በ2020 ቻን ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በትግራይ ስታዲየም ሩዋንዳን አስተናግዶ 1-0 በመሸነፍ የማለፍ ተስፋውን አጣብቂኝ ውስጥ ከቷል።
በጨዋታው የመጀመርያው አስራ አምስት ደቂቃዎች ዋልያዎቹ ብልጫ ያሳዩ ሲሆን በተጋጣሚያቸው ላይ እንደወሰዱት ብልጫ የግብ ዕድሎች መፍጠር ባይችሉም በቁጥር ትንሽ የማይባሉ ሙከራዎች አድርጓል። አማኑኤል ገብረሚካኤል ከከነዓን ማርክነህ የተሻገረለትን ኳስ በውሳኔ አሰጣጥ ችግር ያመከናት፣ ፍቃዱ ዓለሙ ከደስታ ደሙ የተመቻቸለትን ኳስ ተጠቅሞ በግንባር ያደረገው እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራ፣ ከነዓን ማርክነህ ከሐይደር ሸረፋ የተላከለት ኳስ ተጠቅሞ መትቶ ግብ ጠባቂው እንደምንም ያወጣበት እንዲሁም አሕመድ ረሺድ በግሩም ሁኔታ አሻግሮት ከግቡ አቅራቢያ የነበረው አማኑኤል ገብረሚካኤል በማይታመን ሁኔታ ያመከነው ኳስ ለወሰዱት ብልጫ በአብነት የሚጠቀሱ የጎል ዕድሎች ናቸው።
ኦሊቨር ንዮንዚማ እና ጃቤል ማንሻሚዌ በግል ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ውጭ እንደ ቡድን ማጥቃት ያልቻሉት እንግዳዎቹ ሩዋንዳዎች ጂያን ክላውድ ከመስመር የተሻገረለት ኳስ ተጠቅሞ ካደረገው ሙከራ ውጭ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። በአንፃሩ ዋልያዎቹ በመጀመርያው አጋማሽ የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በሃይደር ሸረፋ እና መስፍን ታፈሰ መሪ የሚሆኑባቸውን ጎሎች ለማግኘት ተቃርበው ነበር።
ቡድኑ በመጀመርያው አጋማሽ በኳስ አመሰራረት ሂደት ላይ በርካታ በጎ ነገሮች አሳይቶ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢወስድም የጎል ዕድሎች በመፍጠር ረገድ ግን ደካማ ነበር። በተለይም ቡድኑ በሶስተኛው የሜዳ ክፍል ያለው ደካማ እንቅስቃሴ የኳስ ቁጥጥር ብልጫው ፍሬ አልባ አድርጎታል።
ከመጀመርያው አጋማሽ አንፃር የተሻሉ ጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች በታዩበት ሁለተኛው አጋማሽ ዋልያዎቹ ንፁህ የግብ ዕድሎች የፈጠሩበት ነበር። ደስታ ደሙ እና ከነዓን ማርክነህ ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴ ባሳዩበት አጋማሽ ሙከራ በማድረግ ቀዳሚ የነበሩት ዋልያዎቹ ሲሆኑ ሙከራውም በፍቃዱ አለሙ አማካኝነት የተደረገ ነበር። ከመጀመርያው ሙከራ ብዙም ሳይቆይ አማኑኤል ገብረሚካኤል ከደስታ ደሙ በግሩም ሁኔታ የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ያደረገው ሙከራም ይጠቀሳል።
በመጀመርያው አጋማሽ ዒላማው የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ያልቻሉት ሩዋንዳዎች በሁለተኛው አጋማሽ ግን በርካታ ዕድሎች ፈጥረዋል። በተለይም ሳቢማና ኤሪክ እና ማንዚ ቴሪ ከርቀት ያደረጓቸው ጥሩ ሙከራዎች ይጠቀሳሉ። ከሁለቱ ሙከራዎች ውጭም ኢማኑኤል ኢማንሺማዌ ያደረገው ግሩም ሙከራ እና ፎቲና ኦምቦሪንጋ ከቅጣት ምት ያደረገው ለግብ የቀረበ ሙከራ ይጠቀሳሉ። በስልሳ አንደኛው ደቂቃም አጥቂው ኤርነስት ሱጊራ ከቅጣት ምት የተሻማችለትን ኳስ በግሩም ሁኔታ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።
የዋልያዎቹ ፍፁም ብልጫ እና በርካታ የውሳኔ አሰጣጥ ችግር የታየበት የመጨረሻው አስራ አምስት ደቂቃ ኢትዮጵያ በደስታ ደሙ አማካኝነት አራት የሚደርሱ ዕድሎች ፈጥራለች። በተለይም ተከላካዩ ከሳጥኑ ጠርዝ አክርሮ መቶ ቋሚው የመለሰበት እና ከሃይደር ሸረፋ የተላከለትን ኳስ ተጠቅሞ በግንባር ያደረገው ሙከራ ኢትዮጵያን አቻ ለማድረግ የተቃረቡ ነበሩ። ተከላካዩ ከሁለቱም ሙከራዎች ውጭም በግንባር ያደረገው ሙከራ ተጠቃሽ ነበር። ያሬድ ባዬህ ከርቀት ያደረጋት ሙከራ እና ሙጂብ ቃሲም በመጨረሻው ሰዓት ሞክሯት ግብ ጠባቂው ንዳሽምየ ኤሪክ እንደምንም ያወጣት ኳስ አስቆጪ ነበረች።
ውጤቱ በዚ የህ መልኩ በሩዋንዳ 1-0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ከ27 ቀናት በኋላ በሜዳዋ የመልሱን ጨዋታ የምታደርገው ሩዋንዳ የማለፍ ዕድሏን አስፍታለች።
© ሶከር ኢትዮጵያ