ባሳለፍነው ሚያዝያ ወር ሦስት ተጫዋቾችን ወደ ዋኛው ቡድን አሳድጎ የነበረው ሀዋሳ ከተማ አሁን ደግሞ አምስት ወጣቶችን ከተስፋ ቡድኑ አሳድጓል፡፡
በአሰልጣኝ አዲሴ ካሳ እየተመሩ ባለፈው ቅዳሜ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን የጀመሩት ሀዋሳ ከተማዎች ስድስት አዳዲስ ተጫዋቾችን በማስፈረም እና የስድስት ነባር ተጫዋቾችን ውል በማራዘም ነበር ወደ ዝግጅት የገቡት። ክለቡ በ2011 ሚያዝያ ወር ላይ አጥቂዎቹ መስፍን ታፈሰ እና ምንተስኖት እንድሪያስን እንዲሁም በአሁኑ ሰዓት በዩጋንዳው የሴካፋ ውድድር ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አባል የሆነው ግብ ጠባቂው ምንተስኖት ጊንቦን ከተስፋ ቡድኑ ማሳደጋቸው የሚታወስ ሲሆን ለዘንድሮው የውድድር ዘመን ደግሞ ከ20 አመት በታች ቡድኑ አምስት ተጫዋቾች ወደ ዋናው ቡድን አሳድጓል፡፡
በአሁኑ ሰአት በሴካፋ ከ20 አመት በታች ውድድር ላይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ተካተው እየተጫወቱ የሚገኙት አጥቂው ሀብታሙ መኮንን እና የመሐል ተከላካዩ ፀጋአብ ዮሀንስ እንዲሁም ባለፈው ዓመት በታንዛኒያ የሴካፋ ውድድር ላይ ከ17 ዓመት በታች ቡድን አባል የነበረው አማካዩ ወንድማገኝ ኃይሉ፣ አጥቂው ተባረክ ኢፋሞ እና ተከላካዩ ሚኪያስ ታምራት ወደ ዋናው ሀዋሳ ከተማ ቡድን ውስጥ ያደጉ ተጫዋቾች ሆነዋል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ