ሀዋሳ ከተማ ተስፋዬ መላኩን ሲያስፈርም የጋናዊው ተከላካዩን ውልም ሊያራዝም ነው

የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቹ ተስፋዬ መላኩ ሀዋሳ ከተማን ሲቀላቀል ከመቐለ ጋር ስምምነት ፈፅሞ የነበረው ላውረንስ ላርቴ በሀይቆቹ ቤት ለመቆየት ተቃርቧል።

በመሐል እና በመስመር ተከላካይነት መጫወት የሚችለው ተስፋዬ መላኩ ለሀዋሳ ከተማ ለሁለት ዓመት አገልግሎት ለመስጠት ዛሬ ፊርማውን አኑሯል፡፡ የቀድሞው የወላይታ ድቻ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋች አምና በጅማ አባጅፋር ካሳለፈ በኋላ ዘንድሮ ለመቐለ 70 እንደርታ ለመጫወት ፊርማውን ያኖረ ቢሆንም ክለቡ ቢያድግልኝ ኤልያስን ለማቆየት በመወሰኑ ተስፋዬ በስምምነት ከመቐለ ጋር ከተለያየ በኃላ ማረፊያው የአሰልጣኝ አዲሴ ካሳው ሀዋሳ ሆኗል፡፡

ከሀዋሳ ከተማ ጋር ውሉን ቀደም ብሎ ቢያራዝምም ከክፍያ ጋር ሳይስማማ በመቅረቱ ወደ መቐለ ከተማ ሊያመራ ከጫፍ ደርሶ የነበረው የመሀል ተከላካይ ስፍራ ተጫዋቹ ላውረንስ ላርቴ ዳግም ወደ ሀዋሳ ከተማ ተመልሶ ከክለቡ ጋር ዝግጅትን ጀምሯል፡፡ ጋናዊው የቀድሞው አያክስ ኬፕታውን እና ክለብ አፍሪካን ተከላካይ ከሀዋሳ ጋር በክፍያ ጉዳዮች መስማማት ከቻለ ለሦስተኛ አመት በሀይቆቹ ቤት ቆይታውን ያረጋግጣል፡፡

ከሀዋሳ ከተማ ጋር በተያያዘ በክለቡ የሦስት አመት ቆይታ የነበረው ቶጎዊው ግብ ጠባቂ ሶሆሆ ሜንሳህን ለወልቂጤ ከተማ አሳልፎ በመስጠቱ ከአራት ዓመት በፊት የክለቡ ግብ ጠባቂ የነበረው ደቡብ አፍሪካዊው ብሪያን ቶቤጎን ዳግም ለመመለስ እንቅስቃሴ ላይ መሆኑን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ