መቐለ 70 እንደርታ የሁለት ተጫዋቾች ዝውውር ሲያጠናቅቅ አንድ ተጫዋች ወደ ዋናው ቡድን አሳደገ

ምዓም አናብስት ፍፁም ተክለማርያምን ወደ ዋናው ቡድን ሲያሳድጉ የሁለት ተጫዋቾች ዝውውር አጠናቀዋል።

ከሳምንታት በፊት በተመሳሳይ ዐቢይ ተወልደን ወደ ዋናው ቡድን ያሳደጉት መቐለ 70 እንደርታዎች ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ከዋናው ቡድን ጋር ልምምድ ሲሰራ የቆየው ፍፁም ተክለማርያምን ወደ ዋናው ቡድን አሳድገዋል። ላለፉት ዓመታት በመቐለ ሁለተኛው ቡድን ቆይታ ያደረገው ተጫዋቹ ከአንድ ዓመት በፊት ከዋናው ቡድን ጋር ልምምድ ቢጀምርም በተለያዩ ምክንያቶች በዋናው ቡድን ዝርዝር ውስጥ ሳይካተት ቆይቶ አሁን ወደ ስብስቡ ተቀላቅሏል።

ሁለገቡ አቤል መብራህቱ ቡድኑን የተቀላቀለ አዲስ ተጫዋች ነው። በመስመር ተከላካይነት እና በአማካይነት መጫወት የሚችለው ይህ ተጫዋች ከዚህ ቀደም በመቐለ፣ ስሑል ሽረ እና ትግራይ ውሃ ስራዎች መጫወቱ ሲታወስ ስሑል ሽረዎች ወደ ከፍተኛ ሊግ ሲያድጉ ጥሩ አበርክቶ ካደረጉት ተጫዋቾች መካከል ይጠቀሳል። ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ከቡድኑ ጋር ልምምድ ሲሰራ የቆየው ተጫዋቹ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ወደ አሳዳጊ ክለቡ ተመልሷል።

ሦስተኛው መቐለን የተቀላቀለው አዲስ ተጫዋች ናይጀርያዊው ኤድዋርድ አግቦር ነው። ባለፉት ዓመታት በኢራቆቹ አል ሲናት፣ ጃኑብ፣ አል ካርባያ እና ካርባላ ለተባሉ ቡድኖች እንዲሁም ለቱኒዚያው ኤቶል ዱ ሳህል የተጫወተው ኤድዋርድ በተከላካይነት እና አማካይነት መጫወት የሚችል ሲሆን ባለፈው የውድድር ዓመት ጠባብ አማራጭ ለነበረው የመቐለ የኋላ ክፍል ጥሩ አማራጭ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ