የ2012 የውድድር ዘመን ፕሪምየር ሊግን አስመልክቶ አዲስ የተዋቀረው ዐቢይ ኮሚቴ የመጀመርያ ስብሰባ ዝርዝር ዘገባ።
የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት ኢሳይያስ ጂራን ጨምሮ ሁሉም የኮሚቴ አባላት በተገኙበት ስብሰባ ላይ የ2012 የኢትዮጵያ ፕሪምየር የሚጀመርበትን ቀን በተመከለተ ካሳለፈው ውሳኔ ባሻገር በርከት ያሉ አጀንዳዎችን በማሳት ሲነጋገር የዋለ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ የወሰደው የሰነድ ርክክብ ጉዳይን በተመለከተ፣ የሚቋቋሙ ኮሚቴዎች ጉዳይ እና ከፌዴሬሽኑ ጋር ድምዳሜ ያልደረሱበት በይደር የቆየው የውድድር ሥነ ስርዓት ኮሚቴ እና የፍትህ አካላት አወቃቀር ዙርያ ሰፊ ውይይት አድርገዋል።
በመቀጠል ከመነሻው የኢትዮጵያ እግርኳስ ችግር የሚመነጨው ከውድድር ኮሚቴ እና ከዳኞች ኮሚቴ አባላት በመሆኑ እነዚህ ኮሚቴዎች ላይ ጥርት ያለ አቋም በመያዝ ሀቀኛ አመራር መስጠት የሚችሉ ሰዎች በቦታው ላይ ለመምረጥ ሁሉም ጠንካራ ሰዎች ለጥቆማ (በእጩነት) ይዘው እንዲመጡ ተነጋግረዋል።
ሌላው ድሬዳዋ ከተማ ፣ወላይታ ድቻ ፣ አዳማ ከተማ ፣ሀድያ ሆሳዕና ፣ ወልቂጤ ከተማ ፣ ጅማ አባ ጅፋር ፣ ሰበታ ከተማ እና የሌሎችም ሜዳዎች ማሟላት ይገባቸዋል የተባሉትን የእግርኳስ መጫወቻ ሜዳ፣ ፀጥታ ማስጠበቂያ (አጥር)፣ የተጨዋቾች መልበሻ ክፍል በሚገባ የተዘጋጁ መሆናቸውን በአግባቡ እንዲፈተሹ እና በሜዳዎች ዙርያ ለተመልካቹ አደገኛ የሆኑ ተወርዋሪ ነገሮች እንደ ድንጋይ፣ ኮረት እና አላስፈላጊ ቁሳቁሶች እንዲነሱ ይህ የማይሆን ከሆነ ውድድሩን ለማድረግ እንደሚቸገሩ ተገልጿል።
በተጨማሪም አዲስ የተዋቀረው ኮሚቴ ደብዳቤዎችን ለመፃፍ ገና ህጋዊ መሠረት የያዘ ባለመሆኑ ተዟዙሮ መጫወት እንዲቀጥል መወሰኑን ተከትሎ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለስድስቱ ክልሎች እና ለሁለቱ የከተማ መስተዳድሮች የፕሪምየር ሊግ ክለቦች ተዟዙረው በሚጫወቱበት ወቅት ክለቦች በቂ ጥበቃ እንዲያገኙ፣ ጨዋታውን የሚመሩ ዳኞች ንፁህ ዳኝነት እንዲሰጡ እና የክለብ ደጋፊዎች ተገቢውን ቦታ ተሰቷቸው እንዲደግፉ ተገቢ የሆነ የህግ ከለላ እንዲሰጣቸው የክልሎቹ ፕሬዝደንት እንዲሁም የከተማ ከንቲባዎች የህግ ከለላ ማረጋገጫ በደብዳቤ እንዲሰጡ ፌዴሬሽኑም ለሚመለከታቸው አካላት ደብዳቤ እንዲፅፍ ተነጋግረዋል። ይህ ማረጋገጫ ከሚመለከታቸው አካላት የማይገኝ ከሆነ ተዟዙሮ በመጫወት (በውድድሩ ላይ) ተፅእኖ እንደሚያደርግ ተነጋግረዋል።
በይደር የቆዩ አጀንዳዎችን ጨምሮ በሌሎች ጉዳዮች ዙርያ በቀጣይ ሳምንት ቅዳሜ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
© ሶከር ኢትዮጵያ