ደደቢት ሁለት ተስፈኛ ወጣቶች ሲያስፈርም በርከት ላሉ ተጫዋቾች የሙከራ ዕድል ሰጥቷል

ከአንድ ሳምንት በፊት የቅድመ ውድድር ዝግጅት ጀምረው ስድስት የሚደርሱ ተጫዋቾች ያስፈረሙት ደደቢቶች ባለፉት ዓመታት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ቆይታ ያደረጉት ቃልኪዳን ዘላለም እና ዓብዱልበሲጥ ከማልን አስፈርመዋል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ውጤት የሆነው ቃልኪዳን ዘላለም በኢትዮጵያ ቡና ታዳጊ እና ዋናው ቡድን ቆይታ አድርጎ ባለፈው ዓመት በተሻለ ቡድኑን ማገልገሉ ሲታወስ የአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ መምጣትን ተከትሎ ከቡድኑ ተለያይቶ ደደቢት ተቀላቅሏል።

ሌላው ሰማያዊዎቹን የተቀላቀለው ዓብዱልበሲጥ ከማል ነው። የኢትዮጵያ ቡና ሁለተኛ ቡድን ውጤት የሆነው ይህ ተጫዋች በቡድኑ ተስፋ ተጥሎባቸው ወደ ዋናው ቡድን ካደጉት ተጫዋቾች መካከል አንዱ የነበረ ቢሆንም ብዙም የመጫወት ዕድል ማግኘት ሳይችል ክለቡን መልቀቅ ወደ ደደቢት አምርቷል።

በሌላ ዜና እንደ ባለፈው ዓመት ዘንድሮም በወጣቶች ላይ ለመስራት በዝግጅት የሚገኙት ደደቢቶች በርከት ላሉ ተጫዋቾች የሙከራ ዕድል ሰጥተዋል። ዮሃንስ ፀጋይ፣ ዐቢይ ዓለሙ፣ ክንፈ ኪሮስ፣ ዳዊት ወልዱ፣ ተመስገን ነጋ እና ሰለሞን አረጋዊ የሙከራ ዕድል የተሰጣቸው ተጫዋቾች ናቸው።


© ሶከር ኢትዮጵያ