ፌዴሬሽኑና የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ሊያደርጉት የነበረው ስብሰባ ሳይካሄድ ቀርቷል

የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን በተለያዩ ወቅታዊ እግርኳሳዊ ጉዳዮች ዙርያ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች ጋር ለመነጋገር ዛሬ የተጠራው ስብሰባ ሳይካሄድ ቀረ።

የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጥቅምት 1 ከሚካሄደው የፌዴሬሽኑ ጠቅላላ ጉባዔ በፊት በሊግ አደረጃጀት የአሰራርና የአመራር ችግሮች የሚዳስስና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን የሚያስቀምጥ ጥናት ለባለድርሻ አካላት ለማቅረብ ጥሪ እንዲደረግለት ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ደብዳቤ ማስገባቱ ይታወቃል።

ዛሬ 04:00 ፌዴሬሽኑ አዲስ በገዛው ህንፃ ላይ በጥናቱ አቀራረብ ዙርያ ለመነጋገር በተያዘው ቀጠሮ መሠረት የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንትን ጨምሮ የሥራ አስፈፃሚ አባለት እና ጥናት አቅራቢው ባለሙያ በሰዓቱ ቢገኙም የፌዴሬሽኑ አመራሮች ለሌላ አስቸኳይ ስብሰባ ሄደናል በማለታቸው ስብሰባው ሳይካሄድ ቀርቷል። በዚህም የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን አመራሮችን ቅር ያሰኘ እና ፌዴሬሽኑ ለጉዳዩ ትኩረት ያልሰጠው በመሆኑ እንዳሳዘናቸው ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ