በአሁኑ ወቅት ከእግርኳስ ርቆ ኑሮውን በሀገረ አሜሪካ ያደረገው የቀድሞ የአዳማ ከተማ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋች ዐቢይ ሞገስ የዛሬው የሶከር ኢትዮጵያ እንግዳችን ነው።
የተወለደው ሀዋሳ ከተማ ቢሆንም እግርኳስን መጫወት የጀመረው እና ያደገው በባሌ ከተማ ነው። እንዳጋጣሚ ሆኖ ለዩኒቨርስቲዎች ውድድር አዳማ ከተማ ላይ ያሳየው መልካም እንቅስቃሴም ለእግርኳስ ህይወቱ መሠረት ጥሎለታል። እንዳለው እምቅ ችሎታ የታሰበውን ያህል ለረጅም ዓመታት መጫወት ሳይችል በጊዜ እግርኳስን ቢያቆምም በሪፍት ቫሊ ኮሌጅ ፣ በአዳማ ከተማ ፣ በሰበታ ከተማ እና በቅዱስ ጊዮርጊስ በኃላም ከሀገር ውጪ በሱዳኑ አል አህሊ ሸንዲ እንዲሁም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መጫወት ችሏል። ያመነበትን ነገር ከመናገር ወደኋላ የማይለው ዐቢይ እግርኳስን አቅልለው በነፃነት ከሚጫወቱ ተጫዋቾች መካከል አንዱም ነው። በኑሮ ምክንያት ወደ ሀገረ አሜሪካ በማቅናት ትዳር መስርቶ ልጆች አፍርቶ ህይወቱን እየገፋ የሚገኘው የቀድሞ ስመጥር ተጫዋች ዐቢይ ሞገስ የዛሬው የሶከር ኢትዮጵያ እንግዳችን ነው። አጠቃላይ የእግርኳስ ህይወቱን እና መሰል ጉዳዮችን በማንሳት ያደግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።
ትውልድ እና ዕድገትህ እንዲሁም የእግርኳስ ህይወትህ መነሻ የሆኑ ነገሮችን አጫውተኝ ..
የተወለድኩት ሀዋሳ ከተማ ይሁን እንጂ የልጅነት ዕድሜን እያሳለፍኩ በባሌ ከተማ ነው። ለእግርኳስ ህይወቴ ብዙም የተለዩ መነሻ ነገሮች ባይኖሩኝም እንደማንኛውም ተጫዋች በሠፈር ውስጥ ነው በመጫወት ያደኩት። በመቀጠል በብሔራዊ ሊግ የሚሳተፍ ባሌ ሮቤ ለሚባል ቡድን ለመጀመርያ ጊዜ በክለብ ደረጃ መጫወት ጀመርኩ። እንዲህ እንዲህ እያለ የእግርኳስ ህይወቴ አድጎ ወደ ትላልቅ ክለቦች ማምራት ችያለው።
ከፍ ባለ ደራጃ ያለህን አቅም አውጥተህ ያሳየኸው በአዳማ ከተማ በቆየህባቸው አምስት ዓመታት ውስጥ ነው ፤ እንዴት ነው አዳማን መቀላቀል የቻልከው ?
ቅድም እንዳልኩት የመጀመርያ የክለብ ቡድኔ ባሌ ሮቤ ነው። እዛ እየተጫወትኩ የሪፍት ቫሊ ክለብ አሰልጣኞች እና አመራሮች በእንቅስቃሴዬ ተደስተው የትምህርት ዕድል እና ሌሎች ወጪዎችን እንደሚሸፍኑልኝ ሲነግሩኝ ያው የተሻለ አማራጭ ስላገኘው ክለቡን መቀላቀል ችያለው። የሚገርመው በሪፍት ቫሊ የነበረኝ ቆይታ ለአንድ ወር ብቻ ነው። በዚህ አጭር ቆይታዬ ጥሩ ጊዜ አሳልፌበታለው። በወቅቱ ዋንጫ አንስቼበታለው ፤ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ሆኜም አጠናቅቄያለው። በተለይ ለእግርኳስ ህይወቴ ትልቅ መነሻ የሆኑኝ የተሻሉ ዕድሎች ከብዙ ክለቦች እንዲመጡልኝ ምክንያት የሆነኝ ክለብ ነው። በመጨረሻ ምርጫ ያደረኩትም አዳማ ከተማን ሆኗል።
አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የአዳማ ከተማ አሰልጣኝ በነበረበት ዘመን ነበር ለክለቡ ለመጫወት የተስማማኸው ?
አዎ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ነበር የአዳማ ዋና አሰልጣኝ የነበረው። በነገራችን ላይ ከአሰልጣኝ ውበቱ ጋር በተለያዩ ክለቦች አብሬ ሰርቻለው። እንዳጋጣሚ በ1999 እኔ አዳማን ስቀላቀል ኢትዮጵያ በፊፋ ቅጣት ተጥሎባት ስለነበረ የመጀመርያውን ዓመት ከተለያዩ ቡድኖች ጋር እንጫወት ነበር። ከ2000 ጀምሮ ግን በአዳማ ከተማ በነበረኝ ቀሪ ዓመታት ጥሩ ጊዜ አሳልፌአለው። ምንም እንኳን በዋንጫ የታጀበ ባይሆንም ቡድኑ ጥሩ ደረጃ ይዞ እንዲያጠናቅቅ ከሌሎች ተጫዋቾች ጋር በመሆን ትልቅ አስተዋፆኦ አድርጌአለው። በግሌም የክለቡ ከፍተኛ ጎል አግቢ በመሆን ማጠናቀቅ ችያለው። ደጋፊዎች በየጨዋታው በሚመርጡት የዕለቱ የጨዋታ ኮከብ ምርጫም በተደጋጋሚ ተሸልሜ አውቃለው። በአጠቃላይ አዳማ ከተማ ስፈርም እንዳሁኑ የፊርማ የሚባል ነገር አልነበረም በደሞዝ ነበር። በመሆኑም በገንዘብ ረገድ ብዙም ተጠቃሚ ባልሆንም ብዙ ሰዎችን ያወኩበት እና ደስ የሚያሰኝ ጊዜ ነው በአደማ የአምስት ዓመት ቆይታዬ ያሳለፍኩት።
ከአዳማ በመቀጠል ለአጭር ጊዜ ቆይታ በውሰት ወደ ሰበታ ከተማ አምርተህ ነበር ፣ እንዲያውም ያንተ ወደ ቡድኑ መቀላቀል ሰበታን ተጠቃሚ አድርጎት ነበር ፤ ስለሱ አጫውተኝ…
ሰበታ ለአጭር ጊዜ ነው የተጫወትኩት፤ ስንሄድም ‘አስገቧቸው’ ተብለን ነው በውሰት የተላክነው። ያን ጊዜ ሰበታ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለመግባት ወሳኝ ጨዋታዎች ነበሩት። አራት ጨዋታ ነው ለሰበታ መጫወት የቻልኩት፤ በወቅቱም ጎል እያስቆጠርኩኝ ፕሪምየር ሊግ የመግባት ፍላጎታቸውን አሳክቻለው። የሰበታ ደጋፊዎች የነበራቸው የእግርኳስ ፍቅር በጣም አስገራሚ ነበር። አጭር ጊዜም ቢሆንም ከሰበታ ጋር የነበረኝ ቆይታ በጣም ጥሩ የሚባል ነበር።
ከዚህ በኃላ የነበረው የእግርኳስ ህይወትህ በውዝግብ የተሞላ ነው። ብዙም እንዳሰብከው አልሆነም ምንድነው ተፈጥሮ የነበረው ?
በወቅቱ በ2004 ይመስለኛል በሁለት መቶ ሺህ የፊርማ ገንዘብ ለኢትዮጵያ ቡና ለመጫወት ፊርማዬን አኖርኩኝ። እንዳጋጣሚ ሆኖ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ዝግጅት ሳልጀምር ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዝግጅት ወደ አዳማ ራስ ሆቴል ሄድኩኝ። የዚህን ጊዜ አንዳንድ ጓደኞቼ ‘ለቅዱስ ጊዮርጊስ ብትጫወት ጥሩ ነው ብዙ የምትጠቀማቸው የተሻሉ ነገሮች አሉ’ ብለው ሲያግባቡኝ ያው እኔም በአዳማ አምስት ዓመት ስቆይ ብዙ የተጠቀምኩት ነገር አልነበረም እና መጠቀም ስለነበረብኝ በወቅቱ ለቡና ፈርሜ የነበረው ፌዴሬሽን ስላልፀደቀ ለኢትዮጵያ ቡናዎች ሳልነግራቸው ያው ለቅዱስ ጊዮርጊስ ልፈርም ችያለው።
በወቅቱ ይህ ለሁለት ክለብ የመፈረምህ ነገር የሚዲያ መነጋገሪያ ርዕስ የነበረ እና ብዙ ውዝግብ ያስነሳ ነበር…
አዎ የሚዲያ መነጋገርያ ነበር። ይገርምሀል በአዳማ ከተማ ስጫወት ብዙ ጊዜ ኢትዮጵያ ቡና ላይ ጎሎች አስቆጥር ነበር። በዚህም አኔን ለማስፈረም ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበራቸው ያ ነገር ተሳክቶ እኔን ማስፈረም ሲችሉ ‘አብይ ኢትዮጵያ ቡና ፈረመ’ ተብሎ ሲነገር ደጋፊዎቹ ደስተኞች ነበሩ። ሆኖም እንዳጋጣሚ አጥቂ ቦታ ላይ እኔን ብቻ ነበር አስፈርመው የነበረው። አጥቂው ታፈሰ ተስፋዬም ክለቡን ለቆ ስለነበረ ምንም ተጨማሪ አጥቂ ያልያዙ በመሆኑ ይህ ነገር በመፈጠሩ በሰዓቱ ብዙ ውዝግብ አስነስቶ ነበር።
በቅዱስ ጊዮርጊስ የነበረህ ቆይታ እንዳሰብከው አልሆነም ፤ ብዙም ሳትቆይ ነው ከክለቡ ጋር የተለያየኸው። ለምን ?
ከብሔራዊ ቡድን ዝግጅት መልስ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቅድመ ውድድር ዝግጅት መቐለ ከተማ ነበር ፤ ወደዛ ሄድኩኝ። በወቅቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ጣልያናዊው ዳንኤሎ ነበር። በወዳጅነት ጨዋታ እዛ በነበረን ዝግጅት ጎል እያስቆጠርኩ ጥሩም እየተንቀሳቀስኩኝ ነበር። ዝግጅቱን አሳልፈን እዚህ አዲስ አበባ ስመጣ ግን ብዙ ያላሰብኩት ነገር ገጠመኝ። አብዛኛውን ጊዜ በተጠባባቂ ወንበር ላይ ማሳለፍ ጀመርኩ። ይህ በጣም ያስከፋኝ ጀመር። ‘በዝግጅት ወቅት በእንቅስቃሴም ጥሩ ሆኜ ጎልም እያስቆጠርኩ መልካም ስራ ሰርቼ ነው የመጣሁት ፤ በተጠባባቂ ወንበር ላይ እንድቀመጥ ያደረገኝ ምክንያት ምንድነው?’ ብዬ ጥያቄ ስናነሳ ኤልያስ ማሞም በተመሳሳይ ጥያቄ አብሮኝ ነበር። ሆኖም ለጥያቄያችን አጥጋቢ ምላሽ አልተሰጠንም። በተደጋጋሚ ብጠይቅም ምላሽ በማጣቴ ‘የመጫወት አቅም እያለኝ እዚህ ብዙ ከምቀመጥ ወደ ሌላ ቦታ ሄጄ ልጫወት’ በማለት ጥያቄ አቀረብኩኝ። ጥያቄዬን አልቀበልም ሲሉኝ ‘አይ አኔ መጫወት እፈልጋለው’ ብዬ ለፊርማ የተቀበልኩትን ገንዘብ መልሼ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ልለቅ ችያለው።
በዚህ መልኩ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የነበረህን ቆይታ እንዴት ታየዋለህ ?
ተቀይሬም እየገባሁኝ ቢሆን በአንዳንድ ጨዋታዎች ላይ ጎሎችንም አስቆጥር ነበር። በገባሁባቸው አጋጣሚዎች ጥሩ እንቅስቃሴ አደርጋለው ግን ወደ ቋሚ ተሰላፊነት መመለስ አልቻልኩም። ያው በቡድኑ ውስጥ ሲኒየር የሆኑና የማይነኩ ተጫዋቾች መኖራቸው ይመስለኛል ወደ መጀመርያ አስተላለፍ እንዳልገባ ያደረገኝ።
ከዚህ በኃላ ምን ተፈጠረ ? ክለቡ የዲሲፒሊን ቅጣት አስተላለፈብህ ? ወዴትስ አመራህ ?
በህጋዊ መንገድ እንዲለቁኝ ብጠይቅም በቂ ምላሽ በማጣቴ ነው ክለቡን ለመልቀቅ የተገደድኩት። በዚህም ክለቡ ምንም ያስተላለፈብኝ ቅጣት አልነበረም። አስቀድሞ የተከፈለኝን ብር መልሼ አንደኛው ዙር ሲጠናቀቅ ወደ ቤቴ ሄጄ ተቀመጥኩኝ።
በዚህ ሁኔታ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር እለያያለው ብለህ አስበህ ነበር ?
በፍፁም አላሰብኩም ! አዳማ ከነበረኝ የተሳካ ቆይታ በተሻለ ጥሩ ጊዜ ይኖረኛል ብዬ አስቤ ነበር። ያው ትልቅ ቡድን ስትገባ የሚኖሩ ተግዳሮቶች ቢኖሩም በልምምድና በጨዋታ ላይ የምችለውን አቅም አውጥቼ እራሴን ለማሳየት ከፍተኛ ጥረት አድርጌ ነበር። ሆኖም ከእኔም በወቅቱም ከነበረው አሰልጣኝም አቅም በላይ በመሆኑ በእግርኳስ ህይወቴ የማረሳው አጋጣሚ ሆኖ አልፏል።
ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከተለያየህ በኃላ የእግርኳስ ህይወትህ አልተረጋጋም። በቀጣይ ወዴት አመራህ ?
2005 ወይም 2006 ይመስለኛል ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን መቀላቀል ቻልኩኝ። ለአንድ ዓመትም ጥሩ ጊዜ አሳለፍኩኝ። የሆነ ሰዓት ትዝ ይለኛል ከደደቢት ጋር ስንጫወት በተረከዜ ላይ ጉዳት አስተናገድኩኝ። ትንሽ ህመሙ ጠንከር ስለሚል የተለያዩ ህክምናዎችን በተለያዩ ሆስፒታሎች ባደርግም ከጉዳቴ ማገገም አልቻልኩም። በመጨረሻም በባህላዊ ህክምና እራሴን አስታምሜ ወደ ጨዋታ ብመለስም አጋጣሚ ሆኖ ወደ አሜሪካ ሀገር መሄድ ቻልኩኝ። ይህ ነገር ሌላ ውዝግብ አስነስቶ ‘ለፊርማ የተቀበለውን ገንዘብ ይዞ ወደ አሜሪካ ሄደ’ ተብሎ ተወርቶብኝ የነበረ ቢሆንም እኔ ግን የተሰጠኝን አራት መቶ ሺህ ብር እዛው አሜሪካ ሆኜ በጓደኛዬ አማካኝነት ተመላሽ አድረጌ ነበር። ይገርምሀል ገንዘባቸውን ገቢ ካደረኩ በኃላ ‘ወደ ሱዳን ሊሄድ ነው’ የሚለው ወሬ ተወርቶ ስለነበር ለሦስት ወር ያህል መልቀቂያ አልሰጡኝም ነበር። በመጨረሻም መልቀቂያው ሲሰጠኝ ወደ ሱዳን ላመራ ችያለው።
የእግርኳስ ዘመንህ ማጠቃለያ ላይ ደርሰናል። ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ከተለያየህ በኃላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰህ አልተጫወትክም። ሳይታሰብ ወደ ሱዳኑ አል አህሊ ሸንዲ ያመራህው እንዴት ነው ?
ከአሜሪካ ተመልሼ ኢትዮጵያ መጣሁ። የክለቡ አሰልጣኝ ደግሞ ውበቱ አባተ በመሆኑ ወዳዛ ሄጄ ለመጫወት ችያለው። አል አህሊ ሸንዲ በሱዳን ሊግ ውስጥ ከሚገኙ ክለቦች በርካታ ደጋፊዎች ያሉት እና በፋይናስ አቅሙም የተሻለ ቡድን ነው። እዛ በነበረኝ ቆይታ ጥሩም አስቸጋሪም ጊዜ አሳልፌላው። እኔ ከኢትዮጵያ ስሄድ ክለቡ የሚጫወትበት ከተማ ካርቱም መስሎኝ ነበር። ሆኖም ቡድኑ ጨዋታ የሚያደርግበት ሜዳ ከከተማው ራቅ ያለ ነው። እኔ ብዙ ጊዜ ኢትዮጵያ ሆኜ በተለያዩ ከተሞች ተዟዙሬ ተጫውቻለው ፤ እንደዚህ ዓይነት ነገር አጋጥሞኝ ግን አያውቅም። ከተማዋ ላይ ከፍተኛ የሆነ ሙቀት አለ ፤ ክለቡ ምንም አይነት ካምፕ የለውም በአንድ አዳራሽ ውስጥ የሙቀት ማቀዝቀዣ በሌለው ቦታ ትተኛለህ። የምግብ አቅርቦታቸው ደግሞ ዜሮ ነው። ቁርስ ላይ እንቁላል ትበላለህ ምሳና እራት የምትበላው ፉል ብቻ ነው። በዛ ላይ የሱዳን ህዝቦች አኗኗር ትንሽ ከእኛ የተለየ ነገር አለው። ለምሳሌ ‘እየመጣው ነው’ ካለህ ምን አልባት ከሁለት ቀን በኃላ ሊመጣ ይችላል። በቃ ምን ልበልህ ሸንዲ የነበረው ነገር ተስፋ አስቆራጭ እና ያልጠበኩት ነገር የሆነብኝ። የገንዘብ ችግር የለም ፤ ገንዘብ ጥያቄ ውስጥ አይገባም። ግን ያው ከሀገር አንዴ ስለወጣው እነዚህ ነገሮች ተቋቁሜ ለመኖር ወስኜ የነበረ ቢሆንም የመጀመርያው ዙር እስኪጠናቀቅ ድረስ ብቻ መጫወት ቻልኩኝ። በኃላ ላይ ግን አልቻልኩም። ሁሉ ነገር ከአቅሜ በላይ ሲሆን መጫወቱን ትቼ በዛው ወደ አሜሪካ ሀገር መሄድ ችያለው።
በሱዳን ከአዲስ ህንፃ ጋር በአንድ ቡድን ነበራችሁን እንዲሁም ከሽመልስ በቀለ ጋርም በተለያዩ ክለቦች ተጫውታቹኋል ፤ ስለእነርሱ ንገረኝ እስኪ…
ከአዲስ ህንፃ ጋር በአንድ ክለብ ከመጫወታችን በተጨማሪ እዛ ክለብ በነበረኝ ቆይታ ከእርሱ ጋር ነበር አብዛኛውን ጊዜ አሳልፍ የነበረው። እንደ ጓደኛ እንደ ሀገር ልጅም አዲስ ከእኔ ቀድም ብሎ ስለ ነበር የሄደው ሁሉም ነገር የእነሱ አኗኗርም በደንብ ገብቶት ነበር። ብዙ ነገር እየመከረኝ እና እየረዳኝ አብረን ቆይታ አድርገናል። አዲስ ጥሩ የበረሀ ጓዴ ነበር። ሽሜ ትንሽ ከእኛ በሁሉም ነገር በተሻለ ክለብ ነው ይጫወት የነበረው። በጣም ጥሩ ግንኙነትም ነበረን። ጥሩ ጊዜም አብረን አሳልፈናል። በተለያዩ ክለቦች በተቃራኒ ሆነን መጫወትም ችለናል።
ወደ አሜሪካ የሄድክበት ምክንያት ምን ነበር ?
የሄድኩት ኳስ ተጫዋች ለመሆን አልነበረም። እንደማንኛውም ሰው ለመኖር ነው የሄድኩት ፤ አሪዞና በምትባል ከተማ። የአሁኗ ባለቤቴ ከእኔ ቀድማ እዛ ብዙ ዓመት ኖራለች ፤ እርሷ ጋር ነው የሄድኩት። ያው እርሷ በእግርኳሱ ብዙ እንድገፋ እንድጫወት ትፈልግ ነበር። ትንሽ የእኔ በህሪ ከኳስ ተጫዋቾች ይለያል። እግርኳስን ቀለል አድርጌ እየተዝናው ነው መጫወት የምፈልገው ተጨናንቄ መጫወት አልፈልግም። በነፃነት ነው መጫወት የምፈልገው። ሱዳን የነበረኝን ቆይታ ደግሜ ማየት አልፈለኩም ፤ ‘ከዚህ በኃላ የምረዳው ሰው የለ ለአንድ ለእራሴ ነው’ ብዬ እግርኳስን አቁሜ ተጠቃልዬ አሜሪካ ገባው።
አቅም እያለህ መጫወት እየቻልክ በአጭር ጊዜ ውስጥ የእግርኳስን በማቆምህ አትቆጭም ?
በየትኛውም አጋጣሚ እግርኳስን መጫወትን ልታቆም ትችላለህ። እውነት ነው አሁንም ድረስ መጫወት የሚያስችል አቅም አለኝ። ሆኖም በወቅቱ የነበሩ ሁኔታዎች አስገዳጅ በመሆናቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ እግርኳስን ለማቆም ተገድጃለው። አሁን ላይ ሆኜ የምቆጭበት ምንም ነገር የለም።
ወደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ልውሰድህ፤ በብሔራዊ ቡድን የነበረህ ቆይታ እንዴት ነው ?
ብሔራዊ ቡድን ላይ ብዙም አልነበርኩም። የመጀመሪያዬም የመጨረሻዬም አዳማ እያለው የውጪ ሀገር አሰልጣኝ የጠራኝ ጊዜ ነው። ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጊኒ ኮናክሬ ሄጄ ነበር። ከዛ በኃላ እንዳልኩህ በብሔራዊ ቡድን ተጠርቼ መጫወት አልቻልኩም።
በእግርኳስ ህይወትህ የምታደንቀው ምሳሌ የምታደርገው ተጫዋች አለ ?
ልጅ ሆኜ እንደ እርሱ ብሆን ብዬ የምመኘው ተጫዋች አልነበረም። ሆኖም ለያሬድ ዝናቡ ትልቅ አድናቆት አለኝ። ያሬድ ዝናቡ ያለው አቅም ማንም ተጫዋች ጋር እስካሁን አላየሁም። እርሱ ጋር የተለየ ነገር ነው ያየሁት ፤ ምንም ቦታ ላይ ይጫወታል። ያገኘሁትን ሰው ሁሉ እጠይቃለው ፤ በጣም የሚገርም ችሎታ ነበር ያለው። ሁልጊዜ የማወራው ስለ እርሱ ብቻ ነው። በጣም የያሬድ አድናቂ ነኝ።
ባለህበት ሀገር ሆነህ የኢትዮጵያ እግርኳስን የመከታተል አጋጣሚ አለህ ?
ምንም ነው ማለት ይቻላል ፤ የመከታተል አጋጣሚው የለኝም። በአሜሪካ ስትኖር በተለይ ልጅ ኖሮህ ከሆነ የሚኖርህ ጊዜ አይኖርም። የምትኖረው አሜሪካ በሰጠችህ ሲስተም እንጂ በራስህ መንገድ ባለመሆኑ በየትኛውም አጋጣሚ የማየት ዕድሉ የለኝም።
© ሶከር ኢትዮጵያ