የአዳማ ከተማው ፈጣን የመስመር ተጫዋች ዱላ ሙላቱ ለሙከራ ወደ ዱባይ አምርቷል።
ባለፈው ዓመት ከአዳማ ከተማ ጋር ቆይታ ያደረገው ዱላ ሙላቱ በቱርክ እና ቆጵሮስ ክለቦች የሙከራ ዕድል አግኝቷል። ለተጫዋቹ የሙከራ ዕድል ያመቻቸለት ሰርነስ ሶከር ኤጀንሲ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፀው ተጫዋቹ የሚያመራው ወደ ተባበሩት ዓረብ ኤሜሬትስ ሲሆን በሃገሪቱ ዝግጅታቸውን በሚያደርጉ የቱርክ እና የቆጵሮስ ቡድኖች ሙከራ እንደሚያደርግም ገልጿል።
ተጫዋቹ ወደ ስፍራው ያቀናው በመልማዮች በኩል እንደሆነ ገልፀው በዱባይ ቆይታው በበርካታ ቡድኖች የሙከራ እድል እንደሚገጥመው የገለፁት አቶ ሳምሶን ነስሮ ተመሳሳይ ጥሩ ብቃት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች በአውሮፓ እና ሌሎች አህጉር ክለቦች ዕድል እንዲያገኙ በመስራት ላይ እንዳሉ ገልፀዋል።
በሃድያ ሆሳዕና፣ መቐለ 70 እንደርታ፣ ደቡብ ፖሊስ እና አዳማ ከተማ መጫወት የቻለው ይህ የመስመር አማካይ በአሁኑ ሰዓት በዱባይ የሚገኝ ሲሆን ከቀጣይ ቀናት ጀምሮም በክለቦች ሙከራ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
© ሶከር ኢትዮጵያ