የ2012 ፕሪምየር ሊግ በክለቦች ይመራል

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ኢሊሊ ሆቴል በሚገኘው የስብሰባ አዳራሽ ዛሬ ከክለቦች ጋር ባደረገው ስብሰባ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በምን አግባብ መመራት እንዳለበት ከክለቦች ጋር በመሆን ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

በ2012 በሚደረገው ውድድር ፕሪምየር ሊግ በራሳቸው ክለቦቦቹ መመራት እንዳለበት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ “ይህ ጉዳይ ላለፉት 12 ዓመታት ሲከባባለል ቆይቷል። አሁን ግን ከቃል ባለፈ ወደ ተግባር እንገባለን።” በማለት ንግግር የከፈቱ ሲሆን በ2012 ውድድሩ እንዴት ይካሄድ የሚል ሰፊ ሀሳብ ከተሸራሸረ በኋላ በስተመጨረሻ 7 አባላት ያሉት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አመራር ዐቢይ ኮሚቴ ተመርጧል።

በምርጫው መሠረት መቶአለቃ ፈቃደ ማሞ (ኢትዮጵያ ቡና) ሰብሳቢ ሆነው ሲመረጡ ምክትል ሰብሳቢ ዶ/ር ከሳቴ ለገሰ (ከመቐለ) ተመርጠዋል። አቶ እሸቱ ቢያድጎ (ከፋሲል)፣ አቶ አንበሴ መገርሳ (ከአዳማ)፣ አቶ አሰፋ ሀሲሶ (ከድቻ)፣ አቶ አንበሳው አውግቸው (ከድሬዳዋ) እና አቶ መንግስቱ ሳሳሞ (ከሲዳማ ቡና) ደግሞ በአባልነት የተካተቱ ናቸው።

ከምርጫው በኋላ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ “ኮሚቴው በድንብ እስኪደራጅ ድረስ ፌዴሬሽኑ ቢሮ ያመቻቻል፤ እንዲሁም ቴክኒካል እገዛዎች እና የቢሮ እቃዎችን ያሟላል። ከክለቦች አሰያየም ጋር ያለውን የምዝገባ ሂደት ጨርሰን የምናስረክብም ይሆናል። ይህ ኮሚቴ በሚቀጥለው ሳምንት ተገናኝቶ ውድድር የሚመራበትን ጊዜ እንወስናለን። ለሰላማዊ የስልጣን ሽግግር የስራ አስፈጻሚ አባላትን እናመሰግናለን፤ የተሻለ የውድድር ዘመን እመኛለሁ።” ብለዋል።

የዐቢይ ኮሚቴው ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ በበኩላቸው የ2012 ውድድር ህግ የሚከበርበት መሆን እንዳለበት ገልፀው ህግ እና ደንብ የማያከብሩ ክለቦች ከውድድር እንደሚሰረዙ ገልፀዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ