ፌዴሬሽኑ በጅማ አባጅፋር ላይ ውሳኔ አሳለፈ

ከተጫዋቾች የደመወዝ ክፍያ እና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በፌዴሬሽኑ በተደጋጋሚ ውሳኔ ሲሰጥበት የሰነበተው ጅማ አባጅፋር ለሦስት የውጪ ተጫዋቾች የደመወዝ ክፍያን ባለመፈፀሙ ተጨማሪ ውሳኔ ተላልፎበታል።

በቅርቡ የክለቡ ነባር ተጫዋቾች በፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት ቀርበው የአራት ወራት ደሞዝ አልተከፈለንም በማለት ቅሬታን ያሰሙ ሲሆን ፌዴሬሽኑም የይከፈላቸው ደብዳቤን ለክለቡ ሁለት ጊዜ በመፃፍ ማሳወቁ ይታወሳል፡፡ ከዚህም ጉዳይ በተጨማሪ በክለቡ ውል እያለበት የተለያየው አማካዩ ይስሀቅ መኩሪያ ውል እያለብኝ ነው አግባብ ባልሆነ መንገድ የተሰናበትኩት በማለት ባቀረበው አቤቱታ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በተደጋጋሚ ለተጫዋቹ የይከፈለው ደብዳቤን ቢልክም ክለቡ ለመፈፀም ዝግጁ ባለመሆኑ ክለቡን ከኔ አገልግሎት አታገኙም በማለት የእግድ ውሳኔን አስተላልፎም ነበር፡፡

አሁን ደግሞ በክለቡ ከሚገኙት ሦስት የውጪ ተጫዋቾች የሰባት ወር እና የአምስት ወራት ደሞዝ ባለመከፈሉ ቅሬታቸውን ያቀረቡ ሲሆን ፌዴሬሽኑም በአስር ቀን ውስጥ ክፍያውን እንዲፈፅምላቸው ውሳኔ በመስጠት ይህን ማድረግ የማይችል ከሆነ ጉዳዩን ወደ ፍትህ አካላት እንደሚወስደው እና ተጫዋቾቹ ቀሪ የአንድ ዓመት ውል ቢኖራቸውም መልቀቂያ ደብዳቤን እንደሚሰጥ በደብዳቤው ገልጾ ለክለቡ ልኳል፡፡

የጅማ አባጅፋር ስራ አስኪያጅ አቶ ሱልጣን ቶፊቅ በጉዳዩ ዙርያ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ከሆነ “ለሁሉም ተጫዋቾች የወር ደሞዛቸውን ጠብቀን እየከፈልን ነው ያለነው። የሚቀረው የግንቦት እና ሰኔ ወር ብቻ ነው። እሱንም በሂደት እንከፍላለን።” ያለለ ሲሆን ሦስቱ ተጫዋቾች ማለትም ኦኪኪ አፎላቢ (አሁን መቐለ) ዲዲየር ለብሪ (አሁን ስሑል ሽረ) እና ከባህርዳር ጋር ስሙ የተያያዘው ተከላካዩ አዳማ ሲሶኮ በክለቡ ውል እንዳለባቸው፣ የወሰዱትን ንብረት እንዳልመለሱ እንዲሁም እስካሁን በአካል መጥቶ መልቀቂያ የጠየቀ ተጫዋች እንደሌለ ገልፀዋል፡፡

የተጫዋቾቹ ወኪል የሆነው ኤርሚያስ አሸኔ በበኩሉ የፊፋን ህግ በመጥቀስ “ተጫዋቾቹ ሁለት ወር ደሞዝ ካልተከፈላቸው በህጉ መሠረት ክለቡ ተጫዋቾቹን የመልቀቅ ግዴታ አለበት። ያን ካላደረገ ግን ፌዴሬሽኑ ራሱ መልቀቂያቸውን ይሰጣል።” ብሏል። ለተጫዋቾቹ ክፍያ እየተፈፀመላቸው ለተባለውም አንድም ገንዘብ በተጫዋቾቹ አካውንት ውስጥ እንዳልገባ ተናግሯል፡፡

*ለጅማ አባጅፋር ፌድሬሽኑ የላከው ደብዳቤ ይህንን ይመስላል፡-


© ሶከር ኢትዮጵያ