በወጣው አዲስ ድልድል መሠረት በከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ የተመደበው ስልጤ ወራቤ የአሰልጣኙን ውል ሲያራዝም ረዳት አሰልጣኝ የሾመ ሲሆን ሰባት አዳዲስ ተጫዋቾችንም አስፈርሟል፡፡
በ2011 የውድድር ዘመን ጠንካራ ተፎካካሪ ከሆኑ የከፍተኛ ሊግ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ስልጤ ወራቤ ለዘንድሮው የውድድር ዘመን ራሱን በማጠናከር የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በቅርቡ ጀምሯል፡፡ ክለቡ አስቀድሞ የወጣቱን አሰልጣኝ አብዱልወኪል አብዱልፈታህን ውል ያራዘመ ሲሆን አምና በሻሸመኔ ከተማ በመጀመሪያው ዙር ክለቡን በዋና አሰልጣኝነት መርቶ የነበረው ይልማ ኃይሌን በረዳት አሰልጣኝነት ሾሟል፡፡
ክለቡ ከዚህም በተጨማሪ ሰባት አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርሟል፡፡ ጌቱ ተስፋዬ ግብ ጠባቂ ከቡራዩ ከተማ፣ አብዲ ሁሴን ከቡራዩ ከተማ ተከላካይ፣ ሳሙኤል አሸብር ተከላካይ ከጅማ አባቡና፣ ውብሸት ክፍሌ ተከላካይ ከወላይታ ድቻ፣ አማኑኤል ተፈራ የመስመር አጥቂ ከሺንሺቾ፣ በሱፍቃድ ተሾመ ከሺንሺቾ አማካይ፣ ፍስሀ ቶማስ ከኮንሶ ኒውዮርክ አጥቂ ለክለቡ ፊርማቸውን ያኖሩ ሲሆን በሽር ደሊል፣ ጢሞቲዮስ ቢረጋ፣ አበራ ዓለሙ፣ ፍሬው ኪዳኔ፣ አስቻለው ኡታ እና ተመስገን ዱባ ደግሞ ውል ያራዘሙ ተጫዋቾች ሆነዋል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ