የሀዋሳ ከተማው ተጫዋች በቅርቡ ለሙከራ ወደ አውሮፓ ያመራል

ከሀዋሳ ከተማ ታዳጊ ቡድን የተገኘው እና ባለፈው ዓመት በሴካፋ ከ17 ዓመት ዋንጫ ላይ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ በመባል የተሸለመው አጥቂው ምንተስኖት እንድሪያስ በኅዳር ወር አጋማሽ ለሙከራ ወደ ሜቄዶኒያ ይጓዛል፡፡

እንደ ተጫዋቹ ወኪል ጋሮ ገረመው ገለፃ ከሆነ ከተመሰረተ አስራ ስድስት ዓመታትን ያስቆጠረው የሜቄዶኒያ የመጀመሪያ ሊግ ተካፋዩ ኤፍኬ ሪኖቫ ክለብ ምንስኖት ሙከራ የሚያሳልፍበት ክለብ ነው። በሜቄዶኒያ ሊግ 2009/10 የዋንጫ ባለቤት የሆነው እና በ2011/12 ደግሞ የሀገሪቱን የጥሎ ማለፍ ዋንጫ አንስቶ የነበረው ይህ ክለብ የተጫዋቹን የትራንስፖርትም ሆነ የቆይታ ጊዜውን ሙሉ ወጪ በመሸፈን በህዳር ወር አጋማሽ ለሙከራ ይዞት እንደሚጓዝ ወኪሉ ጨምሮ ገልጿል፡፡

የክለብ የእግር ኳስ ህይወትን በሀዋሳ ከተማ ከ17 ዓመት በታች ቡድን የጀመረው ምንተስኖት በ2011 የውድድር ዘመን ከ20 ዓመት በታች የሀዋሳ ከተማ ቡድን ውስጥ በመጫወት ጥሩ የውድድር ዓመትን በማሳለፉ ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ በአሰልጣኝ አዲሴ ካሳ የሀዋሳ ከተማ ዋናው ቡድን ውስጥ ያደገ ሲሆን በአሁኑ ሰዓትም በክለቡ ስብስብ ውስጥ ይገኛል፡፡ በ2010 በኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ተካቶ ታንዛኒያ ላይ በነበረው የሴካፋ ውድድር ላይ ስምንት ግቦችን በማስቆጠር የውድድሩ ኮከብ ግብ አግቢ ከመሆኑ በዘለለ ኢትዮጵያ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ እንድታጠናቅቅ ማስቻሉ ይታወሳል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ