የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ በኅዳር ወር በታንዛንያ አስተናጋጅነት ይከናወናል።
በያዝነው የፈረንጆች የውድድር ዓመት በኤርትራ የተዘጋጀው የሴካፋ ከ 15 ዓመት በታች ጨምሮ ሁለት ውድድሮች በተሳካ ሁኔታ ያካሄደው የምስራቅ እና መካከለኛ አፍሪካ እግር ኳስ የበላይ አካል ሴካፋ በቀጣይ ወር የሴቶች ዋንጫ እንደሚያዘጋጅ ይፋ ሲደረግ ታንዛንያም ውድድሩን ከኅዳር 6 እስከ ኅዳር 20 ታሰናዳለች።
ውድድሩ ኢትዮጵያን ጨምሮ በዘጠኝ ሀገራት መካከል ይካሄዳል ተብሎ ሲገመት ባለፉት ዓመታት ከአህጉራዊ እና ክፍለ አህጉራዊ የእግርኳስ እንቅስቃሴዎች ተገልላ የቆየችው ኤርትራ በውድድሩ ትሳተፋለች ተብሎ ይጠበቃል።
የውድድሩን ዋንጫ ታንዛኒያ ሁለት ጊዜ በማሸነፍ ስትመራ ሊሱዎቹ ለመጨረሻ ጊዜ በተካሄዱ ሁለት ውድድሮች ሶስተኛ ደረጃ ይዘው ማጠናቀቃቸው ይታወሳል። ብርቱካን ገብረክርስቶስም ሩዋንዳ ዋንጫውን ባነሳችበት የ2018 ውድድር ኮከብ ሆና መሸለሟ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።
ከዚህ በፊት ለሶስት ጊዜያት የተካሄደው ውድድሩ በፈረንጆች አቆጣጠር በ1986 ቢጀመርም ከዛ በኋላ ባሉት ሰላሳ ያክል ዓመታት ሳይካሄድ ቆይቶ በ2016 ነበር በድጋሚ መካሄድ የጀመረው።
© ሶከር ኢትዮጵያ