የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ 0-1 ዩጋንዳ

ዛሬ 10:00 በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም በተደረገ የወዳጅነት ጨዋታ የዩጋንዳ ብሄራዊ ቡድን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን 1-0 አሸንፏል። ከጨዋታው በኋላም የሁለቱ ብድን አሰልጣኞች አስተያየታቸውን በቦታው ለተገኙ ብዙሃን መገናኛዎች ሰጥተዋል።


“በተጨዋቾቼ እንቅስቃሴ ደስተኛ ነኝ” አብርሃም መብራቱ

ጨዋታው እንዴት ነበር?

የዛሬው የወዳጅነት ጨዋታ ባለፈው በሩዋንዳ ጨዋታ የነበረብንን ደካማ ጎኖች አርመን የገባንበት ነው። በተጨዋቾቹ እንቅስቃሴ በጣም ደስተኛ ነኝ። ቡድኑ ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እያየሁ ነው። እንደተመለከታችሁት የዩጋንዳ ቡድን ከሃገር ውጪ ባሉ ተጨዋቾች የተገነባ እና ከምስራቅ አፍሪካ ጠንካራ የሆነ ቡድን ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን በቅርቡ በአፍሪካ ዋንጫም ሲወዳደር የነበረ ቡድን ነው። ስለዚህ ይህንን ቡድን ተቋቁሞ፣ መቋቋም ብቻ ሳይሆን በልጦ መገኘት በራሱ አንድ እድገት ነው ብዬ አስባለሁ። ምንም እንኳን በወዳጅነት ጨዋታ ብንሸነፍም የተሸነፍንበትን መንገድ ማረም ያስፈልጋል። በእስካሁኑ አመጣጣችን የሚቆጠሩብን ጎሎች የቆሙ ኳሶች ናቸው። ይህ ነገር ደግሞ ዋና እያስከፈለን ስለሆነ ጠንክረን እንሰራለን። ከዚህ በተጨማሪ ግብ አካባቢ ያሉ አለመረጋጋቶችንም ለማረም እንሰራለን። በአጠቃላይ የዩጋንዳን ቡድን በልጠን መገኘታችን በስነ ልቦና ለቀጣይ ጨዋታ እንድንነሳሳ ያደርገናል።

ስለ ቡድኑ የዛሬ አቋም እና ስለ ቡድኑ ጠንካራ ጎን?

እኛ በኳስ ቁጥጥሩ የተሻልን ነበርን። እኔ እንደውም ዩጋንዳዎች በአካል ብቃቱ ከእኛ የተሻሉ ስለሆኑ በዚህ ረገድ ይበልጡናል ብዬ አስቤ ነበረ፣ ነገር ግን በጨዋታው በተደጋጋሚ ሲወድቁ የነበሩት እነሱ ናቸው። በአጠቃላይ በአካል ብቃቱም፣ በቴክኒኩም ሆነ በታክቲኩ እኛ ጥሩ ነበርን። ይህ ቢሆንም ግን እነሱ ከልምዳቸው የተነሳ ጨዋታውን ተቆጣጥረው ወተዋል። በእኛ በኩል ከተከላካይ እስከ አማካኝ ያለው ክፍል በጣም ጠንካራ ነው። በዛሬው ጨዋታ ደግሞ ጠንካራ ጎናችን ኳስን ለረጅም ደቂቃ ሳናባክን መጫወታችን ነው። ይህንን ነገር ወደፊት እያዳበርን ከሄድን ቡድናችን ጠንካራ ይሆናል።

ስለ ተጋጣሚ ቡድን?

እነሱ ካገቡት ግብ ውጪ ጠንካራ ሙከራ አላደረጉም።ይህ የሚያሳየው የኛን ጥንካሬ እና በልጦ መገኘት ነው። ከዚህ ውጪ ለዓለም ሲፈተሽ አላየሁም።

“ከሜዳ ውጪ ሁል ጊዜ ጥሩ ጨዋታ ተጫውተክ አታሸንፍም፣ ጥሩ ሳትጫወትም ያገኘከውን እድል አስጠብቀህ መውጣት አለብህ።” ጆናታን ሚክንስትሪ

ጨዋታው እንዴት ነበር?

በመጀመሪያ ኢትዮጵያ በመምጣቴ ደስተኛ ነኝ። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽንም ጨዋታውን ለማድረግ በማሰብ ላመሰግን እወዳለሁ። ጨዋታው ለሁለታችንም የሚጠቅም ነው። በአጭሩ ጨዋታው ለእኛ የሚከብድ ነበረ። ምክንያቱም ተጨዋቾቼን በጊዜ ሳላገኝ ነው ጨዋታውን ያደረኩት። በተቃራኒው ደግሞ ኢትዮጵያኖች ከኛ የተሻለ የውህደት ስራ ለሩዋንዳው ጨዋታ ሰርተው ነው የገጠሙን ስለዚህ በተወሰነ መልኩ ጨዋታው ከባድ አድርጎብን ነበረ። ከዚህ ቀደምም ኢትዮጵያን ሳውቃት በኳስ ቁጥጥር ነው። ኳስን ለመቀማት እስክትቸገር ኳስ ይቀባበላሉ። ዛሬም በተወሰነ ይህንን ሞክረዋል። የሆነው ሆኖ ጨዋታው ብዙ ሙከራዎች ባይደረጉበትም ጥሩ ጨዋታ ነበረ። ባህር ዳር ላይ የነበረው ስሜት ግን የሚገርም ነበረ። አፍሪካ ውስጥ ጨዋታዎችን ከሜዳ ውጪ ማሸነፍ ከባድ ነው። ስለዚህ በውጤቱ ደስተኛ ነኝ።

በሁለተኛው አጋማሽ ስለተበለጡበት ምክንያት

ልክ ነው ለዚህ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ማወደስ አለብን። ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ በሁለተኛው አጋማሽ ወደ ፊት ወተው ለመጫወት ጥረዋል። ከላይ እንደገለፅኩት ደግሞ ብዙዎቹ ተጨዋቾቼ በአጭር ጊዜ ቡድኑን የተቀላቀሉ ናቸው። ስለዚህ ይህ ነገር ፈትኖናል። ከሜዳክ ውጪ ሁል ጊዜ ጥሩ ጨዋታ ተጫውተክ አታሸንፍም። ጥሩ ሳትጫወትም ያገኘከውን እድል አስጠብቀህ መውጣት አለብህ። በአጠቃላይ ግን ተጨዋቾቼ ውጤቱን ለማስጠበቅ ላደረጉት ተጋድሎ ማመስገን እፈልጋለሁ።

በስታዲየም ስለነበረው ድባብ?

እዚህ የነበረው ስሜት የሚገርም ነበረ። እኔ በፊትም የኢትዮጵያ ህዝብ እግር ኳስ እንደሚወድ እና እንደሚደግፍ አቃለሁ። እየተገነቡ ያሉ ስታዲየሞችም እንዳሉ አቃለሁ። ወደፊት ሃገራችሁ አህጉራዊ ውድድሮችን እንደሚያደርግ አስባለሁ። ይህንንም ጊዜ በጉጉት እጠብቃለሁ።


© ሶከር ኢትዮጵያ