በወቅታዊው የእግርኳሱ ችግር ዙርያ የመፍትሔ አቅጣጫ ለመስጠት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ሰብሳቢነት የተካሄደው የውይይት መድረክ ዝርዝር ዘገባ።
የኢፌዲሪ ባህልና ወጣቶች ሚኒስቴር ሂሩት ካሳ (ዶ/ር)፣ የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ም/ኮሚሽነር፣ አሸብር ወ/ጊዮርጊስ (ዶ/ር)፣ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝደንት፣ የዘጠኙ የክልልና የ2ቱ ከተማ መስተዳድር የስፖርት ኮሚሽን አመራሮች እና እግርኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንቶች እንዲሁም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ እና ስድስት የሥራ አስፈፃሚ አባላት በውይይቱ ላይ ተካፍለዋል።
በዶ/ር ሂሩት ሰብሳቢነት በተመራው በዚህ የውይይት መድረክ አቶ ኢሳይያስ ጂራ በ2011 በእግርኳስ የተፈጠሩ ያሉ ችግሮች ምን እንደሆኑ በዝርዝር በማስረዳት እየተፈጠሩ ያሉ አለመግባባቶችን ለመቀነስ እንደመፍትሄ በጊዜያዊነት በሁለት ምድብ የተከፈለ 24 ቡድኖች የሚካፈሉበት ውድድር ማዘጋጀት እንዳስፈለገ ለተሰብሳቢው ገልፀዋል።
” ይህ ውሳኔ የተወሰነው ክለቦች ሳይማከሩበት እና ጥናትን መሠረት ያላደረገ መሆኑን በቅወቱም በሥራ አስፈፃሚ ስብሰባ ወቅት አፅኖት ሰጥተን ተናግረን ነበር። ሆኖም እኛ በማናቀው መልኩ የተወሰነ ውሳኔ ነው።” በማለት አንዳንድ የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈፃሚ አባላት መናገራቸውን ተከትሎ በፌዴሬሽኑ አመራሮች መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ እንደነበረ ሰምተናል።
የክልል እግርኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች በተለይ የአማራና የትግራይ እግርኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች በበኩላቸው 24 ቡድኖች ሆነው አማራና ትግራይ ክለቦች እንዳይገናኙ በማለት የተወሰነው ውሳኔን እንደማይቀበሉት፤ እግርኳስ የሠላም እና የማቀራረቢያ መድረክ መሆኑን ተናግረዋል። አዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጥናት በማስጠናት በውስጥ ውድድር ተካሂዶ በኃላም በኢትዮጵያ ሻምፒዮና ውድድሩ ይጠናቀቅ በማለት ያቀረበው ሀሳብ የሚያስመሰግን ሆኖ ሳለ ፌዴሬሽኑ እንደ መፍትሄ ከመቀበል ይልቅ የራሱን መንገድ መከተሉ ስህተት መሆኑን እና የክልል እግርኳስ ፌዴሬሽኖች ጋር ተቀራርቦ የመስራት ችግሮች እንዳለበት ተናግረዋል። የኦሊምፒክ ፕሬዝደንቱ በበኩላቸው 24 ቡድኖች መሳተፋቸውን እንደማይደግፉ እና ከኦሊምፒክ መርህ አንፃር ክልሎች እና ህዝቦች እንዳይገናኙ ማድረግ ተገቢ አለመሆኑን ገልፀዋል።
የመድረኩ ሰብሳቢ በበኩላቸው “ፊፋ ላስቀመጠው ደንብ እና ህግ ተገዢ በመሆን፤ አባል ሀገራቱም ለተቀመጠው መመርያ ተገዢ እንዲሆኑ በማድረግ እያስተዳደረ በመገኘቱ ነው ተፈሪና ተቀባይነት ያለው ተቋም የሆነው። እናተም ላወጣችሁት ደንብ እና መመረያ ተገዢ በመሆን እግርኳሱን መምራት ይገባችኋል።” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመጨረሻም በፌዴሬሽኑ አመራሮች መካከል የተፈጠረውን የሀሳብ ልዩነት በውስጥ እንዲፈቱ፤ በ24 ቡድኖች ለሁለት የተከፈለው ውድድር ለጊዜው እንዲቆም እና ባለ ድርሻ አካላት ክለቦች በተገኙበት ውይይት በማድረግ ዘላቂ መፍትሄ እንዲቀርብ ተወስኗል። ስፖርት ኮሚሽንም ጉዳዩን በጥንቃቄ እንደሚከታተለው ሰምተናል።
© ሶከር ኢትዮጵያ