ወደ ፕሪምየር ሊጉ ዳግም ያደገው ሀዲያ ሆሳዕና ግብ ጠባቂው ታሪክ ጌትነትን እና የሴራሊዮን ዜግነት ያለው አጥቂው ሙሳ ካማራን አስፈርሟል፡፡
የቀድሞው የደደቢት ግብ ጠባቂ ታሪክ በክለቡ ቆይታው ለብሔራዊ ቡድን በተደጋጋሚ እየተጠራ ሲጫወት የነበረ ሲሆን በ2011 የውድድር ዘመን ወደ ወላይታ ድቻ ተጉዞ የክለቡ ቋሚ ግብ ጠባቂ በመሆን በበርካታ ጨዋታዎች ላይ መሰለፍም ችሏል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ወደ አዳማ ከተማ ለማምራት ከክለቡ ጋር ቅድመ ስምምነት ላይ የደረሰ ቢሆንም ከክፍያ ጋር በተያያዘ መስማማት ባለመቻሉ ሀዲያ ሆሳዕናን ተቀላቅሏል፡፡ ታሪክ አምና በከፍተኛ ሊጉ የሀድያ ሆሳዕናን ግብ በቋሚነት ሲጠብቅ ከነበረው የመቐለ 70 እንደርታው ግብ ጠባቂ ፊሊፕ ኦቮኖ ታናሽ ወንድም ኢኳቶሪያል ጊናዊው አቢ ኦቮኖ ጋር ለቋሚ ተሰላፊነት ብርቱ ፉክክርን የሚያደርግ ይሆናል፡፡
ሌላኛው የሀዲያ ሆሳዕና አዲስ ፈራሚ የሴራሊዮን ዜግነት ያለው አጥቂው ሙሳ ካማራ ነው፡፡ የ22 አመቱ ወጣት አጥቂ በሀገሩ ሴራሊዮን ክለብ የሆነው ኢስት ኢንድ ላይን ለተባለ ክለብ የተጫወተ ሲሆን ወደ ስውዲን አምርቶም በሱፐር ታን ተሳታፊው ክለብ ትሪል ቦርግስ ለመጫወት ፊርማውን ያኖረ ቢሆንም ከአንድ ሳምንት ያልዘለለ ቆይታን አድርጎ ለመለያየት ተገዷል፡፡ ለሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድን በቅርቡ ጥሪ ደርሶት የነበረው አጥቂው በድጋሚ ተመልሶ ሲጫወትበት ከነበረው የሀገሩ ክለብ ኢስት ኢንድ ላይንን በመልቀቅ ወደ ኢትዮጵያ መቶ አዲሱ የሀዲያ ሆሳዕና ፈራሚ ሆኗል፡፡
በአሰልጣኝ ግርማ ታደሰ እየተመራ ከሰሞኑ በሆሳዕና ከተማ በቀን ሁለት ጊዜ በሜዳ እና በጂም ተግባራት የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን የጀመረው ሀዲያ ሆሳዕና አዳዲስ እና ነባር ተጫዋቾችን በመያዝ ልምምዱን አጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን ባለፈው ዓመት በክለቡ በነበሩ ሦስት የውጪ ተጫዋቾች ምትክ ለማስፈረም ለሁለት ጋናዊያን ተጫዋቾች የሙከራ ጊዜን ሰጥቷል፡፡ ፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ