ኢንቨርቲንግ ዘ ፒራሚድ| ምዕራፍ ስምንት – ክፍል ሁለት

የጆናታን ዊልሰን Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የአማርኛ ትርጉም በግሩም አተራረክ ሰባት ምዕራፎች አልፈን ወደ ስምንተኛው ተሸጋግረናል። በዛሬው መሠናዶም የምዕራፉ ሁለተኛ ክፍል ይቀርባል


በእንግሊዝ እጅግ ስኬታማው የእግርኳስ አጨዋወት ዘይቤ ሥር-ነቀልተኝነት (Radicalism) የታየው በ1912 ፒተር ማክዊሊያም የተባለውን አሰልጣኝ በቀጠረው ቶተንሃም ሆትስፐር ነበር፡፡ ምንም እንኳ በዚህ ዘመን አሰልጣኙን የሚያነሳ ቢጠፋም ተጽዕኖው በቸልታ የሚታለፍና በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ እርሱ በእግርኳሱ ቀደምት የእድገት ደረጃዎች ላይ ያሳረፈው አዎንታዊ አሻራ ልዩና ዘርፈ-ብዙ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ማክዊሊያም የስኮትላንዶቹን በቅብብሎች ላይ የተመሰረተ አጨዋወት (Passing Game) የተማረው በኒውካስል ተለምዷዊ የመስመር አማካይ (Wing-Half) ሆኖ እየተጫወተ ሳለ ነበር፡፡ ያኔ ኩዊንስ ፓርክን ለቆ ማግፓይሶችን የተቀላቀለው ቦብ ማኮል ይህን የእግርኳስ አቀራረብ ሥልት ለማክዊሊያም በማሳወቅ ረገድ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ስኮትላንዳዊው ፒተር ማክዊሊያም የቶተንሃምን የአሰልጣኝነት ኃላፊነት ሲረከብ በተጫዋችነት ዘመኑ ከሌላኛው የሃገሩ ልጅ የቀሰመውን በኳስ ቁጥጥር ላይ ያተኮረ የቅብብል ሒደት የሚያመዝንበት የጨዋታ ሥርዓት መተግበር ዋነኛ ግቡ እንዲሆን ወሰነ፡፡ አሰልጣኙ በአዲሱ ክለቡ ለሚከተለው የጨዋታ ሥልት የመርሆዎቹ ዓቢይ ትልም በዚሁ የስኮትላንዶቹ አጫጭር የኳስ ቅብብል ዙሪያ አጠነጠነ፡፡ ከዚህም አልፎ በትምሕርት ቤቶች ውስጥ እግርኳስ መጫወት ለሚያዘወትሩ ልጆች የቅብብሎች ጨዋታን ማስተማር ብቁና ተተኪ ታዳጊዎች የማፍራት እቅዱን የተሳካ እንደሚያደርገው በማሰብ በኬንት የሊግ ውድድር የሚሳተፍ ኖርዝፍሊት ዩናይትድ የተባለ ቡድን አቋቋመ፡፡ ይህኛው የታዳጊዎች ቡድን ለስፐርሶች እንደ መጋቢ ክለብ ሆኖ እንዲያገለግል ተወሰነ፡፡ እንግዲህ ድርጊቱ ከዚያ ጊዜ በፊት ታይቶ ቢታወቅ እንኳ በሃገሪቱ እግርኳስ ግን እንግዳ ክስተት ነበር፡፡ ” በዋነኝነት ተጫዋቾቹ መልካም ባህርይ እንዲላበሱ እናሰለጥናቸዋለን፤ እኔ ታዳጊዎቹን ዘወትር የምነግራቸው ኳሷን እንደ ምርጥ ጓደኛቸው እንዲንከባከቧት ነው፡፡ በጨዋታ ወቅትም ቢሆን ኳስ ሲቀባበሉ በጥንቃቄ እና በትኩረት እንዲሆን አበክሬ አስረዳቸዋለሁ፡፡ በቶተንሃም የእግርኳስ አቀራረብ ባህል ኳሷን በዘፈቀደ መጠለዝ ተቀባይነት እንደሌለው አሳውቃቸዋለሁ፡፡” ይላል ማክዊሊያን ስለ ታዳጊዎቹ የኳስ ቅብብል ሥልጠና ሲያወጋ፡፡

የማክዊሊያን እግርኳሳዊ እሳቤዎች ተራማጅነቱን ቢያሳዩም አሰልጣኙ በተቃራኒው ባህላዊ የጨዋታ አቀራረብ እና የተጫዋቾች አያያዝን ይከተል ነበር፡፡ ” ፒተር ማናችንንም ተለሳልሶ ቀርቦን አያውቅም፤ እርሱ ለዘብተኛነት ባህርዩ አልነበረም፡፡ በጎርናና የስኮትላንዶች የንግግር ዘዬ ‘አካፋን-አካፋ!’ በማለት የሚያምን ፊትለፊት ተናጋሪ ሰው ነበር፡፡ አንድ ተጫዋች ካበሳጨው ፍጹም ከመናገር ወደኋላ አይልም፡፡ ሁላችንንም “ልጆች!” እያለ የሚጠራበት
ሁኔታን መቼም ልረሳው አልችልም፡፡ እኛ ማሸነፍ እንዳለብን የሚያምነውን ጨዋታ ባጋጣሚ ከተረታን እርሱ ወደ መልበሻ ክፍል ሲመጣ አንዳንድ ወጣት ተጫዋቾች ይይዙት ይጨብጡት ያጡ ነበር፡፡” ይላል የስፐርሶች የመስመር አማካይ የነበረው ሮን በርገስ ስለማክዊሊያን ባህርይ ሲያብራራ፡፡

ሮን በርገስ ግለታሪኩን በሚተርክበት መጽሃፉ በኮቬንትሪ ከተጠባባቂ ቡድኑ ጋር ያደረገውን ጨዋታ እንደማይረሳ ይጠቅሳል፡፡ በግጥሚያው በርገስ በአማካይነት ሜዳውን ሙሉ ሲያካልል ዋለና በፈታኙና አድካሚው ፍልሚያ እጅጉን ተዳከመ፡፡ ጨዋታው ተጠናቆ በመልበሻ ክፍል ውስጥ ትጥቁን ሲቀይር ሰንበር በሰንበር የሆነና የበለዘ ቆዳውን እንዲሁም የዛለ ሰውነቱን ከጥፍሩ እስከ ጸጉሩ የተመለከተው ማክዊሊያም ተጫዋቹን ” ዛሬ ደም ሰጥተሃል- ጀግናው! ይህ እንቅስቃሴህ ምናልባትም ወደፊት ኳሷን የሙጥኝ ብለሃት እንዳትባክን ያስተምርህ ይሆናል፡፡” ሲል ነገረው፡፡ በርገስ የሰማው ነገር ገርሞታል፤ ይሁን እንጂ አዛኝነት የማይሰማው ማክዊሊያም የሰጠው አስተያየት ትክክል እንደነበረ ተሰምቶታል፡፡ ” አላስፈላጊ በሆነ ሁኔታ ከተገቢው በላይ ኳሷን እግሬ ሥር ይዤ ጥቅጥቅ ያለ የተጋጣሚ ተከላካይ ክፍል ለማስከፈት የማደርገው ጥረት ከንቱ ነበር፡፡ ይህ የራሴ ጥፋት ቢሆንም ጥሩ አግዞኛል፤ በአስቸጋሪ መንገድም ትምህርት ሰጥቶኝ አልፏል፡፡ የተፋፋቁት የሰውነቴ ክፍሎች ህመም ቢተዉብኝም ድጋሚ ጥፋት እንዳልሰራ አንቅተውኛል፤ ከዚህ አንጻር ‘እንኳንም ተከሰቱብኝ’ እንድል አድርጎኛል፡፡” ብሏል በርገስ በትውስታው፡፡
በ1927 ማክዊሊያም ስፐርስን ለቆ ሚድልስብራን ተቀላቀለ፡፡ በዓመት አንድ ሺህ አምስት መቶ ፓውንድ የሚያገኝበትን የደመወዝ ስምምነትም ተፈራረመ፡፡ ነገርግን ወደ ሰሜን ምስራቅ እንግሊዝ አምርቶ ምቾት ተሰምቶት ሊሰራ እንደማይችል ይገመት ነበር፡፡ እንደታሰበውም እዚያ ተደላድሎ ሊቀመጥ አልቻለም፡፡ በ1934 ወደ ለንደን ተመለሰ፤ የአርሰናል ክለብ ዋና የተጫዋቾች መልማይ ሆኖ ተሾመ፡፡ በ1938 ደግሞ በኋይት ኸርት ሌን የቶተንሃም አሰልጣኝነትን ሹመት ተቀበለ፡፡ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከመጀመሩ በፊት በነበሩት የመጨረሻ ዓመታት ማክዊሊያም በሚመራው የቶተንሃም ቡድን ውስጥ ወደፊት በአህጉሪቱ እግርኳስ በአሰልጣኝነቱ መሥክ ታላቅ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ ሶስት ተጫዋቾች ተገኙ፡፡ ሁለቱ በዚያው በቶተንሃም የሰሩት አርቱር ሮው እና ቢል ኒኮልሰን ሲሆኑ ሌላኛው በአያክስና ባርሴሎና የእግርኳስ ታሪክ ቀዳሚ አሻራውን ያሳረፈው ቪክ በኪንግንግሃም ነበር፡፡
ሮው ለስፐርስ ወደኋላ በጥልቀት ባፈገፈገ የመሃል-ተከላካይ አማካይነት (Deep-Lying Centre-Half) ሚና ይጫወት የነበረ ቢሆንም ከኸርቢ ሮበርትስ እና የእርሱን ሚና ከወረሱ ሌሎች ተጫዋቾች በላቀ የሁለገብነት ባህሪን አሳይቷል፡፡ በጨዋታ ወቅት ሮው ኳስን በቁጥጥር ሥር በማድረግ የተሳኩ ቅብብሎችን መከወን እስከሚችል ድረስ ይጠብቃል፤ ዝም ብሎ ያለ ዓላማ ኳስ ወደፊት መጠለዝን ፈጽሞ አይወድም ነበር፡፡ አርቱር ሮው በማክዊሊያን አበረታችነት ሁሌም አዕምሮውን ይበልጥ የሚጠቀም አርቆ አሳቢ እና ሃሳቦቹንም በተግባር ለማሳየት የሚጥር ብልህ ተጫዋች ሆኖ ጎልብቷል፡፡ በ1949 የእግርኳስ ትምህርት ለማስተማር ወደ ሃንጋሪ አቅንቶ በበርከታ ቦታዎች በተለያዩ የአጨዋወት ዘይቤዎች ላይ ገለጻዎችን አድርጓል፤ ሰፊ ማብራሪያዎችንም ሰጥቷል፡፡ በሮው ዘመናዊ የእግርኳስ ግንዛቤ የተደመሙት የሃገሪቱ የስፖርት ኃላፊዎች በሄልሲንኪ ለሚካሄደው የ1940 የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ሃንጋሪን እንዲያዘጋጅም ጋብዘውት ነበር፡፡ ለብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኞች በአማካሪነት እንዲሰራም ጠይቀውታል፡፡ በወቅቱ ለሃንጋሪያውያኑ የእግርኳስ ማኅበር በተደራዳሪነትና ጉዳይ አስፈጻሚነት ሲያገለግል የነበረው የ<ኔምዜቲ ስፖርት> መጽሄት አዘጋጅ ላስዝሎ ፌሌኪ ይህን ጉዳይ በሚመለከት ለእንግሊዝ እግርኳስ ማህበር ደብዳቤ ጻፈ፡፡ እቅዳቸው ሮው ለሃንጋሪያውያን አዲስ የእግርኳስ አጨዋወት መሰረት እንዲጥል የእንግሊዞች እገዛ አስፈላጊ መሆኑን ማሳወቅ እንደሆነም ገለጸላቸው፡፡ በእርግጥ ያለ እንግሊዛውያኑም እርዳታ የሃንጋሪዎች እግርኳስ እያደገ የነበረ መሆኑ የማይታበል ሃቅ ነው፡፡ ይሁንና እስከዚያ ጊዜ ድረስ ጂሚ ሆጋንን የመሰለ ታላቅ የእግርኳስ ምሁር ላበረከተችው ሃገር የነበራቸው ክብር ከሃንጋሪዎች ዘንድ ጨርሶ አልጠፋም፡፡ የሮው ዘመነኛ የጨዋታ እሳቤዎች በጊዜው በቡና መጠጫ ቤቶች በነበሩት የአጨዋወት ዘይቤ ተወያዮች ቦታ አገኘ፤ በዚህም ምክንያት የእውቀትና ልምድ መጋራት ለመፍጠር ፍላጎት አደረባቸው፤ ስለዚህም ሮውን ፈለጉት፡፡
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተጀመረና ሮው የሃንጋሪዎችን ግብዣ ሳይቀበል ቀረ፤ ወደ ሃገሩ ተመልሶ የእንግሊዝን የመከላከያ ቡድን ማሰልጠን ጀመረ፡፡ ከቼልምስፎርድ ሲቲ ጋርም የሊግ ዋንጫ አሸነፈ፡፡ በ1949 በሁለተኛ ዲቪዚዮን የሚወዳደረው ቶተንሃም የአሰልጣኝ ጆ ኸልም ምትክ አድርጎ ቀጠረው፡፡ ሳይውል ሳያድር እርሱ የሚያሰለጥነው ቡድን እግርኳስን በምን መልኩ መጫወት እንዳለበት የሚያሳይ ትንታኔውን ያብራራ ጀመር፡፡ ያኔ ቶተንሃምን በአምበልነት የሚመራው በርገስ ግለታሪኩ ላይ ባሰፈረው ጽሁፍ ” ለልምምድ በተሰባሰብንበት ወቅት ሮው የእርሱን አዲስ የአጨዋወት ሥርዓት አስረዳን፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ በመልበሻ ክፍል ውስጥ በአጠቃላዩ የቡድኑ ዕቅድ ላይ እንድንወያይ አደረገን፤ የሮውን የእግርኳስ ሃሳቦች በአንክሮ መከታተል ያዝን፤ አንዳንዶቹ ተጫዋቾች ፊት ላይ የጥርጣሬ ምልክት አይቻለሁ፡፡” ይላል አምበሉ፡፡ በርገስ ስለ ሮው ይቀጥላል፡፡ ” ልምምዳችንን ለአስራ አምስት ቀናት እንደሰራን እርሱ የአዲሱን ስልት ውጤታማነት በውድድሮች ላይ በተግባር ለማየት ጓጓ፡፡”
በርገስ የአርቱር ሮው የእግርኳስ ጨዋታ ዘዴ ያልተለመደ መሆኑ ቢገለጥለትም አጨዋወቱ ከምን ይዘት አንጻር የተለየ ስለመሆኑ ግን እርግጠኛ አልነበረም፡፡ ሮው በቡዳፔስት በነበረው ቆይታ ባየው የእግርኳስ አጨዋወት ተማርኮ ጦርነቱ ከመታወጁ በፊት ማክዊሊያም የወጠነውን እዳር እንዳደረሰለት በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ በአንድ በኩል በርገስ ታክቲካዊ እድገቶቹን ” ሙሉ በሙሉ መሻሻል የተደረገባቸው! ” ሲል ይሰይማቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ” ከቀደመው አጨዋወት አንጻር ምንም ዓይነት ተመሳስሎ ባይታይባቸውም በትክክል አዲስ የሆነ ይዘት አልነበራቸውም፡፡” ብሎ ይሞግታል፡፡ ” የእኛ አጨዋወት ዘይቤ ከዘመናዊው የአህጉራችን እግርኳስ ስልት የተቀዳ ነው፡፡ ከአስራ አምስት እስከ ሃያ ሜትሮች ርቀት ላይ በሚደረጉ አጫጭር ቅብብሎች ላይ የተመሰረተ ነበር፡፡ እያንዳንዱ ተጫዋችም ከዚህ ርቀት በላይ ኳሷን መለጋት አይጠበቅበትም፡፡” ሲል ጽፏል፡፡
የሮው እግርኳሳዊ ራዕይ አልፍ ራምሴይን የመሰለ ተጫዋች ለመፍጠር አብቅቶታል፡፡ ራምሴይ በሳውዛምፕተን በቀኝ መስመር ተከላካይነት የሚሰለፍና ባልተለመደ መልኩ ለማጥቃት ሲል የተጋጣሚ ሜዳ ድረስ የሚሄድ ፈጣን ተጫዋች (Attacking Right-Back) ነበር፡፡ ሮው በቀዳሚነት ይህን ተጫዋች ለቶተንሃም ሆትስፐር አስፈረመው፡፡ <ኤንድ ዘ ስፐርስ ጎ ማርቺንግ ኦን> ላይ ሮው ተከላካዩ ለማጥቃት በሚያሳየው ብርቱ ፍላጎትና ፈቃድ ይገረም እንደነበር ይገልጻል፡፡ ተጫዋቹ በረጅሙ ወደፊት በሚላኩ ኳሶች ላይ በጣም ጥገኛ እንዳይሆንም ይመክረው ነበር፡፡ ” በወቅቱ ራምሴይ ልኬታቸውን የጠበቁ ቅብብሎች መከወን እጅግ ወሳኝ ተግባር እንደሆነ ተገንዝቧል፤ እርሱ ከ14ሜ.-18 ሜ. በሚደርስ ርቀት ውስጥ ሆኖ ከፊት መስመሩ በቀኝ በኩል ጥቂት ወደኋላ ለተሳበው (Withdrawan Outside-Right) ሶኒ ዋልተርስ የተመጠኑ ኳሶች ሲልክለት ያልተቋረጠ የቅብብሎች ሒደት ይፈጠራል፡፡ የተጋጣሚ ግራ መስመር ተከላካይ (Left-Back) ወደ ስፐርስ የሜዳ ግማሽ እየመጣ ዋልተርስን ለመከታተል ያመነታል፤ ያኔ የመስመር ተከላካዮች ይህን ክልል የድንበር ያህል ይቆጥሩት ነበር፡፡ በዚህ መልኩ ዋልተርስ እንዳሻው የሚንቀሳቀስበት ሰፊ የሆነ ክፍት ቦታ ያገኛል፡፡ ስለዚህ ራምሴይ ወደላይ ተጠግቶ ራሱን ዝግጁ ካደረገ ዋልተርስ ኳስ ሊያቀብለው የሚያስችለው የቦታና ጊዜ ነጻነት ያገኛል ማለት ነው፡፡” ይላል ሮው የቅርብ-ርቀት ቅብብሎችን ፋይዳ በተመለከተ ሲያርረዳ፡፡
በብሪታኒያ ስፐርሶች ከሁሉ በተለየ መልኩ የተደራጀ ቅብብልን ያካተተ ከኋላ ተመስርቶ የሚጀመር አጨዋወት መተግበር አሰቡ፡፡ ራምሴይም ወደፊት እንደፈለገ የመሄድ ነጻነት ተሰጠው፡፡ ” በማጥቃት ሒደቱ ተከላካይም ቢሆን በሜዳው ቁመት ወደፊት መሄድ የሚጠበቅበት ቦታ ገደብ አልነበረውም፤ በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ ክልል እየሄድኩ ተሻጋሪ ቅብብሎችን ስፈጽም አልያም የግብ ሙከራ ሳደርግ ምናልባት አስተውላችሁ ይሆናል፡፡ ‘አንድ ተከላካይ የጎል ሙከራዎችን ማድረግ አይጠበቅበትም፡፡’ በሚለው ሃሳብ ፍጹም አልስማማም፡፡” ይላል አልፍ ራምሴይ፡፡ የቀኝ መስመር ተከላካዩ (ራምሴይ) ይህን የሚያደርገው ከጎኑ የሚሰለፈው አይበገሬውና ቀጥተኛ ተናጋሪው የመሃል ተከላካይ (Centre-Half) ቢል ኒኮልሰን ስለነበረለትም ነው፡፡ ኒኮልሰን ራምሴይ ትቶት የሚሄደውን ክፍተት እየሸፈነለት ጥሩ ከለላ ያደርግለታል፡፡
ይህ እንግዲህ ከጊዜያት በኋላ ኳሷን አቀብሎ-ወደ ተቃራኒ የሜዳ ክፍል በፍጥነት በመሮጥ አጫጭር ኳሶችን በመጠበቅ የሚታወቀውን የአጨዋወት ሥርዓት (Push-and-Run) ፈጠረ፡፡ ይሁን እንጂ ሥልቱን ተግባር ላየይ ለማዋል የሚባለውን ያህል ቀላል አልነበረም፡፡ ” በአዲሱ የጨዋታ ሒደት በረጅም ርቀት በሚደረጉ ቅብብሎች (Long-Kicking Tactics) ላይ የመስመር አማካዮች በመደበኛነት ከሚሰለፉበት አመዛኙ ቦታቸው በመጠኑ ወደኋላ ተመልሰው መጫወት ተጠበቀባቸው፡፡ በዚህም ሳቢያ ይበልጡን የጨዋታው አካል እየሆኑ ሄዱ፡፡ ከመሃል አጥቂው ግራና ቀኝ ከሚቆሙት የፊት መስመር ተሰላፊዎች (Inside-Forwards) ጋር የሚያደርጉት የቦታ ቅይይርም ሌላ የሥልቱ ትሩፋት ሆነ፡፡” ሲል በርገስ ያስረዳል፡፡ ከነባሩ አቀራረብ አንጻር የበርገስ የመስመር አማካይነት ሚና (Half-Back) ላይም መጠነኛ ሽግሽግ ተደረገ፡፡ ” እኔ ከመሃለኛው የሜዳ ክፍል እየተነሳሁ የማጠቃበትን ኃላፊነት (Attacking Half-Back) እርግፍ አድርጌ ተውኩ፤ ቢል ኒኮልሰንና እኔ ከመስመር ተከላካዮች በአጭር ርቀት ኳስ እየተቀበልን ወደፊት ለአጥቂዎቹ አልያም ለመስመር አማካዮቹ የምንልክበት ቦታ ላይ መገኘት ግድ ሆነብን፡፡” በማለት ሮው በጨዋታ ወቅት የሚጠብቅበትን ሥራ ይዘረዝራል፡፡
ኳስን ተቀብሎ መልሶ በማቀበል- እንደገና ደግሞ ለመቀበል ትክክለኛና ነጻ ቦታ ላይ በመገኘት የሚደረገው የስፐርሶች የጨዋታ ዘዴ የቡድን አጋሮችን በተጋጣሚ የሜዳ ክልል ባሉ ክፍት ቦታዎች ውስጥ ከማግኘት (Finding men in spaces) እና በራስ ጥረት ክፍተቶችን እየፈጠሩ ጥቅም ላይ ከማዋል ሒደት (Creation and manipulation of spaces) ጋር የሚስተካከል ሥልት አልነበረም፡፡ ” ያኔ ብዙ ነገሮችን ቀይረናል፤ ሆን ብለን ኳስ በተጋጣሚ ቡድን ተጫዋች ቁጥጥር ሥር ላለ የቡድን አጋራችን እንሰጥና ሌሎቻችን ነጻ ሆነን ኳሱን ለያዘው ተጫዋች ተጨማሪ የመቀባበያ አማራጭ አቅጣጫ ለመፍጠር እንጥራለን፡፡ ይህ አይነቱ እንቅስቃሴያችን ኳስን በምን መንገድ መቀበልና መስጠት እንዳለብን አሳወቀን፤ ስንቀባበል ሁላችንም ኳስ የምንሰጠው ተጫዋች ጋር መድረሷን እርግጠኛ መሆን ተጠበቀብን፡፡” በማለት የዚያኔው የቡድኑ የመስመር አጥቂ (Inside-Forward) እና በኋላም የቢል ኒኮልሰን ረዳት የሆነው ኤዲ ቤይሊ በ1982 የቶተንሃምን ክለብ ታሪክ ለጻፈው ፊል ሶለር አብራርቶለታል፡፡ በወቅቱ በመደበኛነት ኳስን ከአደጋ ክልል የማራቅ እና የተጋጣሚን የማጥቃት አቅጣጫ የማስቀየር ኃላፊነት በሚወጣ አንድ ተከላካይ ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበት ማንኛውም የባላጋራ ቡድን ተጫዋች እምብዛም ሲቸገር አልተስተዋለም፡፡ አርቱር ሮው ይህን በማስመልከት በሰጠው አስተያየት ” ጎበዞቹ ተጫዋቾች ከኳሷ ጋር እኩል ይከንፋሉ፤ ሰነፎቹ ደግሞ ከኳሷ ጀርባ ይሮጣሉ፡፡” ብሏል፡፡
በ1949-50 የውድድር ዘመን ስፐርሶች ወደ አንደኛ ዲቪዚዮን አደጉ፡፡ በዚህኛው የሊግ እርከን በደረጃ ሰንጠረዡ በሶስተኝነት የሚገኘውን ሰንደርላንድ በእግርኳስ ማህበሩ ዋንጫ አራተኛ ዙር ላይ አገኙትና 5-0 ረቱት፡፡ ይሁን እንጂ በዚሁ ውድድር አምስተኛ ዙር በኤቨርተን የደረሰባቸው ሽንፈት በትልቁ ዲቪዚዮን ተፎካካሪ ለመሆን የአጨዋወት ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋቸው እንደሆነ ጥያቄ ጫረ፡፡ ሮው ግን በያዙት የአጨዋወት ሥልት መቀጠል እንዳለባቸውም አመነ፤ በግትር አቋሙም ጸና፡፡ “በ1925 የጥንቱ የ<ጨዋታ-ውጭ ህግ> ከተቀየረ በኋላ ፣ ምንም እንኳ እጅግ ስኬታማ የነበሩ ቢሆንም አርሰናሎች አዲሱን የጨዋታ ዘዴ ካስተዋወቁበት ጊዜ አንስቶ አዕምሮዬ የእግርኳሱን ለውጦች በአሉታዊ ገጽታቸው ቃኝቷል፡፡ በእርግጥ በመድፈኞቹ ሥልት ምንም አይነት ችግር አልተስተዋለም፤ የእነርሱን መንገድ በስኬታማነት ለመከተል ግን ለዚያ አጨዋወት አመቺ የሆኑና ለዚያ የእግርኳስ ስልት የተሰሩ ተጫዋቾች ያስፈልጉሃል፡፡ እነዚያን ተጫዋቾች ካልያዝክ ግን የአጨዋወት ሥርዓትህ ፍሬያማ አይሆንም፡፡ ያኔ’ኮ ብዙ ክለቦች የአርሰናሎችን ዘዴ ሊኮርጁ ሞክረዋል፤ ተገቢውን ተጫዋቾች ሳይዙ በመሆኑ ሊሳካላቸው አልቻለም እንጂ፡፡ መጨረሻ ላይ ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲያ ዓይነት ነገር ነው የሆነው፡፡ የእኛ ዘዴ ግን የተሻለ የነበረ ይመስለኛል፤ እኛ ‘ቡድን ከግለሰብም በላይ ነው፡፡’ የሚለው እውነታ ላይ ጥሩ መረዳት አዳብረናል፤ በዚህ እሳቤ ተጫዋቾች በተናጠል የተሻለ ተጠቃሚ የሚሆኑበትም አግባብ እንዳለ ተገንዝበናል፡፡” ይላል ሮው፡፡
ስፐርሶች ትልቁን ሊግ መልሰው በተቀላቀሉበት በ1950-51 የውድድር ዘመን አስገራሚ ብቃት ነበራቸው፡፡ በህዳር ወር ኒውካስልን 7-0 ከረመረሙ በኋላ <ቴሌግራፍ> ጋዜጣ ይህን ጽሁፍ ይዞ ወጣ፡፡ ” የቶተንሃሞች የጨዋታ ዘዴ ቀላል ነው፡፡ የስፐርሶች መርህ በአጭሩ ኳሱን ለትንሽ ጊዜ በቁጥጥር ሥር አድርገው መሬት ላይ እየተቀባበሉ ክፍተት ሲገኝና በዚያ ቦታ ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ የቡድን አጋሮች ሲደርሱ ማቀበል ነው፡፡ የማጥቃት አካሄዳቸው በቀኙ መስመር ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ በዚህ የሜዳ ክፍል እያንዳንዱ ተጫዋች ሩቅ ወደሆነ የባህር ዳርቻ እንደሚነጉድ ማዕበል ኳስን በፍጥነት ይዞ መክነፍ ሥራው አድርጎታል፡፡ ይህ ሁሉ ቅብብል የሚከወነው በጎነ ሶስት እና ጎነ አራት ምስል በሚወከሉ የሜዳ ክፍሎች ላይ በሚንቀሳቀሱ ተጫዋቾች የሶስትዮሽና አራትዮሽ ጥምረት ነው፡፡ እናም ጥምረቱ በፍጥነት ተሳክቶ ልክ እንደ ቅዳሜው አይነት መሆን ከጀመረ እያንዳንዱ ቅብብል በረጠበ መጫወቻ ላይ እንኳ የተሳካ ይሆናል፡፡ ይህን የሚቋቋም ተከላካይም ሊኖር አይችልም፡፡”
ቶተንሃሞች በዚሁ አጨዋወት የሊጉን ዋንጫ በአራት ነጥቦች ልዩነት አሸነፉ፤ በዚህም የሁለተኛና የአንደኛ ዲቪዚዮን ዋንጫን በተከታታይ የውድድር ዓመታት ካሸነፉ ሶስት ቡድኖች መካከል እነርሱ ሶስተኞቹ ሆኑ፡፡ ተከታታዩ ውጤታማነታቸው የአጨዋወት ዘይቤያቸው ሙሉበሙሉ ለውጥ የተደረገበት መሆኑን አሳየ፡፡ <ቶተንሃም ዊክሊ ሄራልድ> ጋዜጣ ላይ አንድ ዓምደኛ ” አዲሱ የእግርኳስ ጨዋታ አቀራረባቸው ስፐርሶችን ያለ ጥርጣሬ የበላይ እያደረጋቸው እንዳለ አረጋግጠዋል፡፡ የዚህ ዘይቤ ትክክለኛ አጠቃቀም በእንግሊዝ እግርኳስ ላይ አብዮት እንደሚፈጥር እገምታለሁ፡፡ ከዚህ ቀደም የሃገሪቱ ክለቦች ሶስተኛውን የመሃል ተከላካይ (Third-Back) የሚጠቀመውን ታክቲክ ለመገዳደር የሚያገለግል ሥርዓት እንደፈጠሩ ሁሉ የስፐርሶችን ሥልት ለመቋቋምም አዳዲስ እቅዶችን መንደፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዚህ እጅግ አበረታች የእግርኳስ ጨዋታ አቀራረብ ዕድገት ለቶተንሃም አሰልጣኝ ዕውቅና ሊሰጥ ይገባል፡፡ እርሱ በክለቡ በቆየባቸው ጥቂት ጊዜያት ደረጃውን የጠበቀ እግርኳስ በምን መልኩ እንደሚተገበር በማሳየት ውጤታማ ሆኗል፡፡ በእግርኳሱ አጨዋወት መሰረታዊና ነባራዊ እውነታ ላይ ተመርኩዞ እግርኳስ የቡድን ሥራ መሆኑንና ከቡድን ሥራ ደግሞ ውጤት ሊገኝ እንደሚችል አስመስክሯል፡፡” ሲል ጽፏል፡፡
አርቱር ሮው እድሜያቸው በገፉ ተጫዋቾች ላይ ለረጅም ጊዜ ሙጥኝ ማለቱ ዋጋ አስከፍሎታል፡፡ ባለድል ከሆኑበት ዓመት በኋላ የቡድኑ ውጤት ማሽቆልቆል ጀመረና በሊጉ ሁለተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀቁ፡፡ ሮው ይህን የቡድን ችግር ለመቅረፍ ብዙ ታገለ፡፡ በጥር-1954 የነርቭ መታወክ ገጠመው፤ በዚህ ሳቢያ የአዕምሮ ሁከት ያሰቃየው ጀመር፡፡ እርሱ ግን ከጥቂት ዕረፍት በኋላ በክረምቱ ወደ ሥራው ተመለሰ፡፡ በእንግሊዝ እግርኳስ ማህበር ዋንጫ በአምስተኛ ዙር ቡድኑ በዮርክ ሲቲ ተረታ፡፡ የሮው ጤናም መሻሻል አላሳይ አለ፤ በ1955 በሆስፒታል የህክምና ክትትል ማድረግ ጀመረ፡፡ ከዚያ በኋላ በድጋሚ ወደ ሜዳ አልተመለሰም፤ ወደ ኋይት ኸርት ሌንም ብቅ አላለም፡፡ በዚያው ዓመት ሐምሌ ላይ ራሱን ከአሰልጣኝነት አገለለ፡፡ የእርሱ ምክትል የነበረው ጄሚ አዳምሰን ቢል ኒኮልሰንን በረዳትነት ይዞ የዋና አሰልጣኝነቱን መንበር ተረከበ፡፡ ክለቡ አንዴ የእግርኳስ አጨዋወት መሰረቱ ስለተጣለለት በ1961 ቢል ኒኮልሰን ቡድኑን እየመራ የሊጉንና የማህበሩን ዋንጫ አሳካ፡፡ ይሄኔም ቶተንሃሞች አጨዋወታቸው አልተቀየረም ነበር- Push-And-Run መገለጫቸው ሆኗልና፡፡

ይቀጥላል...


ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡ ባለፉት አስራ ሦስት ዓመታትም አስር መፅሐፍትን ለህትመት አብቅቷል፡፡