የጆናታን ዊልሰን Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የአማርኛ ትርጉም በግሩም አተራረክ ሰባት ምዕራፎች አልፈን ወደ ስምንተኛው ተሸጋግረናል። በዛሬው መሠናዶም የምዕራፉ የመጀመርያ ክፍል ይቀርባል
የእንግሊዞች ተግባራዊ እውነታ (1)
በመጋቢት-ወር 1960 በርሚንግሃም ከተማ በሚገኘው አውሮፕላን ማረፊያ እንደነገሩ በተዘጋጀ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ሄሌኒዮ ሄሬራ እንዲህ አለ፡፡ ” እናንተ እንግሊዛውያን – የምትከተሉት የአጨዋወት ዘይቤ ከረጅም ዓመታት በፊት በሌሎች የአህጉሪቱ ክፍሎች የምንገኝ አሰልጣኞች የተጠቀምንበት ነው፡፡ የበዛ አካላዊ ጥንካሬ ላይ ታተኩራላችሁ፤ ጨዋታችሁ ቴክኒካዊ ውበት አልተላበሰም፤ አቀራረባችሁም ዘፈቀዳዊነት አርቦበታል፡፡” ሄሬራ ይህን አስተያየት ከመስጠቱ አንድ ቀን በፊት በነበረው ምሽት እርሱ የሚመራው ባርሴሎና የእንግሊዙን ሻምፒዮን ዎልቨርሃምተን ዎንደረርስን በከፍተኛ የጨዋታ ብልጫ ሲያሸንፍ ያየ ማንም ሰው በአርጀንቲናዊው አሰልጣኝ ሐሳብ ጥርጣሬ አይገባውም፡፡ በወቅቱ አስደናቂ የውድድር ዘመን በማሳለፍ ላይ የከረመው የስፔኑ ክለብ በዩሮፒያን ካፕ የሩብ ፍጻሜ ፍልሚያ በካምፕ-ኑ ዎልቭስ ላይ ቀደም ብሎ የ4-0 ድል ተቀዳጀ፤ በመልሱ ጨዋታ የእንግሊዙን ክለብ በሞሊኒክስ 5-2 በመረምረም የ9-2 ድምር ውጤት ይዞ ወደ ግማሽ ፍጻሜው አለፈ፡፡ ዎልቭስ በወዳጅነት ግጥሚያዎች ኻኖቭድ እና ስፓርታክ ሞስኮው የመሳሰሉ ክለቦችን የሚረታባቸው እነዚያ ወርቃማ ጊዜያቱ በሚያሳዝን ሁኔታ ያመለጡት መሰለ፡፡
በእርግጥ ሚዛናዊ ሆኖ ነገሩን ለቃኘ ዎልቭሶች ከሌሎች ክለቦች በተሻለ የአጨዋወት ቀጥተኝነት ታይቶባቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ለሄሌኒዮ ሄሬራ ይህም የተዋጠለት አይመስልም፡፡ ” እነርሱ የሃገር ውስጡን ውድድር በበላይነት የተቆጣጠሩበት መንገድ የእንግሊዝ እግርኳስ አካሄድ አጠቃላይ ድክመትን ያንጸባርቃል፡፡” ባይ ነው፡፡ ሄሬራ በሃገሪቱ የሚታየው የእግርኳስ ተፈጥሯዊ ወግ- አጥባቂ ሥርዓት ላይ እየቀለደ “ብሪታኒያውያን በዘመናዊ እግርኳስ የጨዋታውን ዘገምተኛ የእድገት እርከኖች ሳይስቱ አልቀረም፤ እንግሊዛውያን እኮ ሻይ አምስቴ የመጠጣት ልማድ የጀመሩ ናቸው” ይላል፡፡ የያኔው ዎልቭስ አሰልጣኝ ስታን ኩሊስ በእግርኳሱ ዓለም የተራማጅ አስተሳሰብ ከሚያቀነቅኑ እንግሊዛውያን አሰልጣኞች መካከል አንዱ የነበረ መሆኑ የአርጀንቲናዊውን የታክቲክ ባለሟል አስተያየት የምጸት እንዲሆን አድርጎታል፡፡
የሃንጋሪው ከባድ ሽንፈት ለእንግሊዞች ትልቅ ኪሳራ አምጥቶባቸዋል፡፡ ሃገሪቱ በእግርኳስ የገነባችውን የልዕልና ማማ ንዷል፤ በሌሎች ዘንድ እንግሊዛውያኑ በጨዋታው እንደነበራቸው ሲታሰብ የኖረውን የበላይነት ስሜት ተራ ትርክት እንዲሆን አድርጎባቸዋል፡፡ በእርግጥ ሽንፈቱ መጠነኛ አዎንታዊ አበርክቶዎችም ነበሩት፡፡ እግርኳስ ጀማሪዋ ሃገር ሙጥኝ ያለችውን ነባር የጨዋታ አቀራረብ ስልት መቀየር እንዳለባት ግንዛቤ ፈጥሮላታል፤ በጊዜው የሃገሪቱ ወርቃማ የእግርኳስ ዘመናት ካለፉ በርካታ ዓመታት እንደተቆጠሩ የሚያሳዩ ቁጭት አዘል አያሌ መጽሃፍት እየታተሙ መውጣታቸውም ከሽንፈቱ ትሩፋቶች አንዱ ሆኗል፡፡ እንዲያም ሆኖ ችግሩ የሚቀረፍበትን መንገድ በማበጀት በኩል የትኛውም አካል እርምጃ ለመውሰድ አልደፈረም፤ አንደኛው ተግዳሮት ደግሞ መፍትሄውን የመስጠት የጠለቀ እውቀት ባለቤት እጥረት ነበር፡፡
ከዌምብሌዩ ሽንፈት በኋላ W-Mን (3-2-2-3) የማጥላላት ዘመቻ ተካሄደ፤ ነገርግን ፎርሜሽኑ ጥቅም ላይ መዋሉን ቀጠለ፡፡ በችግሮቹ ዙሪያ ውይይቶች ሲደረጉ የሚነሱ መፍትሄዎች በሙሉ ዊሊ ሜይዝል ቀደም ሲል <ሶከር ሪቮሊውሽን> በተሰኘው መጽሃፉ ላይ ያቀረባቸው የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮሩ ሆኑ፡፡ ወደ ቀደመው የእግርኳስ ሃያልነት ዘመን ለመመለስ የሄሌኒዮ ሄሬራን የትችት ሐሳብ እውነታነት ለማረጋገጥ ከመጣር ይልቅ በድጋሚ ወደኋላ ሄዶ <2-3-5>ን ጥቅም ላይ ማዋል የብዙዎች ፍላጎት ሆኖ ተገኘ፡፡ የተቀረው ዓለም በታክቲካዊ ጉዳዮች ይበልጡን እየሰለጠነ ሲሄድ በብሪታንያ የነበሩ ተሰሚ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ የእግርኳስ ጸሃፍት ግን ከሃያ ዓመታት በፊት ወዳበቃለት የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደር ሥርዓት መመለስን በብቸኛ አማራጭነት ይዘው መከራከርን መረጡ፡፡
በብሪታኒያ የሃንጋሪን አጨዋወት ዘይቤ የመኮረጅ ሃሳብ ተግባራዊ የተደረገው በማንችስተር ሲቲ ነበር፡፡ በ1953-54 የውድድር ዘመን መጨረሻ በክለቡ የተጠባባቂ ቡድን ውስጥ ወደኋላ ባፈገፈገ የመሃል አጥቂነት (Deep-Lying Centre-Forward) ጆኒ ዊሊያምሰን ስኬታማ ጊዜ አሳለፈ፡፡ በቀጣዩ ዓመት የዋናው ቡድን አሰልጣኝ ማክ ዶዌል ለዚሁ ሚና ዶን ሪቪዬን መጠቀም ጀመረ፡፡ ሪቪዬ የኋላኋላ ባዘጋጀው ባለ ሃያ ገጽ የግል ማስታወሻው <ሶከር’ስ ሃፒ ዋንደረርስ> ላይ የአጨዋወት ሥርዓቱን ለማብራራት ጥሯል፡፡ ክለቡ በውድድር ዘመኑ የመክፈቻ ጨዋታ ደካማ አቋም አሳይቶ በፕሪስተን 5-0 ተረታ፡፡ ማንችስተር ሲቲ በሃይለኛ ዝናብ ምክንያት ጨቅይተው አስቸጋሪ በሆኑት ሜዳዎች ላይ እየተጫወተ በጥሎ ማለፉ ዋንጫ የፍጻሜ ተፋላሚ ሆነ፤ በሊጉ ደግሞ ሰባተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቀቀ፤ ሪቪዬም የዓመቱ ምርጥ ተጫዋችነት ክብርን ተጎናጸፈ፡፡ ይሁን እንጂ በዚያ ክረምት ሪቭዬ ከክለቡ ፈቃድ ውጪ ከቤተሰቡ ጋር በብላክፑል የእረፍት ጊዜውን አሳለፈ፡፡ በዚህ ድርጊቱ ቀጣዩ ውድድር ዘመን ሲጀመር የተላለፈበትን የሁለት ሳምንታት ቅጣት ከጨረሰ በኋላ በክለቡ ሰዎች ፊት ተነስቶ እዚያው በባይተዋርነት ቆየ፡፡ ከጉዳት መልስ በእግርኳስ ማህበሩ የፍጻሜ ጨዋታ ማንችስተር ሲቲ በርሚንግሃምን ሲረታ በቋሚነት ተሰልፎ ተጫወተ፡፡ በቀጣዩ የውድድር ዘመን ግን እንዳሰበው ከክለቡ ጋር መቀጠል አልቻለም፤ በቀጥታ ወደ ሰንደርላንድ አመራ፡፡
ከሪቪዬ መልቀቅ በኋላ ሲቲ ወደ ቀደመው ባህላዊ የአጨዋወት ሥርዓት ተመለሰ፤ ተጫዋቹም በሮከርፓርክ (የሰንደርላንዳ የቀድሞው ስታዲየም) መረጋጋት ተሳነው፡፡ በወቅቱ ሰንደርላንድ ተገቢ ባልሆነ የገንዘብ አጠቃቀም ሳቢያ ህገወጥ በሆኑ ክፍያዎች ቅሌት ተዘፈቀ፡፡ የክለቡ ኃላፊዎች ለተጫዋቾቻቸው በግዴለሽነት ጨዋታ በማሸነፍ ከሚገኘው የተለመደ የማበረታቻ ከፍተኛ የአራት ፓውንድ የጉርሻ ክፍያ እጥፉን የሚልቅ አስር ፓውንድ በማቅረብ ሚዛኑን የሳተ ምዝበራ ሲፈጽሙ ተያዙ፡፡ በዚህ ትርምስምስ መሃል የሰንደርላንዱ አሰልጣኝ ቢል ሙሬይ ክለቡን ለቀቀ፤ አለን ብራውንም በእርሱ ምትክ ተሾመ፡፡ አዲሱ አሰልጣኝ እድለኛ አልነበረም፤ ቡድኑን ይዞ ወደ ታችኛው ዲቪዚዮን ወረደ፡፡ ሪቭዬም ከቡድኑ ጋር ሊላመድ አልቻለም፡፡ ” እርሱ የሚስማማው አንድ የአጨዋወት መንገድ ብቻ ነበር፡፡ ለእኛ እንግዳ የሆኑ በርካታ እንቅስቃሴዎችን ይከውን ነበር፡፡ ዶን በሜዳ ላይ ጨዋታ የሚያካሄድበት ሥርዓት በማንችስተር ሲቲ ሳለ አዲስ ስለነበር የተሳካ ሊሆን ችሏል፤ ወደዚህ ሲመጣ ግን ሁሉም እርሱን የመቆጣጠር መላ ዘይዶ ስለጠበቀው ተቸገረ፤ እንዲያም ሆኖ ዶን ሊቀየር አልቻለም፡፡” ሲል በሰንደርላንድ ከመሃል አጥቂው በስተቀኝ የሚጫወተው (Inside-Right) ቻርሊ ፍሌሚንግ ያኔ በክለቡ ዶን ሪቭዬ ላይ የተጋረጠውን ተግዳሮት ያብራራል፡፡ የዶን ችግር የእርሱ ብቻ አልነበረም፤ ብዙሃኑ የብሪታኒያ ተጫዋቾች ላይ ይታይ የነበረ ድክመት እንጂ፡፡ ሪቭዬ ወዲያውኑ ሰንደርላንድን ተሰናብቶ ወደ ሊድስ አቀናና በመሃል አጥቂነት ይሰለፍ ጀመር፡፡ በዚያው በዶን ሪቭዬ አማካኝነት የተጀመረው የአዲሱ ሚና ሙከራ አከተመ፡፡
በአውሮፓ ክለቦች ውድድር ጅማሮ የብሪታኒያ ክለቦች ያገኙት አንጻራዊ ስኬት በአዳዲስ የእግርኳስ አቀራረብ ፈጠራዎች አማካኝነት ሳይሆን የጥንቱን አጨዋወት ሥርዓት በጥሩ ሁኔታ መተግበር በመቻላቸው ያመጡት ውጤት ነበር፡፡ለምሳሌ፦በመጀመሪያው የአውሮፓ ክለቦች ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ ተፋላሚ የነበረው ኺበርኒያ በአምስቱ ተጫዋቾች (ጎርደን ስሚዝ፣ ቦቢ ጆንስተን፣ ላውሪ ሬይሊ፣ ኤዲ ተርንቡል እና ዊሊ ኦርሞንድ) በሚመራው የፊት መስመር (Five-Front Line) ዝነኛ ሆኖ ነበር፡፡ የወጣቶቹና ቀልጣፎቹ ቦቢ ቻርልተን፣ ዴኒስ ቫዮሌትና ደንከን ኤድዋርድስ ማንችስተር ዩናይትድም የአጨዋወት ታክቲኩን በW-M ፎርሜሽን ላይ የተመሰረተ እንዲሆን አድርጓል፡፡ ” እነርሱ (አጥቂዎቹ) ረጃጅም እና አጫጭር ቅብብሎች የተዋሃዱበትን የጨዋታ ዘይቤ በመከተል እምብዛም ከተጋጣሚው ሳጥን ውጪ የማይንቀሳቀሰውን የተለመደ የፊት መስመር ቅርጽ (Static Conventional Front-Shape) እንዲወገድ አስችለዋል፡፡ በመሰረታዊነት ደግሞ በአግባቡ የተደራጀ የተከላካይ ክፍል ገንብተው ታላቅ ቡድን ሆኑ፡፡ ፍሰቱን በጠበቀ ድንገተኛ የጨዋታ ሒደት ሽግግር በማጥቃት ወረዳው ላይ ተጋጣሚን በማፈን ውጤታማ ሆኑ፡፡ ይህኛው የአጨዋወት ዘዴ በማጥቃት ክልሉ የመጨረሻ ክፍል ትርፍ ተጫዋች (Spare man/ Man over) እንዲኖራቸው አስቻላቸው፡፡” ይላል ጂኦፍሪይ ግሪን ስለ ቡድኑ የጨዋታ ሥልት ሲተነትን፡፡ በብሪታኒያውያኑ ዘንድ የታላቁ አሰልጣኝ ማት በዝቢ ማንችስተር ዩናይትድ በመከላከል እና ማጥቃት የጨዋታ ሒደቶች ደረጃውን ጠብቆ የሚዋልል ቡድን እንዲሁም የተጫዋቾቹ ድንቅ ጥምረት ጥያቄ የማይነሳበት ቢሆንም ከአውሮፓውያኑ ታክቲካዊ ደረጃ አንጻር በቀጥተኛ ወግ አጥባቂነት የሚፈረጅ ነበር፡፡
ይቀጥላል...
ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡ ባለፉት አስራ ሁለት ዓመታትም ዘጠኝ መፅሐፍትን ለህትመት አብቅቷል፡፡