በከፍተኛ ሊግ ተሳታፊ መሆኑ የተረጋገጠው መከላከያ የሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቋል።
በአዳማ ተስፋ ቡድን እና ገላን ከተማ ከአንደኛ ሊግ ወደ ከፍተኛ ሊግ እንዲገባ ካስቻሉ ተጫዋቾች አንዱ በመሆን መልካም የሚባል ዓመታትን ያሳለፈው ግብጠባቂው ሰሚር ነስሮ ከገላን ከተማ ቀሪ ኮንትራት ቢኖረውም አስቀድሞ የተቀበለውን የሁለት ወር ደሞዝ በመመለስ በስምምነት ከተለያየ በኋላ መከላከያን ተቀላቅሏል። በቅርቡ ከግብጠባቂው ምንተስኖት አሎ ጋር ለተለያየው መከላከያ የሰሚር ነስሮ ፊርማውን ማኖር የነበረውን ክፍተት ይደፍናል ተብሎ ይገመታል።
ኢትዮጵያ መድን፣ በደቡብ ፖሊስ የተጫወተው እና ያሳለፍነው የውድድር ዓመት ሰበታ ከተማ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እንዲያድግ ትልቁን ድርሻ ከተወጡ ተጫዋቾች መካከል አማካይ ሀብታሙ ጥላሁን ሌላኛው መከላከያን የተቀላቀለ ተጫዋች ሆኗል። ከቡድኑ ጋር አብሮ ዝግጅት ከጀመረ የሰነባበተው ሀብታሙ መከላከያ ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲመለስ በሚያደርገው ጥረት ውስጥ የጎላ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
በአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው የሚመራው መከላከያ አስቀድሞ አዲስ ካስፈረማቸው ተጫዋቾች ውስጥ ከምንተስኖት አሎ ፣አንተነህ ተስፋዬ፣ ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን፣ አስናቀ ሞገስ እና ሀብታሙ ገዛኸኝ ጋር ቢለያይም ውል ያላቸው ነባር ተጫዋቾችን ጨምሮ አዲስ ፈራሚዎቹ ዘነበ ከበደ፣ አናጋው ባደግ እና ሐብታሙ ወልዴ ከቡድኑ ጋር እንደሚቆዩ ሲረጋገጥ ለ14ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ለመሳተፍ ከቀናት እረፍት በኋላ ዛሬ በአዲስ አበባ ልምምዳቸውን ጀምረዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ