በኢንተርናሽናል መድረክ ጨዋታዎችን እንዲመሩ የሚያስችለው የፊፋ ባጅን ለማግኘት በተሰጠው ፈተና. ያለፉ እና ከኢትዮጵያ ማዕረጉን የሚያገኙ እጩ ዳኞች ታውቀዋል።
በቅርቡ በተሰጠው የዳኞች ፈተና ላይ ከተሳተፉ ዳኞች መካከል በወንዶች የአንድ ዋና እና ሁለት ረዳት ዳኞች ለውጥ ተከስቷል። በዚህም መሠረት ኃይለየሱስ ባዘዘው ከሁለት አመት በኋላ ወደ ኢንተርናሽናል ዳኝነት ሲመለስ ፋሲካ የኋላሸት እና ይበቃል ደሳለኝ የፊፋ ባጅ ያገኙ ረዳት ዳኞች ሆነዋል። ዳዊት አሳምነው በዋና ፤ ክንፈ ይልማ እና ኃይለራጉኤል ወልዳይ በረዳት ዳኞች ወደ ፌዴራልነት የወረዱ የቀድሞ ኢንተርናሽናል ዳኞች ሆነዋል።
በወንዶች ዘርፍ 6 ዋና እና 5 ረዳት ዳኞች የፊፋ ባጃቸውን ይዘው የሚቀጥሉ ሲሆን በአምላክ ተሰማ፣ በላይ ታደሰ፣ ብሩክ የማነብርሀን፣ አማኑኤል ኃይለሥላሴ፣ ለሚ ንጉሴ እና ቴዎድሮስ ምትኩ በዋና ዳኝነት፤ ተመስገን ሳሙኤል፣ በላቸው ይታየው፣ ትግል ግዛው፣ ሽዋንግዛው ተባባል እና ክንዴ ሙሴ በኢንተርናሽናል ረዳት ዳኝነታቸው የሚቀጥሉ ናቸው።
በሴቶች በዋና ዳኝነት ጌራ ወርቅን በመተካት መዳብ ወንድሙ በኢንታርናሽናልነት ቦታ ስትተካ በረዳት ዳኝነት አዜብ አየልን በመተካት ብርቱካን ማሞ ማደግ ችላለች።
ሊዲያ ታፈሰ፣ ፀሐይነሽ አበበ እና አስናቀች ገብሬ በፊፋ ዋና ዳኝነታቸው የሚቀጥሉ ሲሆን ወይንሸት አበራ፣ ወጋየሁ ዘውዴ እና ይልፋሸዋ አየለ በረዳት ዳኝነት ይቀጥላሉ።
ከላይ የተጠቀሱት (በወንዶች 7 ዋና እና 7 ረዳት፣ በሴቶች 4 ዋና እና 4 ረዳት ዳኞች) በቅርቡ የፊፋ ባጅ እንደሚረከቡ ሲጠበቅ ከ2020 ጀምሮ በሚካሄዱት አህጉራዊ እና ዓለምአቀፋዊ ውድድሮች ላይ ተሳታፊ ይሆናሉ።
© ሶከር ኢትዮጵያ