በሀዋሳ የቅድመ ውድድር ጊዜ ልምምዳቸውን እየሰሩ ያሉት ደቡብ ፖሊሶች አጥቂው ተመስገን ገብረፃድቅን ማስፈረም ሲችሉ የሙከራ ጊዜን የሰጡት ዩጋንዳዊውን አማካይ ኢቫን ሳካዛን ለማስፈረም ከስምምነት ደርሰዋል፡፡
ከሀዋሳ ከተማ የታዳጊ ቡድን እስከ ዋናው ድረስ መጫወት የቻለው የፊት መስመር አጥቂው ተመስገን ገብረፃድቅ ዛሬ ፖሊስን ተቀላቅሏል፡፡ በሀዋሳ ከተማ፣ አዳማ ከተማ፣ ሀዲያ ሆሳዕና እንዲሁም መከላከያ ተጫውቶ ያሳለፈው ተመስገን አምና በሲዳማ ቡና ቆይታን ካደረገ በኃላ በደቡብ ፖሊስ የአንድ ዓመት ቆይታን ለማድረግ ፈርሟል፡፡
አማካዩ ኢቫን ሳካዛ ደቡብ ፖሊስን ለመቀላቀል ከጫፍ የደረሰ ተጫዋች ሆኗል፡፡ ዩጋንዳዊው የመሀል አማካዩ ለአንድ ሳምንት ያህል የሙከራ ጊዜን ያሳለፈ ሲሆን አሰልጣኝ ተመስገን ዳናን በማሳመኑ በክለቡ ለመጫወት ከስምምነት ደርሷል፡፡ በኬኒያዎቹ ክለቦች ሊዮፓርድስ እና ዌስተር ስቲማ እንዲሁም በታንዛኒያው ማዋዱይ ዩናይትድ እና በሱዳኑ አልሀሊ ሸንዲ የተጫወተው ይህ የአጥቂ አማካይ ዝውውሩን ካጠናቀቀ በክለቡ የውል ኮንትራት ካላቸው ላኪ ሰኒ እና ተከላካዩ አዳሙ መሐመድ በመቀጠል ሦስተኛው የውጪ ዜጋ ተጫዋች ይሆናል፡፡
ከደቡብ ፖሊስ ጋር በተያያዘ በግብ ጠባቂነት ፈርሞ የነበረው መስፍን ሙዜ በኢኮስኮ ቀሪ ውል እያለው ክለቡን በመቀላቀሉ ወደ ኢኮስኮ በድጋሚ ለመመለስ የተገደደ ሲሆን ከወላይታ ድቻ መጥቶ የነበረው አጥቂው ሀብታለም ታፈሰም ከፖሊስ ጋር በስምምነት ተለያይቷል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ