ኢትዮጵያ ቡና በዲዲዬ ጎሜስ የአሰልጣኝነት ዘመን ከተስፋ ወደ ዋናው ቡድን በማደግ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ካደረጉ ሦስት ወጣት ተጫዋቾቹ ጋር ተለያይቷል።
ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ከ17 ዓመት በታች ቡድን በኮከብ ጎል አስቆጣሪነት በማጠናቀቅ ክለቡ መፍረሱን ተከትሎ የኢትዮጵያ ቡናን ከ20 ዓመት በታች ተቀላቅሎ እየተጫወተ በአሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ አማካኝነት ወደ ዋናው ቡድን በማደግ ያለፉትን ሁለት ዓመታት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ያደረገው አጥቂው ተመስገን ዘውዱ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የተለያየ ተጫዋች ሆኗል።
አማካዩ ቢኒያም ካሳሁን ሌላው ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የተለያየ ተጫዋች ነው። ከታችኛው ቡድን አንስቶ መልካም እንቅስቀሴ በማሳየቱ ወደ ዋና ቡድን በማደግ ገብቶ በተጫወተባቸው የተወሰኑ ጨዋታዎች ላይ የሚያድግ እንቅስቃሴ አሳይቶ ነበር።
ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ከተለያዩ ወጣት ተጫዋቾች መካከል ሦስተኛው አጥቂው ፍፁም ጥላሁን አንዱ ነው። እንደ ሌሎቹ ተጫዋቾች ሁሉ ከታችኛው ቡድን በአሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ አማካኝነት ወደ ዋናው ቡድን በማደግ በፕሪምየር ሊግ ተቀይሮ በመግባት ጎል በማስቆጠር እና ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ ችሎ ነበር።
ሦስቱ ተጫዋቾች ከቡድኑ ጋር የተለያዩት አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ባዘጋጁት የሙከራ ጊዜ አሰልጣኙን ማሳመን አልቻሉም በሚል ምክንያት ነው።
© ሶከር ኢትዮጵያ