ኢትዮጵያ ቡና ለ2012 የውድድር ዘመን ካስፈረማቸው ተጫዋቾች መካከል ከብስራት ገበየሁ ጋር በስምምነት መለያየቱ ታውቋል።
የመስመር አጥቂው ብስራት ገበየሁ ወልቂጤ ከተማ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መግባት ከፍተኛ አስተዋፆኦ በማድረግ ካሳለፈው ስኬታማ ቆይታ በኋላ ባሳለፍነው ወር ኢትዮጵያ ቡናን ለሁለት ዓመት ለማገልገል ፊርማውን ማኖሩ ይታወቃል። ሆኖም በባቱ ከተማ ከቡድኑ አባላት ጋር ዝግጅት እያደረገ ከቆየ በኃላ ዛሬ በስምምነት መለያየቱ ተረጋግጧል።
እንደተጫዋቹ ገለፃ ከሆነ “ባለፈው ዓመት ከወልቂጤ ጋር መልካም የሚባል ቆይታ አድርጌ ዘንድሮ ኢትዮጵያ ቡናን መቀላቀል ችያለው። ባቱ ከተማ በነበረው ዝግጅት በቀላሉ ከቡድኑ ጋር በመዋሀድ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ የሚሰጠውን ስልጠና በበሚገባ ስሰራ ቆይቻለው። ሆኖም ከአሰልጣኝ ካሳዬ ውጭ ያሉ አንዳንድ ሰዎች ከኢትዮጵያ ቡና ጋር እንድለያይ ምክንያት ሆነዋል። በዚህም በኢትዮጵያ ቡና የመጫወት ህልሜ ቢጨናገፍም ዳግመኛ የምወደውን ቡድን ወደፊት እንደማገለግል ተስፋ በማድረግ በስምምነት ተለያይቻለው። አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌም መልካም ነገር እንዲገጥመው እመኛለው።” ብሏል።
© ሶከር ኢትዮጵያ