርህ ደረጃ በመመሪያው መሠረት ጥፋተኛነቱ ካልተረጋገጠ በቀር ሊቀጣ አይችልም፡፡” ይላል፡፡

አንድ የይግባኝ አቤቱታ የሚያቀርብ ወገን ቀደም ሲል በሚመለከተው የፍትህ አካል ውሳኔ በተሰጠበት እና በዚህ ውሳኔ አልረካሁም ፍትህም አልተከበረልኝም ብሎ ሲያስብ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ በመሆኑም የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው የቀረበለትን የይግባኝ አቤቱታ በሚመለከት ወደ ዝርዝር ሁኔታ ከመግባቱ በፊት በቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ላይ በዚህ የዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት ቅጣት ተላልፎበታል ማለት ይቻላል ወይስ አይደለም ጉዳዩስ በይግባኝ መታየት ይኖርበታል ወይስ አይደለም በሚሉ ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ በመጨረሻ እንደሚከተለው ከድምዳሜ ደርሷል፡፡

በቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ የቀረበው የይግባኝ አቤቱታ ጥያቄ ቀደም ሲል በተጠቀሰው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት ጉዳዩ ላይ ቅጣት ውሳኔ የመስጠት ስልጣን በተሰጠው የፍትህ አካል (በዲሲፕሊን ኮሚቴው) የተወሰነ ባለመሆኑ የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ተሰጠብኝ ባለው ውሳኔ ዝርዝር ሁኔታ ላይ ውይይት ማድረግ የማይጠበቅበት መሆኑን እንዲሁም በዲሲፕሊን መመሪያው መሰረት በቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ እና በክለቡ የቡድን መሪ ላይ የተወሰነው ምንም ዓይነት ህጋዊ የዲሲፕሊን ቅጣት (የፍትህ ውሳኔ) የሌለ በመሆኑ፤ በህግ ስልጣን ከተሰጠው አካል ውጭ የተሰጠን የቅጣት ውሳኔ ውድቅ እንዲደረግ፤ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ለይግባኝ ያስያዘው ብር 1500 (ብር አንድ ሺህ አምስት መቶ) ተመላሽ አንዲደረግለት በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

በተጨማሪ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የተደረሰበትን የውሳኔ ግልባጭ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ እና ለሚመለከታቸው አካላት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽ/ቤት በኩል በጽሁፍ እንዲደርሳቸው በሚል ውሳኔ አስተላልፏል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ