ዋሊያዎቹ ዛሬ ማምሻውን ባህር ዳር ገብተዋል

በካሜሩን አስተናጋጅነት የሚካሄደው የአፍሪካ ሃገራት ሻምፒዮና (ቻን) ውድድር ላይ ለመካፈል የማጣሪያ ጨዋታዎችን እያደረጉ የሚገኙት ዋሊያዎቹ ለዝግጅት ዛሬ ባህር ዳር ገብተዋል።

በአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ የሚመሩት ዋሊያዎቹ በካሜሩኑ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታቸውን በትግራይ ዓለማቀፍ ስታዲየም አከናውነው 1-0 መሸነፋቸው ይታወሳል። ብሄራዊ ቡድኑ የመልሱን ጨዋታ ሩዋንዳ ኪጋሊ ላይ ለማድረግ ዝግጅቱን በአዳማ ያደርጋሉ ተብሎ ቢነገርም የወዳጅነት ጨዋታ በመሃል በመገኘቱ የዝግጅቱ ቦታ ተቀይሯል። በዚህም አሰልጣኙ የመረጧቸው 24 ተጨዋቾች ትላንት በአዲስ አበባ ስታዲየም ሪፖርት አድርገው ዛሬ ማምሻውን ወደ ባህር ዳር ገብተዋል። 11:00 ባህር ዳር የደረሰው ብሄራዊ ቡድኑም በዩኒሰን ሆቴል ማረፊያውን አድርጓል።

በሰላም ባህር ዳር የደረሰው ብሄራዊ ቡድኑም ለ45 ደቂቃ የቆየ የጂምናዚየም ስራ ባረፈበት ዩኒሰን ሆቴል እንዳደረገ ታውቋል። ከሩዋንዳው ወሳኝ ጨዋታ በፊት ከዩጋንዳ ብሄራዊ ቡድን ጋር እሁድ የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ ያለሙት ዋሊያዎቹ ከነገ ጀምሮ በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም በቀን አንድ ጊዜ ልምምድ እንደሚያደርጉ ተሰምቷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ