ቻን 2016፡ ኮንጎ ዴሞክራቲክ እና ኮትዲቯር ግማሽ ፍፃሜውን ተቀላቅለዋል 

በሩዋንዳ አዘጋጅነት የሚካሄደው የአፍሪካ ሃገራት ዋንጫ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች ዛሬ ቀጥለው ተደርገዋል፡፡ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ እና ኮትዲቯርም ግማሽ ፍፃሜውን የተቀላቀሉ ሃገራት ሆነዋል፡፡ ኮንጎ አዘጋጅዋ ሩዋንዳን 2-1 ስታሸንፍ ኮትዲቯር ካሜሮንን 3-0 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፋለች፡፡ 

ከፍተኛ ፉክክር በታየበት ጨዋታ አዘጋጅዋ ሩዋንዳ በዲሪ ኮንጎ ተሸንፋለች፡፡ ግብ በማግባት ቅድሚያውን የያዙት ኮንጎዎች በዶአ ጊካንጂ አማካኝነት ነበር፡፡ አማቩቢዎቹን የአቻነት ግብ ኧርነስት ሱጌራ በሁለተኛው አጋማሽ አስቆጥሯል፡፡ መደበኛው 90 ደቂቃ የተጠናቀቀውም 1-1 በሆነ ውጤት ነበር፡፡

አሸናፊውን ለመለየት በተጨመረው 30 ደቂቃ የኮንጎው ፓሮ ቦምፑንጋ ሁለተኛ ግብ በማከል ሃገሩን ለግማሽ ፍፃሜ አብቅቷል፡፡ ኮንጎ የመጀመሪያውን የቻን ዋንጫ በ2009 ስታነሳ አሁን ደግሞ ዋንጫውን ለሁለተኛ ግዜ ለማሸነፍ ተስፋ ሰንቃለች፡፡ የኮንጎ አሰልጣኝ ፍሎረንት ኢቤንግ ከ2014 ጀምሮ የተሳካ የአሰልጣኝነት ህይወት እያሳለፉ ይገኛሉ፡፡ በ2014 ኤስ ቪታን ለካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜ ያደረሱት አሰልጣኙ በ2015 የኮንጎ ብሄራዊ ቡድንን በአፍሪካ ዋንጫ 3ተኛ ሆኖ እንዲያጠናቅቅ አስችለዋል፡፡

 

ቀዝቀዝ ብሎ የተጀመረው የኮትዲቯር እና ካሜሮን ጨዋታ ባልተጠበቀ መልኩ በዝሆኖቹ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ በምድብ ጨዋታቸው አንድ ግብ ብቻ ያስተናገደ የተከላካይ መስመር የነበራቸው ካሜሩኖች ሶስት ግብ ማስተናገዳቸው ግርምትን አጭሯል፡፡ ከጨዋታ ጨዋታ እየተሻሻለ የመጣው ዝሆኖቹ የአጥቂ መስመርም በሁለት ጨዋታ ሰባተኛ ግባቸውን አስቆጥረዋል፡፡

ሙሉ የጨዋታ ግዜውን 0-0 የተለያዩት ሁለቱ ሃገራት በተጨማሪው 30 ደቂቃ በተጠቆሩ ሶስት ግቦች ኮትዲቯርን ለፍፃሜ ግማሽ አብቅቷታል፡፡ ለዝሆኖቹ ሶስቱን ግቦች ኮፊ ቦአ፣ አቶቾ ጁኒየር ጆቦ እና ሰርጌ ንገስሳን በስማቸውን አሰመዝግበዋል፡፡ የንገስሳን ግብ የግብ ጠባቂውን ከግብ ክልሉ መውጣት ተመልክቶ ከረጅም ርቀት ያስቆጠራት ግሩም ግብ ነበረች፡፡

ኮትዲቯር የቱኒዚያ እና ማሊን አሸናፊ በግማሽ ፍፃሜ ስትገጥም ኮንጎ ከዛምቢያ እና ጊኒ አሸናፊ ጋር ትገናኛለች፡፡

ያጋሩ