ከሁለት ወራት ገደማ የተመሰረተው የትግራይ አሰልጣኞች ማሕበር ዛሬ ጠዋት በድምፂ ወያነ ትግራይ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል።
በሚካኤል አምሀ፣ ዳንኤል ተስፋይ እና በቀድሞ የመቐለ አዳማ እና ደደቢት ተጫዋች ግርማይ ምሩፅ መሪነት የተካሄደው ይህ ጋዜጣዊ መግለጫ በርካታ ሃሳቦች የተነሱበት ነበር።
ከዚህ ቀደም ማኅበሩን ለመመስረት ተሞክሮ መሳካት ያለቻለበት ምክንያት በመግለፅ መድረኩን በንግግር የከፈቱት አቶ ሚካኤል የማኅበሩ አላማ አብራርተዋል። ” የማህበሩ ዓላማ የትግራይ ክልል እግርኳስ እድገትን ለማፋጠን እና ለአሰልጣኞቻችን ምቹ የስራ ሁኔታ መፍጠር ነው፤ በትግራይ ብሎም በኢትዮጵያ እግርኳስ አዳዲስ አሰልጣኞች መፍጠር ነው አላማችን። ” ያሉት አቶ ሚካኤል አምሃ ማኅበሩ አሰልጣኞች ጊዜውን የጠበቀ ስልጠና እንዲያገኙ እንደሚሰራም ገልፀዋል።
ቀጥለው ሃሳባቸው የሰጡት አቶ ዳንኤል ተስፋይም የማኅበሩ አላማ በስሩ ያሉት አሰልጣኞች ጊዜውን የጠበቀ ስልጠና እንዲያገኙ እና ፕሮፌሽናሊዝምን የተላበሰ አሰልጣኝ እንዲፈጠር እንደሆነ ገልፀዋል።
በመጨረሻ ሃሳቡን የሰጠው የቀድሞ የደደቢት ፣ አዳማ እና መቐለ ተጫዋች ግርማይ ምሩፅ ሲሆን ማኅበሩ ከጀማሪ እስከ ኢንስትራክተሮች ያቀፈ መሆኑን ገልፀው የእግር ኳሱን እድገት ለማፋጠን አልሞ እንደተነሳም ገልጿል።
በተያያዘ ዜና ማኅበሩ በቀጣይ እሁድ በ9:00 በሚላኖ ሆቴል የመጀመርያው ጉባዔውን እንደሚያደርግ ገልጿል።
© ሶከር ኢትዮጵያ