ቻን 2020 | የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለመልሱ ጨዋታ ወደ ኪጋሊ አምርቷል

በባህር ዳር ከተማ ለአስር ቀናት ለቻን ማጣሪያ ዝግጅትን ሲያደርግ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለመልሱ ጨዋታ ወደ ሩዋንዳ ተጉዟል፡፡

ብሔራዊ ቡድኑ በመጀመርያ ግጥሚያው በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም 1-0 ሽንፈት የገጠመው ሲሆን ወደ ቻን ለማለፍ የመልስ ጨዋታውን በማሸነፍ ላይ ብቻ ተመስርቶ ቅዳሜ ኪጋሊ ላይ ይጫወታል። ለዚህም ዛሬ ረፋድ 4:45 ላይ 20 ተጫዋቾችን ጨምሮ በድምሩ ከ25 በላይ የልዑክ አባላት በመያዝ ወደ ስፍራው አቅንቷል፡፡

ብሔራዊ ቡድኑ በዩኒሰን ሆቴል ማረፊያውን ካደረገ በኋላ 24 ተጫዋቾችን በስብሰቡ ውስጥ አካቶ በባህር ዳር ስታዲየም ልምምድን ለአስር ተከታታይ ቀናት ሲሰራ የቆየ ሲሆን ባሳለፍነው ዕሁድ ከዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ጋር የወዳጅነት ጨዋታውን አድርጎ 1-0 ሽንፈትን አስተናግዷል።

አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በጥሩ የተነሳሽነት መንፈስ በጨዋታው ላይ ለመቅረብ ሲሰሩ እንደነበር እና ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ በሚገባ መዘጋጀታቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ አሰልጣኙ አክለውም ጀማል ጣሰው፣ አስቻለው ግርማ፣ ያሬድ ባዬ እና አህመድ ረሺድ በገጠማቸው ጉዳት ወደ ስፍራው እንዳላመሩ ገልፀዋል፡፡

ጨዋታው የፊታችን ቅዳሜ 22 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ስታድ ሪጅናል ኒያሚራምቦ ስታዲየም 10:00 የሚያከናውኑ ይሆናል፡፡

ወደ ሩዋንዳ ያመሩ 20 ተጫዋቾች

ግብ ጠባቂዎች (2)፡ ምንተስኖት አሎ፣ ለዓለም ብርሃኑ

ተከላካዮች (6)፡ አስቻለው ታመነ፣ ደስታ ደሙ፣ አንተነህ ተስፋዬ፣ ጌቱ ኃ/ማሪያም፣ መሳይ ጳውሎስ፣ ረመዳን የሱፍ

አማካዮች (7)፡ አማኑኤል ዮሐንስ፣ ፍፁም ዓለሙ፣ ሐይደር ሸረፋ፣ ዮናስ በርታ፣ ሱራፌል ዳኛቸው፣ ፉአድ ፈረጃ፣ ከነዓን ማርክነህ

አጥቂዎች(5): መስፍን ታፈሰ፣ አማኑኤል ገ/ሚካኤል፣ ሙጂብ ቃሲም፣ ፍቃዱ ዓለሙ፣ አዲስ ግደይ


© ሶከር ኢትዮጵያ