“ያለፈው ዓመት ፕሪምየር ሊግ አልተጠናቀቀም” የደደቢት ክለብ ፕሬዝዳንት – አቶ ሚካኤል ዓምደመስቀል

ደደቢቶች የሊጉ ፎርማት ወደ ቀድሞ መመለሱ ተከትሎ ቅሬታቸው በማቅረብ ውሳኔው ለማስቀየር እንደሚሰሩ ገለፁ።

የፕሪምየር ሊጉ ፎርማት ወደ ቀድሞ መመለሱን ተከትሎ ደቡብ ፖሊስ እና መከላከያ ቅሬታቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ መግለፃቸው ይታወሳል። አሁን ደግሞ ደደቢት ተረኛው ቅሬታው የገለፀ ቡድን ሆኗል።

” የፕሪምየር ሊጉ ተሳታፊ ቡድኖች ወደ 24 ማደጉን ተከትሎ በሊጉ ትሳተፋላቹ ተብለን በዛ መልክ ነው ስንዘጋጅ የቆየነው ውሳኔው መቀየሩ በርካታ ነገር አበላሽቶብናል።” ያሉት የክለቡ ፕሬዝደንት አቶ ሚካኤል ዓምደመስቀል ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር በነበራቸው ቆይታ የሚከተለውን ሃሳብ ሰጥተዋል።

– ቡድኑ በፎርማት ለውጡ ላይ ያለው አቋም

እኛ ሊጉ ገና አላለቀም ባዮች ነን። በተለይም ጊዮርጊስ የተሰጠው ፎርፌ ከተነሳ ውድድሩ ገና አላለቀም ማለት ነው። አሁን ጊዮርጊስ ወደ ውድድሩ ተመልሷል ተብሏል፤ ውድድሩን ያጠናቀቀበት ደረጃስ ስንት ነው? ዘጠኝ ነጥብ በፎርፌ ለተጋጣሚ ተሰጥቶ ነበር። አሁን ይህ ውሳኔ ከተሻረ ውጤቱ ለማን ነው የተሰጠው? የሚሉት ጥይቄዎች ምላሽ ያስፈልጋቸዋል።

በአጠቃላይ የባለፈው ዓመት ውድድር መጥፎ ነበር። በዚ መሰረትም ፌደሬሽኑ የባለፈው ዓመት ውድድር በትክክል አልመራሁትም ብሎ ይቅርታ በመጠየቅ ለሁላችንም አስታራቂ ሃሳብ ማቅረብ አለበት። ካልሆነ ለአንዳንድ አካላት ነፃ በማድረግ እየተኬደበት ያለው መንገድ ትክክል አይደለም። የፌደሬሽኑን ውሳኔ እንቃወመዋለን፤ በጠቅላላ ጉባዔም በዚህ ጉዳይ ላይ በደምብ እንሄድበታለን።

– ፎርማቱ ወደ ቀድሞ በመመለሱ በቡድኑ ስላከተለባቸው ነገሮች

ፌደሬሽኑ አዲስ ባወጣው ፎርማት መሰረት ተዋውለን ደሞዝም ከፍለናል። በዛ መሰረት የቀጣይ ዓመት እቅድ አፅድቀናል። ተጫዋቾችም አስፈርመናል። ተጎጂዎች ነን፤ ባስፈረምናቸው ተጫዋቾችም ተጠያቂ ነን። በአጠቃላይ አካሄዱም ውሳኔውም ትክክል አደለም። ጊዮርጊስን ነፃ ለማውጣት አንድ የፌደሬሽኑ ሰራተኛን ተጠያቂ በማድረግ የህግ ስርዓቱ ማዛባት ትክክል እና ሚዛናዊም አደለም። በአጠቃላይ የባለፈው ዓመት ሊግ አልተጠናቀቀም የ 2012 ፕሪምየር ሊግ በተመለከተ ደግሞ በደረሰን ደብዳቤ መሰረት ተጫዋቾች አስፈርመናል ፤ የፌደሬሽኑ ውሳኔ የበሰለ እና የታሰበበት ውሳኔ አደለም። ውሳኔውን ለማስቀየር እስከመጨረሻው እንሄዳለን።

– ቡድኑ ባለፈው ዓመት ባስመዘገበው ነጥብ ቀጣይ ዓመት በብሄራዊ ሊግ መሳተፍ አለበት ተብሎ ለሚነሳው ጥያቄ

ህግ ይተግበር፤ ባልተጠናቀቀ ሊግ ላይ እንዲ ነው እንዲ ነው የሚያስብል ነገር የለም። ፌደሬሽኑ እንደ ፌደሬሽን መጠየቅ እያለበት ስህተቶች በግለሰቦች እያደረጉ ማምለጥ ተገቢ አይደለም።


© ሶከር ኢትዮጵያ