ካፍ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ላይ ቅጣት አስተላልፏል

(መረጃው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ነው)

የ2011ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እና የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች የጥሎ ማለፍ ዋንጫ ከተያዘላቸው ጊዜ በመዝግየት መጠናቀቃቸው ይታወሳል። የመዘግየታቸው ዋንኛ ምክንያቶች በስታዲየሞች አካባቢ የነበሩ የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደሎች እና ሀገራዊ የነበሩ ጸጥታ ችግሮች ውድድሮች ላይ ጫና የፈጠሩ እና በተያዘላቸው ጊዜ እንዳይጠናቀቁ ምክንያት ሆነዋል።

ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የአፍሪካ ቻንፒዮንስ ሊግ እና የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳፊዎችን ማሳወቂያ ጊዜ ይራዘምልኝ የሚል ጥያቄ ለካፍ የውድድር ዲፓርትመንት ማቅረቡን ተከትሎ ካፍም ጥያቄውን ተቀብሏል። በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በ2019/20 የአፍሪካ ሻንፒዮንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ካፕ ኢትዮጵያን የወከሉ ክለቦችን ውድድሩ በተጠናቀቁባቸው ቀናት ሰኔ 30/2011ዓ.ም(መቐለ 70 እንድርታ) እና ሐምሌ 14/2011ዓ.ም (ፋሲል ከነማን) ለካፍ አሳውቋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባደረገው ከፍተኛ ጥረት ክለቦቹ በውድድሮቹ ተሳታፊ ሆነዋል።

ነገር ግን በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ተሳታፊ የሆኑት መቐለ 70 እንደርታ እና የፋሲል ከነማ ከክለብ ላይሰንሲግ ጋር ያሉ ጉዳዮች ለክለብ ላይሰንሲንግ በተቀመጠው ጊዜ ገደብ በትክክል ለዲፓርትመንቱ አለመድረሱን በመግለጽ የ5,000.00 የአምስት ሺህ የአሜሪካን ዶላር ቅጣት ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ላይ ካፍ ማስተላለፉን ነሀሴ 23/2011ዓ.ም በጻፈው ደብዳቤ አሳውቋል።

ይህንንም ውሳኔ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በወቅቱ የተቃወመ እና አስፈላጊ መረጃዎችን በጊዜው የላከ መሆኑን ገልጾ ስለመቀበላቸው ከተደረጉ የኢሜል ልውውጦችን በማስረጃነት ቢያቀርብም ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ ካፍ ውሳኔውን ማጽናቱን አሳውቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ