የጆናታን ዊልሰን Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የአማርኛ ትርጉም የዛሬው መሠናዶ የስምንተኛው ምዕራፍ አምስተኛ ክፍልን ይዞላችሁ ቀርቧል።
በ1940ዎቹ መባቻ ስታን ኩሊስ ” በእግርኳስ ተደጋጋሚ የግብ እድሎችን ለመፍጠር ያስችላል፡፡” ብሎ የሚያምንበትን አመክንዮ የሚጋራው ባለሙያ አገኘ፡፡ ብሪጅኖርዝ ከተማ አቅራቢያ በሰፈረው የታላቋ ብሪታኒያ አየር ኃይል (RAF) እዝ ውስጥ በሒሳብ ሹምነት ተመድቦ እየሰራ የወታደራዊ ክንፍ አዛዥነት (Wing-Commander) ማዕረግ ድረስ የደረሰው ቻርለስ ሪፕ የኩሊስን እግርኳሳዊ እሳቤዎች ገቢራዊነት ለማረጋገጥ ጥሯል፡፡ ይህ የአየር ኃይል መኮንን ከ1930ዎቹ መነሻ ጀምሮ በደቡብ ምዕራብ ለንደን ቡሺ ፓርክ ይኖር ነበር፡፡ በ1933 ቻርለስ ጆንስ የተባለው የአርሰናል የቀኝ መስመር አማካይ (Rght-Half) የሰጠውን ሶስት ሰዓታት የሚፈጅና የእግርኳስ አቀራረብ ስልትን የተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ (Lecture) ለሁለት ጊዜያት ያህል ከተከታተለ በኋላ ሪፕ በኸርበርት ቻፕማን የአጨዋወት ዘዴ እጅጉን ተማረከ፡፡ ጆንስ በክለቡ የጨዋታ አቀራረብ ዙሪያ ባቀረበው ገለጻ ኳስ ከኋለኛው የሜዳ ክፍል ወደ ፊት በፍጥነት የሚደርስበት ሁኔታ ላይ አጽዕኖት ሰጥቶ ሲያስተምር ተስተዋለ፤ ቻፕማን በመስመር አማካዮች የጨዋታ ታክቲክ ትግበራ ዙሪያ ያለውን አቋምም በዝርዝር አስረዳ፡፡
የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲያበቃ ቻርለስ ሪፕ በሹመት ወደ ጀርመን ተላከ፡፡ ቆይታውን አጠናቆ በ1947 ወደ ሃገሩ ሲመለስ W-M ፎርሜሽን በብዙዎች ዘንድ ጥቅም ላይ መዋሉን ቢቀጥልም ሌሎቹ የቻፕማን ሐሳቦች ግን ጭራሹኑ ደብዛቸው ጠፍቶ ጠበቁት፤ በዚህም እጅጉን ተበሳጨ፡፡ በወቅቱ የሚደረገው ጨዋታ ዝግ ያለ ሆኖ ታየው፤ የመስመር አማካዮች (Wingers) ከተለመደ ሚናቸው የተለየ መሻሻል እንዳላሳዩ አውጠነጠነ፥ እንደ ቀድሞው ጊዜ ለብቻቸው ተነጥለው አብዶዎቻቸውን ያለ ከልካይ ቢከውኑም ጎል የሚሆኑ ኳሶችን በተሻጋሪ ቅብብል ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በማድረስ በኩል ግን እምብዛም እድገት እንዳላሰመዘገቡ አሰላሰለ፡፡ በ1989 ከግለ ታሪኩ ተቀንጭቦ <ዘ-ፐንተር> በተሰኘ የስኮትላንድ መጽሄት ላይ የወጣ ጽሁፍ በእነዚህ ጉዳዮች የሪፕ ተስፋ መቁረጥ ቀስበቀስ እያደገ ሄዶ በመጋቢት 19-1950 በካውንቲ ግራውንድ የተደረገውን የሲውንደን ታውን ጨዋታ ከተመለከተ በኋላ ሙሉ ትዕግስቱ እንደተሟጠጠ ያስረዳል፡፡
በእርግጥ ከላይ በተጠቀሰው ቀን ማለትም በመጋቢት 19-1950 የተካሄደ ጨዋታ አልነበረም፡፡ ሪፕ ለሚያካሂዳቸው የቁጥራዊ መረጃዎች ትክክለኝነት ከሚሰጠው ከፍተኛ ትኩረት እና ከሚወስደው ጥንቃቄ አንጻር ስህተቱን መቀበል አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ባልተሟላ መረጃ ላይ ተመስርቶ አልያም በተፋለሰ የማስረጃ አያያዝ ተወናብዶ የዕለት መለዋወጥ ገጥሞትም ይሆናል፡፡ እንዲያም ሆኖ በመጋቢት-19 ዋዜማ በነበረው ምሽት በደቡብ እንግሊዝ በተካሄደ የሶስተኛ ዲቪዚዮን ጨዋታ ሲውንደን በሜዳው ብሪስቶል ሮቨርስን 1-0 ረቷል፤ ምናልባትም ሪፕ ከላይ ሊያነሳ የፈለገው ጨዋታ ይህኛው ሳይሆን እንዳልቀረ ይገመታል፡፡ በዚህ ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ የተጋጋለው የማጥቃት ሒደት ምንም ፍሬያማ አለመሆኑን ሪፕ ተገነዘበ፤ ስለዚህም ሁለተኛውን አጋማሽ የሲውንደኖችን እንቅስቃሴ በቁጥሮች እያስደገፈ ሊመዘግብ ወስኖ ተዘጋጀ፡፡ ሁለተኛው 45′ ከተጀመረ በኋላ እርሱ በያዘው ዳታ ባለ ሜዳውዎቹ ሲውንደኖች 147 የማጥቃት ሒደቶችን (Attacks) ከወኑ፡፡ ይህን ያስተዋለው ሪፕ የሚታይ ነገርን መሰረት አድርጎ የማይታየውን ወጥ ስሌት ለማስላት በሚያስችለው ሒሳባዊ ቀመር (Extrapolation) በአንድ ጨዋታ 280 የማጥቃት ሒደቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ሒሳባዊ ግምት አስቀመጠ፡፡ ከእነዚህ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ውስጥም ሁለት ግቦች ሊገኙ እንደሚችሉ አሰበ፡፡ ከማጥቃት ሒደቶቹ አንጻር የሚቆጠሩት የጎሎች መጠን ሲሰላ 99.29 በመቶ የሚሆነው ያለመሳካት ምጥጥን (Failure Rate) እንደሆነ አሳየ፡፡ በአንድ ጨዋታ በአማካይ ሶሥት ጎሎችን ለማግኘት በቀሪው 0.71 በመቶ አይነተኛ መሻሻል ማሳየት በቂ እንደሚሆን አመነ፡፡ ለክለቦች እንደምንም ብሎ ይህን ሰፊ ዕድል ማሳካት መቻል ወደ ላይኛው የሊግ እርከን በቀላሉ የማደግ ዋስትና እንደሚሰጥ ተነበየ፡፡
ቻርለስ ሪፕ ቁጥራዊ ትንታኔዎቹን ይበልጥ ውስብስብ እያደረጋቸው ሄደ፤ ዘመናዊ ምልከታዎቹንም አከለባቸው፡፡ በጨዋታ ወቅት የሁለቱን ተጋጣሚዎች የማጥቃት እንቅስቃሴ (Attacking Moves) እየቆጠረ ይመዘግብ ጀመር፡፡ የምዝገባ አጀማመሩን አስመልክቶም ” ከ1950 በፊት እነዚህን የመሳሰሉ ጥናታዊ ግኝቶች ሙሉ በመሉ ተቀባይነት የሚያገኙበት አጋጣሚ አልተፈጠረላቸውም ነበር፡፡በሒደት ግን ግዜ ትክክለኝነታቸውን አረጋገጠላቸው፡፡ ከሶሥት ጊዜ በላይ ያልተቆራረጠ ንክኪ ባላቸው ቅብብሎች (Received Passes) ከተደረጉ ዘጠኝ የማጥቃት ሒደቶች የሚቆጠሩት ሁለት ግቦች ብቻ እንደሆኑ ታየ፡፡” ሲል ጽፏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከራስ የሜዳ ክልል የሚላኩ ረዣዥም ኳሶች የተሳኩ የማጥቃት ሒደቶችን ለማድረግ ያግዙ እንደነበርም ተመለከተ፤ በተጋጣሚ የሜዳ ክልል ሳጥን ውስጥ አልያም ከሳጥኑ ውጭ የሚገኝ ኳስ የጎል እድሎችን ለመፍጠር የሚያስችል ተመራጩና ውጤታማው ዘዴ መሆኑንም ታዘበ፡፡ በዚህም መንገድ እስከ ስምንት ከሚደርሱ የጎል ሙከራዎች አንዱ ብቻ እንደሚቆጠር አጤነ፡፡
ቻርለስ ሪፕ እነዚህን ጥናቶች በሚያካሂድበት ጊዜ የሚኖረው በዬቴስበሪ አውራጃ ነበር፡፡ እዚያ በሰፈረው የእንግሊዝ አየር ኃይል እዝ ውስጥ የእግርኳስ ቡድኑን ማሰልጠን ጀመረ፡፡ ያን ጊዜ የመስመር አማካዮች (Wingers) እንዴት መጫወት እንዳለባቸው የሚደነግግ ህልዮት አዘጋጀ፡፡ ይህን እውነታ የሚያረጋግጡ በዚያ ዘመን የተመዘገቡ ቋሚ ማስረጃዎች አሁን ላይ በቀላሉ ማግኘት ባይቻልም ቻርለስ ሪፕ በኖርዌያውያን እግርኳስ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩ እሙን ነው፡፡ በኧይቪንድ ላርሰን የተጻፈ ጽሁፍ እንደሚያወሳው እንግሊዛዊው የረዥም እግርኳስ አቀንቃኝና ተንታኝ በ1990ዎቹ የኖርዌይ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ለነበረው ዝነኛው ኤጊል ኦልሰን ስለላከው ሪፖርት በሰፊው ያብራራል፡፡ በእርግጥ ሪፖርቱ በመጀመሪያ የተዘጋጀው በ1954 መጨረሻ እንግሊዝ ከኡሯጓይ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ከማድረጓ ጥቂት ቀደም ብሎ ለዋልተር ዊንተርቦተም ቢሆንም የያኔው የእንግሊዝ አሰልጣኝ ጽሁፉን ያንብበው-አያንብበው የተረጋገጠ መረጃ አልተገኘም፡፡ አብዛኛው የጽሁፉ ትኩረት በ1954ቱ የዓለም ዋንጫ ኡሯጓይ በስኮትላንድ ላይ የግብ ናዳ አውርዳ 7-0 በሆነ ሰፊ ውጤት በረመረመችበት ጨዋታ የተስተዋለውን ድባብ በሙያዊ ምልከታ የዳሰሰ ነበር፡፡
በጽሁፉ ሰፊ ሐተታ ውስጥ የመስመር አማካዮች (Wingers) ወደ ላይኛው የሜዳ ክፍል ተጠግተው፣ የሚሰለፉበትን የጎንዮሽ መስመር ታክከው፣ በ<ጨዋታ ውጭ ወጥመድ> ሳይያዙ ከተከላካዮቻቸው የሚላኩላቸውን ረዣዥም ኳሶች መጠበቅ እንዳለባቸው የሚያሳስብ ጥቆማ ተካቶበታል፡፡ ኳስን በቁጥጥሩ ሥር ያደረገው የመስመር አማካይ አቅጣጫውን ወደ ተጋጣሚ የመከላከል ወረዳ አድርጎ በፍጥነት በመሮጥ የግብ ሙከራውን ለእርሱ በቀረበው የጎል ቋሚ ጎን (Near-Post) ጠንካራ ምት (Shoot) እንዲመታ አልያም ገና ከሩቁ ተሻጋሪ ቅብብል (Cross) እንዲልክ ይመክራል፡፡ በታቃራኒው መስመር የሚገኘው ደግሞ ከኳሱ እንቅስቃሴ አንጻር ለእርሱ በሚቀርበው ወይም ለአቀባዩ በሚርቀው የጎል ቋሚ (Far Post) አካባቢ በመገኘት የመሃል አጥቂውን ለማገዝ እንዲጥር ያሳስባል፡፡ በተዘዋዋሪ የሪፖርቱ አጠቃላይ መልዕክት በ1930ዎቹ መጀመሪያ የቻፕማን የመስመር አማካዮች የሚጫወቱትን ሚና በ1950ዎቹ አጋማሽም የዊንተርቦተም ልጆች እንዲተገብሩ ማዘዝ ነበር፡፡ ዬተስበሪዎች በዚህ የአጨዋወት መንገድ ተጠቅመው ከሆነ ውጤት አምጦላቸዋል ይሆናል፡፡ ምክንያቱም በ1950 በደቡባዊ እንግሊዝ የጦር ሰፈር የተካሄደውን የወታደራዊ ካምፕ የጥሎ ማለፍ ዋንጫ አሸንፈዋልና ነው፡፡
በ1950 መጨረሻ ቻርለስ ሪፕ በድጋሚ ወደ ቡሺ ፓርክ እንዲዛወር ተደረገ፡፡ በቡሺ ፓርክ ከእግርኳስ አጨዋወት ጋር በተያያዘ የሚያቀርባቸው መላ-ምቶች በወቅቱ የብሬንትፎርድ አሰልጣኝ በነበረው ጃኪ ጊቦንስ ትልቅ ትኩረት አገኙለት፡፡ ከዚያም ክለቡ ሪፕን ከየካቲት 1951 ጀምሮ የትርፍ ሰዓት ሥራ ሰጠው፡፡ ሪፕ ቡድኑን ሲቀላቀል የውድድር ዘመኑ ሊገባደድ አስራ አራት ጨዋታዎች እየቀሩ ክለቡ በመውረድ አደጋ ስጋት ውስጥ ይዳክር ነበር፡፡ ብሬንትፎርዶች በቻርለስ ሪፕ አማካሪነትና ጎትጓችነት በአማካይ በጨዋታ ያስቆጥሩ የነበሩትን የጎል መጠን ከ1.5 ወደ 3.00 አሳደጉ፡፡ ወደ ታችኛው የሊግ እርከን ከመውረድ ራሳቸውን ለመታደግም ማግኘት ከሚጠበቅባቸው 28 ነጥቦች 20ውን አሳክተው ከሰቀቀን ተላቀቁ፡፡ ነገርግን ሪፕ በብሬንትፎርድ ብዙ አልከረመም፤ በዚያው ዓመት መጨረሻ ቀድሞ ይኖር ወደነበረበት ብሪጅፎርድ ተመለሰ፡፡
የሮያል ስታስቲካል ሶሳይቲ ሊቀመንበር የነበረው ቤርናርድ ቤንጃሚንና ቻርለስ ሪፕ በ1953 እና 1967 መካከል በነበሩት አስራ ሶሥት ዓመታት ውስጥ በዋነኝነት በእንግሊዝ ሊግ የተደረጉ ግጥሚያዎችን እና በሶሥት የዓለም ዋንጫዎች የተካሄዱ ፍልሚያዎችን አካተው 578 የሚደርሱ የእግርኳስ ጨዋታዎችን አጥንተዋል፡፡ በጥናታቸው ውጤት መሠረትም ከአጠቃላዩ የተጫዋቾች የሜዳ ላይ እንቅስቃሴዎች (Moves) ውስጥ አምስት በመቶ የሚሆኑት ብቻ አራት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ያልተቆራረጡ ቅብብሎችን (Received Passes) ሲያካትቱ ስድስትና ከዚያ የበለጡ ተከታታይ ቅብብሎችን የያዙት ደግሞ አንድ በመቶ የሚሆኑት ብቻ ነበሩ፡፡ ያን ጊዜ በባዝ ዩኒቨርሲቲ በስፖርትና ሳይንሳዊ የሰውነት ማጎልመሻ ትምህርት ክፍል ውስጥ በተጋባዥ መምህርነት ያገለግል የነበረው ኬን ብሬይ <ሃው ቱ ስኮር> የተሰኘ መጽሃፉ ላይ በሪፕና በቤንጃሚን ጥናትና ምርምር ውስጥ የታየውን ከፍተኛ የረዣዥም ቅብብሎች መጠን በማስመልከት ” የዚህ ምክንያቱ እኮ ግልጽ ነው፡፡ ያልተቆራረጡ የአጭር ርቀት ቅብብሎች (Long chains of passes) ተከታታይ በሆነ ድግግሞሽ የሚገኝ ልከኛነት (Accuracy) ያስፈልጋቸዋል፤ በተለይ ተከላካዮች ክፍት ቦታዎችን ለመድፈን በሚጥሩ ጊዜ የእነዚህን ቅብብሎች ቀጣይነት ጠብቆ ማቆየት አስቸጋሪ ይሆናል፤ ኳሱ እንዲደርሳቸው ኢላማ የተደረጉ የቡድን አጋሮች በተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች ሰውን-በ-ሰው በመያዝ በሚደረገው የመከላከል ዘዴ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ወጥመድ ውስጥ ሲገቡ (Man-Marking) አጫጭሮቹን ቅብብሎች ዘላቂና የተሳኩ እንዲሆኑ ማድረግ ያዳግታቸዋል፡፡” በማለት መነሻ ሰበቦቹን ይደረድራል።
ከዚህ ክርክር አንጻር የቻርለስ ሪፕ ድምዳሜ በኳስ ቁጥጥር የበላይነት ላይ ያተኮረ ጨዋታ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝን እንደሆነ ያሳያል፡፡ የእንግሊዙ የአየር ኃይል እና ብሬንትፎርድን በመሳሰሉ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ በሚገኙ ክለቦች ደግሞ የሪፕ ሐሳብ ወደ እውነታ የቀረበ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ የሚገርመው የእግርኳስ አጨዋወት እድገትን ተከትሎ የቻርለስ ሪፕ እሳቤ አለመለወጡ ነው፡፡ በ1980ዎቹ የእንግሊዝ እግርኳስ ማህበር ቴክኒክ ዳይሬክተር የነበረው ቻርለስ ሂዩጅስም ይህንኑ የቻርለስ ሪፕ መላ-ምት እንደወረደ ተቀብሎ ተመሳሳዩን የአጨዋወት ሐሳብ ያራምድ ነበር፡፡ ኬን ብሬይ በመጽሃፉ የቻርለስ ሪፕንም ሆነ የቻርለስ ሂዩጅስን ስህተት ነቅሶ ለማውጣት ወደኋላ ማለቱ እንግዳ ነገር ተደርጎ ተወስዷል፡፡ በ1950ዎቹ በእንግሊዝ እግርኳስ ባልተቆራረጡ የአጭር ርቀት ቅብብሎች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች (Long Passing Moves) እምብዛም የሚዘወተሩ ያለመሆናቸው ሥልቱን የማያስፈልግ አያደርገውም፡፡ ቤተኛ የሆነ አልያም የተለመደ ነገር ሁሉ ጥሩ ነው ማለትም አይደለምና፡፡ በኸርበርት ቻፕማን ዘመን ተጫዋቾች ጨዋታ እንደተጀመረ ኳስ በረዥም ርቀት እንዲቀባበሉ ይበረታቱ ነበር፡፡ በእርግጥ በጊዜው ለግማሽ የውድድር ዘመን የሚሰነብተውን አስቸጋሪ የሜዳ ጭቃ ሊያልፉ የሚችሉት ይህን በማድረግ ብቻ መሆኑ አሳማኝ ምክንያት ይሆናቸዋል፡፡ ያኔ የአጭር ርቀት ቅብብሎች የሚከወኑበት አጨዋወት ተመራጭነት ባይኖረውም ይቆጠሩ የነበሩ ጎሎች እጅግ አነስተኛ መሆናቸው ትስስሩን አስገራሚ አድርጎታል፡፡
የቻርለስ ሪፕን ቁጥራዊ ትንታኔዎች በመጠቀም ቀጥተኛ የእግርኳስ አጨዋወት (Direct Football) ይበልጥ ስኬታማ ስለማድረጉ የሚሞግቱ ወገኖች አደናጋሪ መከራከሪያዎች ሲያቀርቡ ይስተዋላል፡፡ የሪፕ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት እርሱ ጥናት ካካሄደባቸው ጨዋታዎች 91.5 በመቶ የሚሆኑት ማናቸውም የሜዳ ላይ እንቅስቃሴዎች ሶሥት አልያም ከዚያ ያነሱ ቅብብሎችን (Received Passes) ብቻ ይዘዋል፡፡ በጨዋታ ሒደት ውስጥ ጎል ከመቆጠሩ በፊት የሚታዩ ያልተቆራረጡ ቅብብሎች (passes in chain) መጠን ምንም ዓይነት ልዩነት ካላሳየ ሶሥትና ከዚያ በታች በሆኑ ቅብብሎች ከሚካሄዱ እንቅስቃሴዎች ሊገኙ የሚችሉ ጎሎችም በመቶኛ 91.5 መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ ሁሉን አግባቢና ምክንያታዊ ስሌት ነው፡፡ ቀጥተኛ እግርኳስ (Direct Football) ከሌላው አጨዋወት አንጻር የተሻለ ስኬታማ ስልት ከሆነም ከላይ የተጠቀሰው የግቦች አሃዝ ይበልጥ ከፍተኛ ሆኖ መገኘት ነበረበት፡፡ ኬን ብሬይ ግን በቻርለስ ሪፕ ቁጥራዊ ትንታኔዎች ላይ ተመርኩዞ ” ከሁሉም ጎሎች ውስጥ ሰማንያ በመቶ የሚሆኑት ሦስቴ እና ከዚያ በታች የሚደረጉ ቅብብሎችን በያዙ የማጥቃት ሒደቶች የሚፈጠሩ ናቸው፡፡” ሲል ደምድሟል፡፡ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ሪፕ ራሱ ሶሥትና ከዚያ በላይ በሆኑ ቅብብሎች ከተደረጉ ዘጠኝ የማጥቃት ሒደቶች የሚቆጠሩት ሁለት ግቦች ብቻ እንደሆኑ አምኗል፡፡ ይህም ማለት ከዘጠኙ 77.8 በመቶ ግድም የሚጠጉት በሶሥትና ከዚያ በታች በሚሆኑ ቅብብሎች በተካሄዱ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች የተፈጠሩ ጎሎች ናቸው ማለት ነው፡፡ እንደሚታወቀው በ1981-82 የውድድር ዘመን ዋትፎርዶች ካስቆጠሯቸው ግቦች 93.4 በመቶ የተጠጉት ሶሥትና ከዚያ በታች የሆኑ ቅብብሎች ብቻ ባካተቱ የማጥቃት ሒደቶች ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በ1982ቱ የዓለም ዋንጫ ከተቆጠሩት 106 ጎሎች ሶሥትና ከዚያ በታች በሆኑ ቅብብሎች የተመዘገቡት 72ቱ ብቻ አልያም 67.9 በመቶ የተጠጉት ናቸው፡፡
ከላይ የተጠቀሱት አሃዛዊ ማስረጃዎች የሚያሳዩት ነባራዊ ሁኔታ እርግጠኛ ከሆነ ሰማንያ በመቶ ግድም የሚሆኑ ጎሎች የሚገኙት ሶሥት ወይም ከዚያ በታች የሆኑ ቅብብሎችን በሚያካትቱ የማጥቃት ሒደቶች ነው፡፡ ይሁን እንጂ 91.5 በመቶ የሚሆኑት የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ሶሥት ወይም ከዚያ ያነሱ ቅብብሎችን ይዘዋል፡፡ ሪፕ በቀላሉ የምንረዳቸው ሒሳባዊ ቀመሮችን ቢያቀርብልንም እውነታው ግን ሶሥት ወይም ከዚያ በታች በሆኑ ቅብብሎች ከሚደረጉ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ይልቅ አራትና ከአራት በላይ በሆኑ ቅብብሎች የሚካሄዱ የማጥቃት ሒደቶች የበለጠ ውጤታማ ማድረጋቸው ነው፡፡ እነዚህና ሌሎችም የቻርለስ ሪፕ ትንታኔዎች መሰረታዊ የጨዋታ ባህርያትን አለማካተታቸው ትልቅ ስህተት ይመስላል፡፡ ለምሳሌ ያህል በተከታታይ የሚካሄዱ ቅብብሎች በተለያዩ ጥፋቶች (ኃይል በተቀላቀለበት ጨዋታ፣ ኳስን በእጅ በመንካት፣…) ተቋርጠው የቆሙ ኳሶች (Dead-Ball) ከሆኑ በኋላ የሚገኙ ጎሎች በምርምርና ትንታኔው ከግምት አልገቡም፤ ከመልስ ምት፣ ከማዕዘን ምት፣ ከእጅ ውርወራ፣….(Breakdown) የተፈጠሩ ጎሎችም ለጥናቱ በግብዓትነት አልቀረቡም፤ የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ይዞ ተጋጣሚውን የሚያሯሩጥ ቡድን ከባላጋራው አንጻር በቶሎ ያለመድከሙ የሚታወቅ ሲሆን እንዲያውም በመጨረሻ ኳሷን ለማግኘት ሲል በልፋት የዛለው ቡድን ላይ ተደጋጋሚ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ቀላል ተግባር ይሆንለታል፡፡ ይህም እውነታ በእነ ቻርለስ ሪፕ ጥናትና ምርምር ውስጥ ቦታ አላገኘም፡፡ በግልጽ ለማስቀመጥ በዋነኝነት በቁጥራዊ መረጃዎች የተሳሳተ አተረጓጎም ወይም የተዛባ አረዳድ ላይ የተመረኮዘ የጨዋታ ፍልስፍና በእንግሊዝ እግርኳስ የሥልጠናው ዘርፍ የመሰረት ድንጋይ እንዲሆን መፈቀዱ እጅጉን የሚያሳቅቅ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ከምሁራዊ አስተሳሰብ መሸሽ (Anti-intellectualism) ራሱን የቻለ አንድ ማህበረሰባዊ ማነቆ ሊሆን ይችላል፤ ስህተት በሆነ መንገድ የምሁራዊ አስተሳሰብ አራማጅ መስሎ ለመገኘት መጣር (Pseudo-intellectualism) ግን የበለጠ የከፋ ነው፡፡
አንድ እጅግ ወሳኝ የሆነ ቁጥራዊ መረጃ ቻርለስ ሪፕ <ጆርናል ኦፍ ዘ ሮያል ስታቲስቲካል ሶሳይቲ> በሚባል መጽሔት ላይ ካሳተመው ጽሁፍ ተገኝቷል፡፡ ምንም እንኳ ትንታኔው ከሪፕ የጥናትና ምርምር ውጤት አንጻር በተቃራኒው የሚሄድ ቢሆንም በብዙዎች ዘንድ ትኩረት ሳይሰጠው ቆይቷል፡፡ በ1958ቱ የአለም ዋንጫ 1.3 በመቶ የሚሆኑት የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ሰባትና ከዚያ በላይ የሆኑ ቅብብሎችን የያዙ ነበሩ፡፡ ይህ በ1957-58 የውድድር ዘመን በእንግሊዝ ከሁሉም ሊጎች ተመርጠው የተጠኑ ጨዋታዎች ላይ ከተመዘገቡት የ 0.7 በመቶ ጋር የተራራቀ መጠን ነው፡፡ በ1962ቱ የቺሊው የአለም ዋንጫ ወቅት ደግሞ ይኸው ንጽጽር ቀደም ባለው ዓመት ከተወሰዱ የሊግ ጨዋታዎች ጋር ሲተያይ 2.3 በመቶ ለ1.3 በመቶ እንደነበር ከተገኘው ዳታ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በ1966ቱ የዓለም ዋንጫም ቢሆን ከላይ የተነሳው የውድድሮችን ይዘት የተመረኮዘ የቅብብሎች ድግግሞሽ በታላቁ ውድድር 2.6 በመቶ ሲሆን በሊግ ጨዋታዎች ደግሞ 1.2 በመቶ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ እንግዲህ ከላይ የተዘረዘሩት ቁጥሮች ከመጠነኛ ናሙና ሊገኙ ከሚችሉ ትርጉም አዘል ሁለት ድምዳሜዎች ላይ እንድንደርስ ያደርጉናል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ያልተቆራረጡ ተከታታይ ቅብብሎች (Long chain of passes) በሰፊው እየተዘወተሩ የመጡት ከ1958-1962 ድረስ በነበሩት ዓመታት መሆኑን እንረዳለን፡፡ ሁለተኛው ደግሞ እስካሁንም ድረስ ከፍተኛ ትኩረት የሚቸረው ዓለምአቀፍ የብሄራዊ ቡድኖች ጨዋታ ከክለብ እግርኳስ አንጻር በተከታታይ የቅብብሎች ሒደት መጠን በእጥፍ እንደሚልቅ ተረጋግጧል፡፡ ቀጥተኛና ረዣዥም ቅብብሎችን ያካተተው አጨዋወት የበለጠ ስኬታማ ቢያደርግ ኖሮ በእርግጥም በከፍተኛው የእግርኳስ ደረጃ ላይ ቅቡልነቱ ያመዝን ነበርን? በቺሊው እና በእንግሊዙ የዓለም ዋንጫዎች መካከል የተከታታይ ቅብብሎች እድገት ማሻቀቡ ግልጽ ቢሆንም በአጨዋወት ዘይቤዎቹ የተስተዋለው የድግግሞሽ አለመመጣጠን በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ሊቀንስ እንደሚችል ይታወቃል፤ ብዙዎች በወበቅማ የአየር ሁኔታ የኳስ ቁጥጥር ላይ ማተኮር እንደሚመርጡ ማሰብ አያዳግትም፡፡ ቻርለስ ሪፕ ግን ለእነዚህና ሌሎች ከሜዳ ውጭ ላሉ ተጽዕኖ ፈጣሪ ጉዳዮች ምንም አይነት ትኩረት አልቸረም፡፡
ይቀጥላል...
ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡ ባለፉት አስራ ሦስት ዓመታትም አስር መፅሐፍትን ለህትመት አብቅቷል፡፡